Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት አሠራሮች እንዲፈተሹ መመርያ አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት አሠራሮች እንዲፈተሹ መመርያ አስተላለፉ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከሚኒስትሮች፣ ከሚኒስትር ዴኤታዎችና ከዋና ዳይሬክተሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ አሁን ያለው የመንግሥት አሠራር እንደማያዋጣና እያንዳንዱ የሥራ ኃላፊ አሠራሩን በመፈተሽ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡

በውይይቱ ወቅት ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየስብሰባው ላይ ትችቶችን ብቻ ይዞ መምጣት እንደማይገባም፣ ግሳፄ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ሚኒስትር ሐሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጪ አይደለም፡፡ ስለዚህ በየስብሰባው በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ ኑ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካሁን ቀደም በሥራ ሰዓት በሚደረጉ ስብሰባዎች የሚባክኑ የሥራ ሰዓቶችን በሥራ ማሳለፍ እንዲቻል ስብሰባዎችን ከሥራ ሰዓታት ውጪ ለማድረግ በገቡት ቃል መሠረትም፣ በየሳምንቱ ዓርብ ጠዋት ይደረግ የነበረውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባን ወደ ቅዳሜ ጠዋት ማዛወራቸውን ለተሰብሳቢዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህም የሥራ ሰዓትን ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል፡፡

‹‹በካቢኔ ስብሰባ ስም የሚባክን የሥራ ቀን መኖር ስለሌለበት ስብሰባችን ቅዳሜ ቅዳሜ ሆኗል፤›› ሲሉ ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠንካራ ቃላት በተሞላው ንግግራቸው፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚጎድሏቸውና አሁን መንግሥት ላለበት ሁኔታ በአጣዳፊነት መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ እነርሱም ቅንነት (Integrity)፣ ልህቀት (Excellence) እና ጊዜን ለመጠቀም የሚኖር ንቃት (Time Consciousness) እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹የመጀመርያው ቅንነት (Integrity) ነው የሚጎድለን፣ የሚያስቸግረን እርሱ ስለሆነ፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰብሳቢ ባለሥልጣናት ምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

‹‹አንድ በሩጫ ውስጥ ያለ አገርና በሩጫ ውስጥ ያለ ሰው ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ሊኖሩት ይገባል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የራዕይ፣ የእሴትና የተልዕኮን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

‹‹ራዕይ አልባ ሰው ዝም ብሎ ለመኖር የሚኖር ከሆነ ብዙ ርቀት ለመሄድ ይቸገራል፡፡ የጋራ ራዕይ እንደተጠበቀ ሆኖ በግለሰብ ደረጃም ባለራዕይ መሆን አለበት፡፡ ራዕይ ማንነትን ይለካል፤›› በማለት የራዕይን ምንነት ገልጸዋል፡፡ ስለራዕይ ሲያስረዱ በየመሥሪያ ቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው ማንም ቢጠየቅ የማያስታውሳቸው፣ የማይታወቁና የማይተገበሩ ነገሮች መሆን እንደማይገባ፣ ከሦስትና ከአራት ያልዘለሉና ሁሉም ሊጠብቃቸው የሚገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ብቃት ከሌለ ወደ ተልዕኮ መሄድ አይቻልም፡፡ ራዕይ መድረሻ ነው፡፡ ተልዕኮ ሒደት ነው፡፡ እሴት ያንን የምናሳካበት ድልድይ ነው፣ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ አድጋለች ከማለት በዘለለ የሕዝቡ ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ምን እንደሚመስል በሚያሳይ ደረጃ መለካት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ካሁን በኋላ የካቢኔ አባላት ቆይታ የሚወሰነው በአፈጻጸም ላይ ተመርኩዞ እንደሚሆን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እያንዳንዱ ሚኒስትር ከሚቆጣጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ጋር የሥራ ውል በመግባት ሥራን ቆጥሮ ተረክቦ፣ ቆጥሮ የማስረከብ አሠራር ለማሥፈን ከመስከረም ወር ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የውጭ አገር ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለሥልጣናት መንግሥት መረጃው እንዳለው፣ በውጭ መንግሥታት ትብብር በአካውንታቸው ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ ሚኒስትር ከመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር የሚኖረው የሥራ ግንኙነት ቀለል ያለና በውጤት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለሥልጣናቱን ከመሰብሰቢያ አዳራሽ ይዘው በመውጣት በአፄ ምኒልክ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመናት የተለያዩ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸዋል የተባሉትን የታላቁን ቤተ መንግሥት የተለያዩ የተዘጉ ክፍሎች በማስከፈት እንዳስጎበኙዋቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...