ዜጎች በአገራቸው ውስጥ በሚከናወኑ ማናቸውም ጉዳዮች በእኩልነት የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡ ቅሬታ ሲኖራቸውም ሆነ ደስተኛነት ሳይሰማቸው ሲቀር በፍትሐዊነት መስተናገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም መስኮች በእኩልነትና በፍትሐዊነት መስተናገድ አለባቸው ሲባል፣ ከመንግሥት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ኩባንያዎች፣ ማኅበራትና የመሳሰሉት መዋቅሮች ሁሉ ይመለከታቸዋል፡፡ መንግሥት በኃላፊነት ለሚያስተዳድራቸው ዜጎች ከማንም በላይ ተጠያቂነት ሲኖርበት፣ ሌሎችም ወገኖች ዜጎችን ሳያበላልጡና አድልኦ ሳያደርጉ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የማስተዳደርም ሆነ የማስተናገድ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ እኩልነትና ፍትሕ በሌለበት ከሰላም ይልቅ ብጥብጥና አለመረጋጋት ይንሰራፋል፡፡
ብዙ ጊዜ በፖለቲካዊ መብቶች ላይ ብቻ በመወሰን የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ በእርግጥም እነዚህ መብቶች ዓለም ያፀደቃቸውና መንግሥታትም በቃል ኪዳን ሰነድነት የተቀበሉዋቸው በመሆናቸውና ተፈጥሮአዊም ስለሆኑ መከበር አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት መብቶችም ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ የኢኮኖሚ የበላይነት የያዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሳይቀሩ፣ እኩልነትንና ፍትሐዊነትን ሲገፉ ችግሩ የፖለቲካው ዓውድ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ነገር ግን ዜጎች ለኑሮአቸው ተስማሚ ባልሆኑ ሥራዎችና ከባቢዎች ውስጥ ሆነው ኢፍትሐዊ በሆኑ ክፍያዎች ምክንያት በድህነት ሲቆራመዱ፣ ለኑሮ ተስማሚ ባልሆኑ የተፋፈጉ መንደሮች ውስጥ ሲኖሩ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የጤና እንክብካቤ ሳያገኙ፣ ለልጆቻቸው በቂ ምግብና አልባሳት ማቅረብ ሲቸግራቸውና የኑሮ መከራ ሲጠብሳቸው ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ ከድህነት ወለል በታች ተዘፍቀው ዕድሜያቸውን ይገፋሉ፡፡ እኩልነትና ፍትሐዊነት ቢሰፍን ግን ጥቂቶች በቁንጣን ሲቸገሩ፣ ብዙኃን መከራ አያዩም ነበር፡፡
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 41 የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶችን በተመለከተ ያስቀመጣቸው ጠቃሚ ቁም ነገሮች አሉ፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያ የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት እንዳለው፣ ዜጎች በሙሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው፣ መንግሥት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት እንደሚመድብ በሕገ መንግሥቱ ሠፍሯል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንና ያለወዳጅ ወይም ያላሳዳጊ የቀሩ ሕፃናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ እንደሚያደርግ፣ መንግሥት ለሥራ አጦችና ለችግረኞች ሥራ የመፍጠር ፖሊሲ በመከተል ፕሮጀክቶችን እንደሚያካሂድ፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸውና ለምርት ካደረጉት አስተዋጽኦ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ተገቢ ዋጋ የማግኘት መብት እንዳላቸውና መንግሥት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎችን ሲተልም በዚህ ዓላማ መመራት እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ደንግጓል፡፡
አገሪቱ በሕገ መንግሥቱ ለሰው ልጆች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚጠቅሙ መሠረታዊ መብቶችን ዋስትና ስትሰጥ፣ ተግባራዊነታቸውስ እንዴት እየሆነ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አገር ባላት አቅም የምታመነጭው ሀብት ዜጎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት ሊዳረሳቸው ይገባል፡፡ መንግሥት በሚያወጣው ፖሊሲ መሠረት ዜጎች ሠርተው እንዲተዳደሩ የሚያስችሏቸው የሥራ ዕድሎች መፈጠር አለባቸው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ አማካይነት የሚፈጠሩ ሥራዎች በተቻለ መጠን ለኑሮ በቂ የሆነ ክፍያ ማስገኘት አለባቸው፡፡ የዜጎች የሥራ ደኅንነትና ጤና ጉዳይም ጎን ለጎን መታየት አለበት፡፡ የዜጎችን ጉልበት እየበዘበዙ ተገቢውን ክፍያ የማይከፍሉ ቀጣሪዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ግሽበት ሲከሰት ጫናው ተቀጣሪዎች ላይ ብቻ መውደቅ የለበትም፡፡ መንግሥት በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የምግብ ምርቶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ማረጋጋት ወይም ድጎማ ማድረግ ሲኖርበት፣ መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ቀጣሪዎች የግሽበቱን ጫና መጋራት ይኖርባቸዋል፡፡ በኑሮ ውድነት ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖችን እያዩ ዝም ማለት ኢፍትሐዊነት ነው፡፡ በጣም መሠረታዊ የሚባለው ምግብ ጠፍቶ ሰዎች መራብ የለባቸውም፡፡
መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአቅም በላይ እየሆነ ያለውን የመጠለያ ችግር ለመፍታት እየተፍጨረጨረ ቢሆንም፣ ጥረቱ ግን አመርቂ አይደለም፡፡ መንግሥት ገና ከጅምሩ በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ 30 ሺሕ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በየዓመቱ እየገነባ ለማስረከብ ዕቅድ የያዘው ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ 120 ሺሕ ቤቶች በመገንባት ለዜጎች ለማስረከብ መታቀዱም አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ባለፉት 12 ዓመታት የተገነቡትና የተላለፉት 130 ሺሕ ያህል ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በተደረገ ምዝገባ ከ950 ሺሕ በላይ ዜጎች ወረፋ ይዘዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምዝገባ አልተካሄደም እንጂ የዚህን ያህል ተጨማሪ ተመዝጋቢዎች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡ በመንግሥት አቅም ብቻ ተገንብተው ለዜጎች በወቅቱ የማይደርሱ ቤቶች ጉዳይ፣ የአገሪቱን የመጠለያ ፍላጎት አንሮታል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች በኑሮ ጫና ላይ የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት እያስመረራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአገራቸው በእኩልነትና በፍትሐዊነት እየተስተናገዱ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ለግሉ ዘርፍ ወይም ለውጭ ገንቢዎች ዕድሉን በመስጠት የዜጎችን የመጠለያ ፍላጎት በተቻለ መጠን ለማሟላት ጥረት ካልተደረገ፣ ስለእኩልነትና ፍትሐዊነት ሲወራ አዳማጭ የለም፡፡
ዜጎች በአገራቸው ውስጥ በእኩልነት የልማቱ ተቋዳሽ ናቸው ሲባል ልዩነት ሳይደረግባቸው መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ መንግሥትም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ዜጎችን በሥራም ሆነ በተለያዩ ውሎች የሚያስተዳድሩ ወገኖች በሕግ የተረጋገጠውን እኩልነት የማስፈን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ፍትሐዊ የሆነ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በሕግ የተረጋገጠለትን መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው የሚባለው እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት ጥቂቶችን ሚሊየነር እያደረገ ብዙኃኑን የድህነት አዘቅት ውስጥ መክተት የለበትም፡፡ ዜጎች በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው ዋስትና መሠረት በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸው ሲከበር፣ ከልፋታቸው ጋር የሚመጣጠን ጥቅም ሊያገኙ ይገባል፡፡ ይህ የእኩልነትና የፍትሐዊነት ማሳያ ነው፡፡ ጥቂቶች ያላግባብ እየከበሩ ብዙኃኑ እንዲደኸዩ ማድረግ ደግሞ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 መሠረት ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው የሚለው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ከዚህ የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነ ሕግ በተቃራኒ በመንግሥትም ሆነ በማንኛውም ወገን የሚፈጸም ድርጊት ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ በተደላደለ ጎዳና ላይ የሀብት ተራራ ሲቆልል ሌላው የድህነት አዘቅት ውስጥ መወርወር የለበትም፡፡ በአገሪቱ በሁሉም ሥፍራ እከሌ ከእከሌ ሳይባሉ ኢትዮጵያዊያን የሕግ ጥበቃና ከለላ አግኝተው፣ በመረጡት የሥራ ዘርፍ ተሰማርተውና እንደፈለጉ ተዘዋውረው ሀብት የማፍራት መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሠርተው የመኖር መብታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ለአንዱ የተፈቀደው ለሌላው ሲከለከል፣ አንዱ በሕጋዊ መንገድ ጠይቆ እንቢ ሲባል ሌላው በሕገወጥ መንገድ ሲያገኝ፣ አንዱ ለአገር የሚጠቅም ተግባር እያከናወነ ማግኘት የሚገባውን መብት ሲነፈግ፣ ሌላው አፍራሽ ድርጊት እየፈጸመ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሲሆንለት፣ ወዘተ የአገርን ሰላም ያደፈርሳል፡፡ በዜጎች መካከል ደረጃ በማውጣት የአገሪቱን አንድነት ያናጋል፡፡ እኩልነትና ፍትሐዊነት የሚረጋገጡት በወረቀት ላይ ሳይሆን በተግባር ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር፡፡ ስለሆነም እኩልነትና ፍትሐዊነት በሁሉም መስኮች መስፈን አለባቸው!