የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመት ኤጀንሲ አደጋ በሚበዛባቸው አሥር ዋና ዋና መንገዶች፣ አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን መቆጣጠር የሚያስችል መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊያውል ነው፡፡
በፍጥነት ምክንያት ከሦስት ሰው በላይ ሕይወት የሚቀጥፉ አሥር መንገዶች በጥናት የተለዩ መሆናቸውን ኤጀንሲው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አደገኛ ተብለው የተለዩት መንገዶች ከጃክሮስ እስከ ጎሮ አደባባይ፣ ከጎሮ አደባባይ እስከ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ከጎሮ አደባባይ እስከ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን (ፊጋ)፣ ከመካኒሳ እስከ አቦ መጋጠሚያ፣ ሐኪም ማሞ ድልድይ፣ ሃና ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ዘነበወርቅ አደባባይ፣ ቀራኒዮ መንገድና ቦሌ መንገድ (አፍሪካ ጎዳና) ናቸው፡፡
ከእነዚህ አሥር መንገዶችና አካባቢዎች በተጨማሪ በኅብረተሰቡ ጥቆማ 42 መንገዶችና አካባቢዎች መለየታቸውን ኤጀንሲው በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ኤጀንሲው በተመረጡት ቦታዎች በ3.3 ሚሊዮን ብር ወጪ የአልኮል መጠን መለኪያ መሣሪያዎች ግዥ በመፈጸም ለማሠራጨት እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የፍጥነት መቀነሻ ግንባታዎች እያካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኤጀንሲው በአጠቃላይ አምስት ሺሕ የትንፋሽ መለኪያ መሣሪያዎችን፣ እንዲሁም አንዴ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የትንፋሽ መሰብሰቢያ ፕላስቲኮች ለአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የትራፊክ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች ለማሠራጨት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተካሄደ ቁጥጥር ቀደም ብሎ በገባው መሣሪያ ከተመረመሩት 10,339 አሽከርካሪዎች ውስጥ ከመጠን በላይ ጠጥተው ያሽከረከሩ 202 ሲሆኑ፣ ከመጠን ቦታች ጠጥተው ያሽከረከሩ ደግሞ 551 ናቸው ተብሏል፡፡ የአልኮል ቁጥጥር በሚደረግበት ወቅት በተለያዩ ደንብ መተላለፎች የተያዙት ደግሞ 1,154 አሽከርካሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ አደጋ እየጨመረ በመሆኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 325 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 1,441 ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት፣ እንዲሁም 746 ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተጨማሪም 18,595 የንብረት ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ግን መጠነኛ መሻሻሎች መታየታቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡