Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምሥረታ በሚቀጥለው ሳምንት ይደረጋል

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምሥረታ በሚቀጥለው ሳምንት ይደረጋል

ቀን:

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት መሥራች ጉባዔውን ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚያደርግ አደራጅ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡

ታኅሳስ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሆርን ኦፍ አፍሪካ ፕሬስ ኢንስቲትዩት (ሃፒ) የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ሚሚ ስብሐቱና ምክትል ሰብሳቢው አቶ አማረ አረጋዊ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ለዓመታት በሒደት ላይ የነበረው የምሥረታ ሒደት ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በተመድ የስብሰባ አዳራሽ በሚካሄደው ጉባዔ ይደመደማል፡፡

ጉባዔው የሕትመትም ሆነ የሥርጭትም መገናኛ ብዙኃን በሙሉ ፈቃደኝነት በአንድ የሥነ ምግባር ደንብ ለመገዛትና ለሚያገለግሉት ሕዝብ ተጠያቂ ለመሆን ቃል የሚገቡበት በመሆኑ ‹‹ታሪካዊ›› እንደሆነ ወ/ሮ ሚሚ ገልጸዋል፡፡

በመግለጫው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ሒደቱ በርካታ ዓመታትን ለምን ወሰደ? ምክር ቤቱ የሕዝብን ጥቅም ከማስከበርና ሕጎችን የሚያከብር ሚዲያ ከመፍጠር አኳያ ሚናው ምንድን ነው? ምክር ቤቱ የጋዜጠኞችን ሳይሆን የሚዲያ ባለቤቶችን መብት የሚያስከብር ነው መባሉ እንዴት ይታያል? የተቋማቱ የተናጠል ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ከምክር ቤቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ሲጋጭ እንዴት ነው የሚታረቀው? የምክር ቤቱ የገንዘብ ምንጭ ነፃነቱን እንዳይጋፋ ምን ዓይነት አሠራር ይከተላል? የምክር ቤቱ የሕግ ሰውነት እንዴት ይገኛል? በምሥረታ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚከናወኑ ሁነቶች ምንድን ናቸው? የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የምክር ቤቱ ምሥረታ ለመዘግየቱ ዋናው ችግር የባለድርሻ አካላቱ ተሳትፎ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ጽንሰ ሐሳቡ ለአገሪቱ አዲስ በመሆኑና የኢትዮጵያም ሚዲያ ለማጅና የተለያዩ ፅንፎች የያዘ መሆኑ ተጨማሪ የዘገየበት ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ እንዲመሠረት ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ምክር ቤቱ በሚዲያና በሕዝብ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲደረግ፣ ቅሬታ ያለው አካልም ያለ ብዙ ውጣ ውረድ በቀጥታ መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግ ጠቀሜታ ስላለው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ሚዲያው ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት በራሱ ተጠቂነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑና ራሱን በራሱ ስለሚገዛ፣ ኢንዱስትሪውና መንግሥት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የአደራጅ ኮሚቴው አመራሮች አብራርተዋል፡፡ ምክር ቤቱ የሚተገብረው የሥነ ምግባር ደንብም ኅብረተሰቡን በተገቢው ሁኔታ ለማገልገል ቁልፍ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

የምሥረታ ሒደቱ ላይ ትችትና ተቃውሞ ያቀረቡ አካላት የመመሥረቻ ሰነዶቹ ላይ ያሉት ክፍተቶችን በአግባቡ ያልተረዱ ስለነበሩ፣ ከእነዚህ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉም ተጠቁሟል፡፡ ለአብነት ያህልም ከጋዜጠኞች ማኅበር አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ተጠቅሷል፡፡ ሚዲያው በምክር ቤቱ ሥር አብሮ ለመሥራት ተስማምቷል ማለት በእያንዳንዱ ነገር ላይ ይስማማል ማለት እንዳልሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ነገር ግን አንድ የሚዲያ ተቋም የተለየ አመለካከት ስላለው ከሒደቱ እንዳይገለል ጥረት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

የሚዲያ ተቋማቱ የተናጠል የሥነ ምግባር ደንብና የምክር ቤቱ የሥነ ምግባር ደንብ የሚጋጩ እንደማይሆኑም ተገልጿል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ የተናጠል ደንብ ከድርጅቱ ዓላማ አንፃር የተገደበ እንደሆነ፣ የምክር ቤቱ ደንብ ግን በሙያው ስምምነት የተደረገባቸውን ድንጋጌዎች እንደሚያካትት ወ/ሮ ሚሚና አቶ አማረ አስረድተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ የሕግ ሰውነትን በተመለከተ የኮሚቴው አባላት ከመንግሥት ጋር ውይይት እንዳደረጉና ከምሥረታው በኋላ መፍትሔ እንደሚፈለግለት መንግሥት ቃል መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ተቋም የሚስተናገድበት መንገድ ላይ መንግሥት ጥናት እንደሚያደርግ ቃል ገብቶልናል፡፡ መሰል ተቋም ኖሮ ስለማያውቅ የሚመዘገብበት ሁኔታ የራሱ የሆነ መሥፈርት ሊወጣለት እንደሚችል ተነጋግረን ሒደቱን ቀጥለናል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሚሚ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ በአደራጅ ኮሚቴው ሳይሆን በመሥራች ጉባዔው በሚመረጠው ሥራ አስፈጻሚ የሚቀረፍ እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡

የምክር ቤቱ የገንዘብ ምንጭ ከየትና እንዴት ይገኛል የሚለው ጉዳይ እስካሁን የልዩነት ምንጭ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ አቶ አማረ ‹‹አሁንም ቢሆን ይሄ ጉዳይ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው፡፡ ከአባላቱ አቅም ጋር የተገናዘበ መዋጮ በማድረግ ራሱን እንዲችል ታስቧል፡፡ ከውጭ የሚመጣ ዕርዳታ በአባላት ጉባዔ ሳይፀድቅ ተግባራዊ መሆን የለበትም የሚል አቋም ላይ ተስማምተናል፤›› ብለዋል፡፡

በመመሥረቻ ጉባዔው፣ በሥነ ምግባር ደንቡና በመመሥረቻ ጽሑፉ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ውይይት እንደሚደረግና እንደሚፀድቅ ተነግሯል፡፡ በዕለቱም መሥራች አባላት በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ይጠበቃል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አባላት ጋዜጠኞች ሳይሆኑ ተቋማት ይሆናሉ፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...