Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሰጣቸው ሦስት ኩባንያዎች ለመንግሥት ጥያቄ አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሳሊኒ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የፋይናንስና የቴክኒክ ድርድር ጀመረ

የጣሊያኑ ግዙፍ ኩባንያ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ የሚሆን ፋይናንስ ማግኘቱን ማረጋገጫ አቅርቦ ወደ ድርድር ቢገባም፣ ሦስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፕሮጀክቱ እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዲስ ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡

ሳሊኒ ቀደም ሲል ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለፕሮጀክቱ የሚሆን ፋይናንስ እንደሚያገኝ ቢገልጽም፣ ከሳምንት በፊት ከጣሊያን ኤግዜም ባንክ 1.5 ቢሊዮን ዩሮ ብድር እንደሚያመጣ መተማመኛ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን፣ ከሳሊኒ ጋር በፋይናንስና በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ድርድር መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

ነገር ግን ይህ ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት የቱርክ ኩባንያ አዝሚር፣ የብራዚል ኩባንያ ፔሮዝና የቻይና ኩባንያ ሲኖ ኃይድሮ የጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንዳረጋገጡት እነዚህ ኩባንያዎች ለግንባታ የሚሆን ፋይናንስ እንደሚያመጡና ለአገር በቀል ኩባንያዎችም ሥራ እንደሚሰጡ በመግለጽ፣ መንግሥት ውስን ጨረታ አውጥቶ አሸናፊ ለሚሆነው ኩባንያ ሥራውን እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለኩባንያዎቹ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፣ በኢትዮጵያ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ጉልህ ሥፍራ የያዘው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ድርድሩን ቀጥሏል፡፡

ሳሊኒ በቴክኒክ ድርድር ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚያምኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች፣ ድርድሩ ረዥም ጊዜ ሊወስድ የሚችለው በፋይናንስ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ከአውሮፓ አገሮች የሚገኝ ብድር ወለዱ ከፍተኛ ስለሚሆን በአዋጭነቱ ላይ መንግሥት ብዙ ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ ሊከት እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርድሩ እየተካሄደ ውሳኔ ባይሰጥም፣ ሳሊኒ በጊቤ አራት ፕሮጀክት ላይ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በደቡብ ክልል በቱርካና ኃይቅ አቅራቢያ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው ጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 1,450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው ቀደም ሲል የተካሄደ ጥናት ያመለክታል፡፡ በጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተካሄደ ባለው ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች