Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየ152 የሙስና ወንጀል ተከሳሾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታቸውን አቀረቡ

የ152 የሙስና ወንጀል ተከሳሾች ቤተሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታቸውን አቀረቡ

ቀን:

  • ‹‹ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበን በአጭር ቀን ምላሽ እንሰጣለን››

የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 152 የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ፣ ከ60 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተገኝተው አቤቱታቸውን አሰሙ፡፡

የተከሳሾቹ ቤተሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝተው አቤቱታቸውን ማቅረብ ባይችሉም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕግ ክፍል ሠራተኛ እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡ አቤቱታቸውን ካሰሙም በኋላ ለካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳ እንደሚያቀርቡና ምላሹን እንደሚያሳውቋቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

አቤቱታውን ያቀረቡት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በ2009 ዓ.ም. መጠናቀቂያ ወራት ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው በተለያዩ የክስ መዝገቦች ክስ የተመሠረተባቸው የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴርና ሌሎችም ተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች የተውጣጡ መሆናቸውን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች ያቀረቡት አቤቱታ እንደሚያስረዳው ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር፣ የልማት እንቅፋት እንደሆነና በሙስና ውስጥ እኩል ተጠቃሚነት ሊኖር እንደማይችል ያምናሉ፡፡ በዚህ ረገድም መንግሥት እየወሰደ ያለውን ቁርጠኛ አቋም በፅኑ ይደግፋሉ፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው (ተጠርጣሪዎቹ) ከግልም ሆነ ከመንግሥት ተቋማት በሙስና ሽፋን ታፍሰው በሐሰት በተቀነባበረ ምስክርነት መታሰራቸውን፣ ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብታቸው ተረግጦ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡  

የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች ጨምረው እንዳስረዱት፣ ሌሎች የልማት እንቅፋት በሆኑ በትልልቅ ዓሳዎች ፈንታ ማረሚያ ቤት ተወርውረው እንደሚገኙ ትልቅ ምስክር የሚሆነው የተመሠረተባቸው ክስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደርሰውበታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት በወቅቱ ኅብረተሰቡ ዳር እስከ ዳር አንስቶት የነበረውን ተቃውሞ በሽፋን ለማለፍ፣ በጥቂት ግለሰቦች ትዕዛዝ በተቀነባበረ የሐሰት ውንጀላ ማረሚያ ቤት ተወርውረው፣ ታሳሪ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ እነሱ በመንገላታት ላይ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያውቁላቸው ማመልከታቸውን አቤቱታ አቅራቢ ቤተሰቦች አስረድተዋል፡፡ በታሳሪ ቤተሰቦቻቸውና በመንግሥት መካከል እምነት እንዳይኖርና መቃቃር ጠንክሮ እንዲቀጥል መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በታሳሪ ቤተሰቦቻቸውም ሆነ በእነሱ ላይ (አቤቱታ አቅራቢዎቹ ላይ) ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የሥነ ልቦና ውድቀት መድረሱንም አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪ ቤተሰቦቻቸው በተቀነባበረ ሴራ ቢሮ ውስጥ በፈረሟቸው ተራ የቢሮክራሲ ወረቀቶች ተከሰው ከመጉላላታቸውም ባሻገር፣ የቀረበባቸውን የክስ ድርጊት አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪ ቤተሰቦቻቸው ቢያጠፉም ‹‹መጠየቅ የለባቸውም›› እያሉ እንዳልሆነ የገለጹት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ነገሩ ‹‹ላም ባልዋለበት . . . ›› ስለሆነባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲመለከቱላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለማስፈጸም ተግተው በመሥራት ላይ እንደነበሩ ጠቁመው፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ሀብት ያካበቱ ቡድኖችና ግለሰቦች ሳይነኩ፣ እነሱ በሐሰት በተቀነባበረ ወንጀል ለእስር መዳረጋቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት ሰጥተው ጉዳዩ እንዲመረመር እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበዓለ ሲመታቸውም ዕለት ሆነ ሌሎች ሚኒስትሮችን ባሾሙበት ዕለት እንደተናገሩት፣ በተደራጀ መንገድ ሙስናን ለመታገል ያስቀመጡትን አቅጣጫ በፅኑ እንደሚደግፉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ የተጠርጣሪ ቤተሰቦቻቸውም ጉዳይ በተገቢው ሁኔታ ታይቶና ተጣርቶ፣ ንፁህነታቸው እንዲረጋገጥና የብሔራዊ ዕርቁ አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥትም በሙስና ላይ በሚወስደው እውነተኛ ዕርምጃ ተባባሪ ሆነው ከጎኑ እንደሚቆሙም አክለዋል፡፡

በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉት ያለው ዕርቅ ግማሽ እንዳይሆን አቤቱታቸውን በተገቢው ሁኔታ ታይቶና ፍትሕ አግኝተው ታሳሪ ቤተሰቦቻቸው ከእስር ተፈትተው፣ በአገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል ያገባናል በማለት በአንድነት እንዲሠለፉ እንዲያደርጉላቸው ተማፅነዋል፡፡

የተጠርጣሪ ቤተሰቦች አቤቱታውን ሲያቀርቡ ምንም እንኳን ተስፋ በቆረጠ አኳኋን መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት በአገር ደረጃ በተለይም በፍትሕ ዘርፍ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እየወሰደ ያለው ቁርጠኝነት አቋም ተስፋ ስለሰጣቸው መፍትሔ እንደሚያገኙ እምነት ስላደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳያቸው በተገቢው ሁኔታ በአስቸኳይ ታይቶላቸውና መፍትሔ ተሰጥቷቸው፣ ታሳሪ ቤተሰቦቻቸው ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ባላቸው የረዥም ጊዜ ልምድና ዕውቀት በመጠቀም አገራቸውን እንዲያገለግሉ፣ ልዩነት ሳይፈጥሩ በአንድ ላይ በያገባናል ስሜት ለጋራ ልማት እንዲሠለፉ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...