Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሥራ ያቆመውን የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥራ ለማስጀመር ውይይት...

በኦሮሚያ አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሥራ ያቆመውን የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥራ ለማስጀመር ውይይት ሊካሄድ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያ አርሶ አደሮች ተቃውሞ ሥራ ያቆመውን የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥራ ለማስጀመር፣ ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ያቋረጠውን ውይይት ሊጀምር መሆኑ ታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የከተማውን ደረቅ ቆሻሻ በዘመናዊ መንገድ ለማስወገድ የገነባው የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ምክንያት ሥራ በጀመረ በሰባት ወሩ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ይታወሳል፡፡

      የከተማው አስተዳደር የሰንዳፋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ጣቢያ በተቃውሞ ምክንያት ሥራ በማቆሙ፣ በድጋሚ ወደ ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ (ቆሼ) ተመልሶ የከተማውን ቆሻሻ በማስወገድ ላይ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሰንዳፋ በመመለስ ደረቅ ቆሻሻ ለማስወገድ ዕቅድ በማውጣት ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከወረዳና ከዞን፣ እንዲሁም ከሚመለከታቸው የክልል ባለሥልጣናት ጋር የከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ተደጋጋሚ ስብሰባዎች አካሂዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሦስት ወራት በፊት ባገረሸው ተቃውሞ ምክንያት የዘመናዊው ቆሻሻ ማስወገጃ ማሽኖች በመቃጠላቸው ሲካሄድ የቆየው ውይይት ያለውጤት ተቋርጦ ነበር፡፡

      የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍስሐ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዘመናዊው የቆሻሻ ማስወገጃ በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ምክንያት ቆሞ ነበር፡፡

      ‹‹ከአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ከወረዳና ከዞን እንዲሁም ከክልሉ የበላይ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረናል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ ‹‹ከአካባቢው ነዋሪዎች የቀረቡ ቅሬታዎችን በተለይም ከቆሻሻ ማስወገጃው የሚወጣውን ሽታና ዝቃጭ ለመቀነስ ስምምነት ላይ በመድረስ ማሽነሪዎችን ገዝተን ነበር፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በድጋሚ በተነሳው ሁከት ማሽነሪዎቹ ተቃጥለዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

      አቶ ኃይሌ ጨምረው እንደገለጹት፣ የከተማው አስተዳደር አሁን አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ ለማቋቋም ዕቅድ የለውም፡፡ አስተዳደሩ የተቋረጠውን ውይይት በመቀጠል ከነዋሪዎች የተሰጡ ማስተካከያ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃን በድጋሚ ወደ ሥራ ለማስገባት አቅዷል፡፡ ውይይቱ የሚካሄድበት ቀን ባይቆረጥም በቅርቡ ግን እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡

      ለአዲስ አበባ ከተማ ፈተና ከሆኑ ጉዳዮቹ መካከል አንዱ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ነው፡፡ በተለይ ላለፉት 45 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ቆሼ ዘመናዊ ባለመሆኑ፣ በሒደት መሀል ከተማ በመግባቱ ጭምር አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ መገንባት አስፈልጓል፡፡ ነገር ግን የሰንዳፋ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ የአካባቢ ነዋሪዎችን በአግባቡ ያላሳተፈ በመሆኑ፣ በቀጥታ ማኅበረሰቡ ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ሥራ እንዲያቆም አድርገዋል፡፡ የተገዙ ማሽኖችም ወድመዋል፡፡

      የከተማው አስተዳደር ይህንን የቆሻሻ ማስወገጃ ወደ ሥራ ለማስገባት ከያዘው ዕቅድ በተጨማሪ ለዕይታ የማይመቸውን የቆየውን የደረቅ ቆሻሻ ቅብብሎሽ ጣቢያ አሠራር ለመቀየር ዕቅድ አውጥቷል፡፡ እያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 85 ቦታዎች ላይ ግንባታ ለማካሄድ፣ የትኛውም ዓይነት ቆሻሻ ከሰው ዕይታ ውጪ መሆን እንዳለበት ዕቅድ መውጣቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...