Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፋይናንስን ጨምሮ በቴሌኮምና በንግድ ዘርፎች ዕጣ ፈንታ ላይ የፖሊሲ ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጅት መጀመሩ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከ12 ዓመታት በፊት የጀመረችው ጉዞ እንዳይሳካ ማነቆ በሆኑት የፋይናንስ፣ የቴሌኮምና የሸቀጥ ንግድ ዘርፎች ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ፣ የፖሊሲ ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጅት መጀመሩ ተሰማ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድ ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱ ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸምን ታኅሳስ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት፣ አገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኮሚቴው አባላት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የድርጅቱ አባል ለመሆን የተጀመረውን ድርድር ለማጠናቀቅ የተያዘው ዕቅድ እንዴት እንደተከናወነ፤ እንዲሁም በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን በተመሳሳይ ድርድሩን የማጠናቀቅ ዕቅድ ለምን እንደተቀመጠና የወደፊት መተግበሪያ ሥልቶቹ እንዲብራሩ የኮሚቴ አባላት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በተነሳው ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ድርድርና ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ልሳነ ወርቅ ጐርፉ፣ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ድርድሩን ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም በኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ በተለይም የአገሪቱን ፖሊሲ የሚነኩ ሦስት ንዑስ ዘርፎች ዕጣ ፈንታን፣ ማለትም ንዑስ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የሚሆኑበት ዝርዝር ዕቅድ በዚህ ወቅት ካልቀረበ በሌሎች ለአባልነት በሚያበቁ ጉዳዮች ላይ ላለመደራደር፣ በዋናነት በአሜሪካ መንግሥት በኩል ቅድመ ሁኔታ በመቀመጡ በኢትዮጵያ የበላይ አመራሮች ድርድሩ ባለበት እንዲቆም መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያን ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የሚያበቃውን ድርድር ማጠናቀቅ ተብሎ በድጋሚ በዕቅድ የተያዘውም በዚህ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ ዕቅድ ቢኖርም አንድ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ አለ፡፡ ይኼውም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ስለፈለገች ብቻ አባል ልትሆን የማትችል መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ለድርጅቱ በርካታ አባል አገሮች ሁሉን ነገር ሰጥተን አንድ የሚፈልገውን ነገር ያላገኘ አገር ሊያቆመን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባ ጥረት ከጀመረች ከአሥር ዓመታት በላይ እንደተቆጠሩ፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ሁለት ዙር ድርድር መደረጉን አቶ ልሳነ ወርቅ ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው ድርድር ከመላው የድርጅቱ አባል አገሮች ጋር ሲሆን፣ በዚህም ሦስት ዙር ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ ቀርበው ለሁለቱ ምላሽ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

አንደኛው አገሪቱ ስለምትፈቅደው የዕቃዎች ታሪፍ መዘርዝር የያዘ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተደረጉት ድርድሮችን ይዘትና ውጤት የያዘ ሰነድ መሆኑን፣ ይህም የዓለም የንግድ ድርጅት የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ ለመከታተል ከአቋቋመው ኮሚቴ ጋር ውይይት ለማካሄድ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአባልነት እንቅስቃሴው በዚህ ደረጃ ላይ እንዳለ ግን ሦስተኛ ዙር ፈታኝ ጥያቄ ለኢትዮጵያ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዕቃዎች የታሪፍ ምጣኔ ሰነድ አቅርባ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ድርድር በጀመረችበት ወቅት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ይህን ሐሳብ የምናየው የአገልግሎት ዘርፍ ሰነድ ሲቀርብልን ብቻ ነው፤›› የሚል ቅድመ ሁኔታ በአሜሪካ መንግሥት መቀመጡን አቶ ልሳነ ወርቅ ለፓርላማው የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል፡፡

ጥያቄው በዋናነት በአሜሪካ በኩል ቢቀርብም በአጠቃላይ የበለፀጉት አገሮች ጥያቄ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉን ክፍት ለማድረግ ኢትዮጵያ ያሰናዳችው ሰነድ ቢኖርም፣ የቀረበው ጥያቄ የሚመለከተው ግን አገሪቱ በፖሊሲ ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ክፍት ያደረገቻቸውን ጥብቅ ጥንቃቄ የሚሹ ንዑስ ዘርፎች ማለትም የፋይናንስ፣ የቴሌኮምና የሸቀጦች ንግድን የሚመለከት በመሆኑ የአገሪቱ አመራር ድርድሩ ባለበት እንዲቆም መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ ድርድሩ ባለበት መቋረጡን ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ድርድሩን ማጠናቀቅ ተብሎ በድጋሚ መታቀዱ ተገቢ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውጪ አማራጭ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ የመጨረሻዎቹ ታዳጊ አገሮች ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከበለፀጉት አገሮች ያገኘቻቸው የገበያ ዕድሎች፣ ማለትም የአሜሪካ አጐዋና የአውሮፓ ኅብረት ከጦር መሣሪያ በስተቀር ማንኛውም ምርት ከቀረጥና ነፃና የኮታ ገደብ ውጪ እንድታቀርብ የሚፈቅዱት ዕድሎች፣ አገሪቱ የመካከለኛ ገቢ አገሮች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስትደርስ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ኢትዮጵያ ጥንቃቄ በምታደርግባቸው የአገልግሎት ሦስት ንዑስ ዘርፎች ዕጣ ፈንታን በተመለከተ ምን ያህል ክፍት እናድርጋቸው? በምን ያህል የመሸጋገሪያ ጊዜ እንክፈታቸው? ወይም የትኞቹን ሰጥተን ምን የተሻለ ነገር እናገኛለን? በሚሉት ነጥቦች ላይ ብቻ ማተኮር ድርድሩን ለማጓተት ካልሆነ በስተቀር ብዙ የሚያዋጣ አካሄድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ፖሊሲዎቻችን ላይ ቀድመን መሥራት እንዳለብን ተገንዝበናል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር ዋነኛ አካሄዱ መሆኑን፣ በዚህ ረገድም የሚዘጋጀው የአገልግሎት ዘርፍ ሰነድ ተጠናቆ በመንግሥት ውሳኔ ሲያገኝ ድርድሩ የሚቀጥል መሆኑንና በዕቅድ ዘመኑ ድርድሩን ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከላይ የተገለጸውን ለማድረግ ስላቀደችና የድርጅቱ አባል መሆን ስለፈለገች ብቻ ሁሉ ነገር ይሳካል ማለት እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር 28 አገሮች የተናጠል ውይይት ማድረግ እንደሚፈልጉ የተናገሩት አቶ ልሳነ ወርቅ፣ በርካቶቹ አገሮች በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ፍላጐት አላቸው፡፡ ይህ ዘርፍ ደግሞ ጥብቅ ጥንቃቄ የሚደረግበት ቢሆንም፣ ይሁን እንጂ ቀይ መስመር አይደለም ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1995 ጀምሮ 34 አገሮች የዓለም ንግድ ድርጅትን የተቀላቀሉ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ልሳነ ወርቅ፣ ሁሉም የፋይናንስ ዘርፋቸውን ክፍት አድርገዋል ብለዋል፡፡ ከፖሊሲ ውሳኔዎች በተጨማሪ የአገሪቱ ሕጐችን ከድርጅቱ ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ፣ እንዲሁም አስፈላጊ ተቋማትን መመሥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች