Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኢኮኖሚውን ነገር እስኪ እንነጋገር!

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ገለጻ አንድ ያወሱት ቁምነገር ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እያደገች ናት፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር ሕዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አለብን፤›› ማለታቸው ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለአገሪቱ ሕዝብ የመዳረሱ ጉዳይ መቼም ቢሆን ችላ መባል የሌለበት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን አፅንኦት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የግብይት ሥርዓቱ አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አጠቃላይ የኢኮኖሚው ይዞታ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ጉዳይ በርዕሰ ጉዳይነት አንስቶ ለመነጋገር ሲፈለግ ደግሞ፣ ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው መሠረታዊ አቅርቦቶች መነሳት ተገቢ ነው፡፡ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ ግሽበት ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡

  የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት በገበያው ውስጥ እየተለመደ በመምጣቱ ስኳር፣ ዘይት፣ ዳቦ፣ እንቁላል፣ ወተትና የመሳሰሉ ምርቶች አቅርቦት በጣም አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በአንዳንድ የግብይት ሥፍራዎች ለማዳረስ ሲባል የኮታ አቅርቦት ተጀምሯል፡፡ የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ቢያንስ አራት ጊዜ ጭማሪ የታየባቸው ምርቶች አሉ፡፡ የኑሮ ውድነት እንደ ሰደድ እሳት የሚለበልበው ሕዝብ በመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ ግሽበት ሲመታ ሌላ ቀውስ ስለሚፈጠር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከወር ገቢው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለቤት ኪራይ እየከፈለ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር የሚያጋጥመው የወር ደመወዝተኛ፣ እንዴት ተረጋግቶ ሥራውን ሊያከናውን ይችላል? በዚህ ላይ ለልጆች ምግብ፣ ልብስ፣ ትምህርትና መሰል ወገብ አጉባጭ ወጪዎች ሲዳረግ ደግሞ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› ይሆንበታል፡፡ መንግሥት ይኼንን ሥር የሰደደ ችግር በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የመፍትሔ አማራጮች በመጠቀም ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

  የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮች ከፊቱ እየተጋረጡበት ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከል አንደኛው ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝና መድከም ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ አስቸኳይ ዕርምጃ ካልተወሰደ አምራች ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ ቀጥ ሊል ይችላል፡፡ የተለያዩ ምርቶችን የሚፈበርኩ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በተደጋጋሚ እንዳሉት፣ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ምክንያት ከአቅማቸው በታች ከማምረት አልፈው ለመዘጋት የሚገደዱበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአማካይ 51 በመቶ ከመጨመሩም በላይ፣ በገበያው ውስጥ ከፍተኛ እጥረት የሚታይባቸው ግብዓቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የቅድሚያ ቅድሚያ ያገኙ ከነበሩ መሠረታዊ ከሚባሉ አቅርቦቶች ውስጥ መድኃኒት ዋነኛው ቢሆንም፣ ኢንሱሊንን የመሳሰሉ ሕይወት አድን መድኃኒቶች ከገበያ እየጠፉ ነው፡፡ ሌሎች በርካታ በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ማግኘት እያዳገተ በመሆኑ የሕሙማን ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡

  የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ባለመመራቱና ቁጥጥር ስለማይደረግበት፣ ለአገር ፋይዳ ለሌላቸው ተራ ጉዳዮች ሲባክን ተስተውሏል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚኮበልለው የውጭ ምንዛሪ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ያሸሹ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲመልሱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህ መሆን ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ግንዛቤ በመያዝ፣ በሌላ በኩል ግን አፋጣኝ የሆኑ ተከታታይ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ በአገሪቱ እያጋጠመ ያለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና መዳከም በግልጽ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ላይ እየታየ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ በእንጀራ ዋጋ ላይ ጭምር በየዕለቱ ለውጥ እያታየ ነው፡፡ በሌሎች ሸቀጦች አቅርቦት ላይ እጥረት ሲፈጠርም የዋጋ ለውጡ ይቀጥላል፡፡ ይኼም የዜጎችን ምሬት ያባብሳል፡፡ ሌላ ቀውስ ያመጣል፡፡

  የኑሮ ውድነቱ ማኅበራዊ ቀውስ ከሚፈጥርባቸው ችግሮች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ራሱ እየገነባ፣ እየተቆጣጠረና እያከፋፈለ በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ባለመቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበው የመንግሥት የጋራ ቤቶች ግንባታ ስትራቴጂ፣ አዋጭ የሆነ ጥናት ተካሂዶበት መሠረታዊ ለውጥ ካልተደረገ ሌላው የአገር መከራ ይሆናል፡፡ ‹እስካሁን ይኼንን ያህል ቤቶች በመገንባት ስኬት አስመዝግቤያለሁ› የሚለው መንግሥታዊ አካል፣ ራሱን ከማታለል ወጥቶ ለመፍትሔው እንዲተጋ ቢጥር መልካም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ይገኛሉ፡፡ በካፒታሊስት ነፃ ኢኮኖሚ እየተመሩ ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ውስጥ መደበቅ ፋይዳ የለውም፡፡ ቤት ገንብቶ ለብዙኃኑ ማስረከብ የሚቻለው በተግባር የተፈተኑ ተሞክሮዎችን ከተለያዩ አገሮች በመቃረምና ከአገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ መሆኑን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ በቤት ኪራይ እየተጠበሰ ኑሮውን መምራት ያቀተው ሕዝብ መልሶ መንግሥት ላይ ማፍጠጡ አይቀርም፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  በአጠቃላይ በገጠርም ሆነ በከተማ ነዋሪዎች ላይ የኢኮኖሚው አሉታዊ ተፅዕኖ ሲጨምር ቀውስ ይፈጠራል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችም ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት ከመቀዛቀዝ አልፈው ይዳከማሉ፡፡ የገንዘብ ዝውውር ከሌለ ጎዳና ላይ ከሚነግዱት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ደረጃ ያሉት ሥራቸው ይታወካል፡፡ የዕለት ጉርሱን ሲያሳድድ የሚውለውና በወርኃዊ ገቢ የሚተዳደረው ኢትዮጵያዊ ጭምር ፈታኝ በሆነ የኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ነው፡፡ መንግሥት ይኼንን ሥር የሰደደ ችግር በመረዳት አገር የሚያከስሩ የማያዋጡ ፕሮጀክቶችን በማዘግየት ሕዝብ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለበት፡፡ ይህ ውሳኔ መረር ቢልም ከተጋረጠው ችግር አንፃር መጨከን የግድ ይላል፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮ የዜጎችን አቅም እየተፈታተነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አገርን እያከሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን በማቆም ሕዝብን መታደግ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ገበያውን የሚያመሰቃቅሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን በመከታተል ማስቆም የግድ ነው፡፡ ገበያው ውስጥ ተደራጅተው የገቡ ሕገወጦች የግብይት ሥርዓቱን እያፋለሱት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመፈተሽ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከፖለቲካው የባሰ የኢኮኖሚው ቀውስ አገር ላይ ችግር እንደሚፈጥር መታመን አለበት፡፡ የኢኮኖሚው ጉዳይ ብርቱ የሆነ ንግግር ያስፈልገዋል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  የቴሌቪዥን ፈቃድ ክፍያ የማይከፍሉ በወንጀል እንዲቀጡ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ውድቅ ተደረገ

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015...

  ክፍያ የፈጸሙ ተገልጋዮች ሁሉ አስቸኳይ ፓስፖርት እንዲያገኙ ሊደረግ ነው

  በኢሚግሬሸንና ዜግነት አገልግሎት አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...