‹‹ሙጋቤና ሙሴቬኒ አብቅቶላቸዋል፡፡ አስራቸዋለሁ፡፡ እስር ቤት እከረችማቸዋለሁ፡፡ የአሜሪካ አስተዳደር እነኝህን ሁለት አምባገነኖች ማስቆም ካቃተው እኔ በግሌ አደርገዋለሁ፡፡›› የአሜሪካው ከበርቴና ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት በዕጪነት የቀረቡት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ የአሜሪካ ታላላቅ ጀግኖች ቀን ሲዘከር ይህንን ተናግረዋል፡፡ በርካቶችን የሚያበሳጩና የሚያናድዱ ንግግሮችን በመሰንዘር የታወቁት ዶናልድ ትራምፕ ሁለቱን አፍሪካዊ መሪዎች ከሚበቃቸው በላይ አምባገነን ሲሉም ኮንነዋቸዋል፡፡ ከዶናልድ ንግግር በኋላ የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤም አጸፋውን መልሰዋል፡፡ ‹‹ትራምፕ የትም ሊወስደን አይችልም፡፡ አፍሪካውያን ጠንካሮችና ፍርኃት የማያውቀን ሰዎች ነን፡፡ እኔ የምፈራው ነገር የለኝም፡፡ ልክ አያቱ ሒትለር ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንደቀሰቀሰው፣ ትራምፕም ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት በመለኮስ ትሩፋቱን ትቶ ለማለፍ እየሞከረ ነው፡፡›› ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ይህንን ስለመናገራቸው የዘገበው ዚምባብዌ ደይሊ የተባለው ጋዜጣ በድረ ገጹ ባወጣው ጽሑፍ ነው፡፡