Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሰፋፊ እርሻዎች በተፈጠረ ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሥልጣናትን ሊያወያዩ ነው

በሰፋፊ እርሻዎች በተፈጠረ ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሥልጣናትን ሊያወያዩ ነው

ቀን:

በሰፋፊ እርሻዎች ሥራ አፈጻጸም ላይ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፌዴራልና ከክልል ባለሥልጣናት ጋር ሊመክሩ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ስብሰባ የሚጠሩበት ቀን ባይቆረጥም፣ በዚህ ወር መጨረሻ ወይም በጥር ወር መጀመሪያ እንደሚሆን ታውቋል፡፡ በዋናነት ችግሩ የተፈጠረው ለሰፋፊ እርሻዎች የሚሆን ቦታ ለፌዴራል መንግሥት በውክልና በሰጡ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት በውክልና የወሰደውን መሬት እንዲያስተዳድር ኃላፊነት በተሰጠው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መካከል ነው፡፡

የችግሩ ማጠንጠኛ ጉዳይ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከክልሎች 3.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በውክልና ተረክቦ፣ 2.5 ሚሊዮን ሔክታር ለኩባንያዎች አከፋፍሏል፡፡ ነገር ግን ከዚህ 2.5 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ የለማው ከ30 እስከ 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በቅርቡ መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በጠሩት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፣ ለሰፋፊ እርሻዎች ሥራ አፈጻጸም ደካማ መሆን ሁለት ነጥቦች ጎልተው ወጥተዋል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አበራ  ሙላት ባቀረቡት ሪፖርት፣ ለሥራ አፈጻጸሙ ደካማነት ካቀረቧቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የመጀመርያው ለኢንቨስትመንት የተሰጡ ሰፋፊ መሬቶችን ማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ አቶ አበራ ለዚህ ምክንያቱ የኤጀንሲው ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ መሬት በውክልና የሰጡ ክልሎች በጉዳዩ ላይ የጠራ አቋም አለመያዛቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አበራ በተለይ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ሰፋፊ የእርሻ መሬት በውክልና መስጠታቸውን አስታውሰው፣ ሁለቱ ክልሎች መሬት ማስተዳደር በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው መብት መሆኑን በመጥቀስ ሚኒስቴሩ እንዲመልስላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ የክልሎችን መሬት የማስተዳደር መብት የክልሎች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ተፈራ እንዳብራሩት፣ ክልሎች ሰፋፊ እርሻዎችን የማስተዳደር አቅም ገና አልገነቡም፡፡ ብቃታቸውን ካረጋገጡ ግን የፌዴራል መንግሥት በውክልና የወሰደውን መሬት እንደሚመልስ ተናግረዋል፡፡

‹‹የውጭ ኩባንያዎችን መሳብ የፌዴራል መንግሥት ሥራ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎችም ፈቃድ የሚያወጡትና ማበረታቻ የሚያገኙት ከፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የክልሎችን መሬት ፌዴራል መንግሥት ቢያስተዳድር ሥራው የተቃና ይሆናል፤›› በሚል ምክንያት የፖለቲካ ውሳኔ መሰጠቱን አቶ ተፈራ አስረድተዋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በእነዚህ ሁለት ክልሎች፣ እንዲሁም በደቡብና በሶማሌ ክልሎች በርካታ ሰፋፊ መሬቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ኩባንያዎች ሰጥቷል፡፡

በተለይ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ አመራሮች ሰፋፊ እርሻ ለወሰዱ ኩባንያዎች በቂ ድጋፍ ካለመስጠታቸውም በላይ፣ በራሳቸው መንገድ ለሚያስተናግዷቸው ኩባንያዎች ቀደም ሲል ሚኒስቴሩ በሰጠው ቦታ ላይ ደርቦ መስጠት፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሳው የፀጥታ ችግርና የመሬት ወረራ ለሥራ አፈጻጸም ደካማነት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶች ለሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተገቢውን ምላሽ በአግባቡ አለመስጠትና ባለሀብቶች በወሰዷቸው መሬት ላይ ሥራዎችን በአግባቡ አለማከናወናቸውም እንደ ምክንያት  ተጠቅሷል፡፡

አገሪቱ ከሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶች ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንድታገኝ፣ በክልሎችና በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መካከል ያለው አለመግባባት በፖለቲካ ውሳኔ መፈታት ያለበት በመሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ተነግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ በተካሄደው ስብሰባ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት እንደሚካሄድ አቶ አበራ ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ የፌዴራሉ መንግሥት ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባሮች መካከል ለክልሎች ውክልና መስጠት እንደሚችል በአንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 9 ላይ በግልጽ የሠፈረ ሲሆን፣ ክልሎች በውክልና ሥልጣንና ተግባሮቻቸውን መስጠት ስለመቻል አለመቻላቸው አልተቀመጠም፡፡ ይሁንና የሕገ መንግሥቱ ቃለ ጉባዔዎች አርቃቂዎቹ ለፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጥ ውክልናን በጥርጣሬ እንዳዩትና ዋናው ምክንያታቸውም የድርድር አቅም አለመመጣጠን እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኞቹ የፌዴራሊዝምና የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች የፌዴራሉ መንግሥት በውክልና የወሰደውን መሬት የማስተዳደር ተግባርን ይቃወማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...