ለአገራዊ የስንዴ እጥረት መፈጠር ምክንያት የሆነው የ400 ሺሕ ቶን ስንዴ ግዥ አሁንም አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ስድስት ወራት ሙሉ የተጓተተው የስንዴ ጨረታ ገዥውን አካል ማለትም የመንግሥት ግዥዎችና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትን ለወቀሳ ዳርጎታል፡፡ ከዚህ ቀደም ጨረታው በወጣበት ጊዜ ሻኪል የተባለ የፓኪስታን ኩባንያ 2.6 ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ጨረታውን አሸንፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ኩባንያው የውል ማስከበሪያ ሰነድ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ግዥውን እንዲፈጽም የተመደበው መሥሪያ ቤት ኩባንያው ያቀረባቸውን ሌሎች አማራጮችን ባለመቀበሉ ጨረታው ሊሰረዝ ችሏል፡፡
በመቀጠል ሁለተኛ ጨረታ ወጥቶ ፕሮሚሲንግ የተባለ ኩባንያ 2.7 ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ ዋጋ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ኩባንያው አጨቃጫቂ በሆነ መንገድ የቴክኒካል ግምገማ አላለፈም ተብሎ ከጨረታው ውድቅ ተደርጓል፡፡ ሌላው በጨረታው 2.9 ቢሊዮን ብር ዋጋ አቅርቦ የነበረው ኤዲኤም የተባለ ኩባንያ ያቀረበው ዋጋ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ካለው የስንዴ ዋጋ ከፍ ያለ ነው ተብሎ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በተፈጠረ መጓተት በአገሪቷ የስንዴ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ለሦስተኛ ጊዜ ጨረታ ለማውጣት የተገደደው አገልግሎቱ፣ 400 ሺሕ ቶን ስንዴ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ ከሳምንታት በፊት ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህን ሲያደርግም ከመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ባገኘው ፈቃድ የግዥ ሒደቱን ለማፋጠን ተብሎ ለ21 ቀናት ብቻ ጨረታው አየር ላይ እንዲውል ተደርጎ ነበር፡፡
ስንዴው በዋናነት ተገዝቶ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለዳቦ ቤቶች በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች በኩል መከፋፈል የነበረበት ቢሆንም፣ በጨረታው መጓተት ምክንያት የተጠቀሱት ዳቦ ቤቶችና የዱቄቶች ፋብሪካዎች እየተቸገሩ ይገኛሉ፡፡
የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን ዓርብ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ይከፍታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ በጎን ከተጫራቾች የሚገዛው 400 ሺሕ ቶን ስንዴ በግማሽ መቀነሱንና ጨረታውን የሚከፍትበት ቀንም ከግንቦት 10 ወደ ግንቦት 17 ቀን ማራዘሙን ሪፖርተር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቀሪውን 200 ሺሕ ቶን ስንዴ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. በተመሳሳይ በወጣ ጨረታ ለብሔራዊ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ለማከፋፈል የወጣውን ጨረታ አሸንፎ የነበረው ፕሮሚሲንግ ኩባንያ እንዲያቀርብ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጊዜው ለኮሚሽኑ የሚቀርበው ስንዴ አጠቃላይ መጠን 400 ሺሕ ቶን የነበረ ቢሆንም፣ በጨረታው 200 ሺሕ ቶን የሚሆነውን ፕሮሚሲንግ በ1.64 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ አሸንፎ ነበር፡፡ ቀሪውን 200 ሺሕ ቶን ስንዴ ደግሞ ኢንትሬድ የተባለ ኩባንያ በ1.655 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ አሸንፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት ፕሮሚሲንግ አብዛኛውን ስንዴ ለኮሚሽኑ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሳምንት በፊት በወጣው ጨረታና በአገሪቱ ከተከሰተው የስንዴ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ውሳኔውን በመጨረሻ በመቀየር፣ ፕሮሚሲንግና ኢንትሬድ እያንዳንዳቸው ካቀረቡት መጠን በተጨማሪ 200 ሺሕ ቶን ስንዴ ከዚህ በፊት ባቀረቡት ዋጋ ማቅረብ ይችሉ እንደሆነ መጠየቁን፣ በዚህም ፕሮሚሲንግ የተባለው ኩባንያ ሙሉውን ለማቅረብ መስማማቱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በአገሪቱ የግዥ ሕግ መሠረት ገዥው አካል አንድ ጨረታ ካወጣም ሆነ ከአቅራቢው ጋር ውል ከገባ በኋላ በሚቀርበው ዕቃ ላይ እስከ 25 በመቶ ብቻ የመጠን ማስተካከያ ማድረግ ይችላል፡፡
ነገር ግን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከሕጉ በተቃራኒ የ25 በመቶውን ጣሪያውን በማለፍ የ50 በመቶ የመጠን ጭማሪ ከዚህ ቀደም ፕሮሚሲንግ በገባው ውል ላይ ማስተካከያ በማድረግ፣ 200 ሺሕ ቶን ስንዴ በተጨማሪ እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
ይህ ድርጊት በአገሪቱ የግዥ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ያሉት ሪፖርተር ያናገራቸው የግዥ ባለሙያ፣ ኤጀንሲው በልዩ ሁኔታ ያለውን አገራዊ የስንዴ እጥረት አይቶ ካልፈቀደ በስተቀር ገዥው አካል በሚገዛው መጠን ላይ ከ25 በመቶ በላይ ማስተካከያ ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሮሚሲንግ 200 ሺሕ ቶን ስንዴውን በተመሳሳይ በ1.64 ቢሊዮን ብር እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡ የአገልግሎቱን ውሳኔ በተመለከተ ሪፖርተር ያናገራቸው የግዥ ባለሙያዎች፣ አገልግሎቱ አሁን ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት ሲል የወሰነው ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከተገዛ ስንዴ የግዥ ውልና የሚገዛላቸው ተቋማትም የተለያዩ ሆነው እያሉ፣ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ለመድረስ ባይገደድ ሲሉ ባለሙያዎቹ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ጨረታ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተወዳዳሪ የነበረው ሻኪል የተባለው ኩባንያ ጨረታው ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ቢሆንም፣ የጨረታ ሰነድ መግዛትም ሆነ በጨረታው መሳተፍ እንደማይችል መከልከሉን የኩባንያው ኃላፊ አቶ ሻኪል አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ወጥቶ በነበረው ጨረታ ኩባንያው አሸንፎ ባለመቅረቡ በወቅቱ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ኤጀንሲውን ከዚህ በኋላ በሚወጡ ጨረታዎች ለተወሰነ ጊዜ መሳተፍ እንደማይችል እንዲከለከል መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ኤጀንሲው ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ሻኪል ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ የውል ማስረከቢያ ሰነድ ማቅረብ አለመቻሉ ስህተት መሆኑን ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ ለአገልግሎቱ በጻፉት ደብዳቤ ሻኪል ሰነዱን ማቅረብ ባይችልም፣ ከዚህ በኋላ በሚወጡ ጨረታዎች ለመሳተፍ የሚያሳግድ አለመሆኑን ሚያዚያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
የሻኪል ተወካዮች ግን በጨረታው መሳተፍ እንደማይችሉ በቃል እንደተገለጸላቸው፣ ሰነዱንም እስከ ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ባለው መግዛት እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ይከፈታል ተብሎ በሚጠበቀው ጨረታ ፕሮሚሲንግን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስንዴ አቅራቢዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስለጉደትውለውዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ሪፖርተር ጠይቋቸው፣ ሻኪል በጨረታው የመሳተፍ መብት እንዳለውና ስለመከልከሉ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ለፕሮሚሲንግ ኩባንያ የተሰጠው ተጨማሪ 200 ሺሕ ቶን ስንዴ የማቅረብ ውልና የ50 በመቶ ማስተካከያን በተመለከተም ከኤጀንሲው ልዩ ፈቃድ እንዳገኙ አስታውቀዋል፡፡