ገላጋይ ሕግ አጥቶ ለወራት ሲያወዛግብ የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ለመጨረሻ ጊዜ በተባለለት ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋር ሰመራ ይደረጋል፡፡ ክልሎች ለምርጫው ዕጩ የሚያቀርቡበት ቀነ ገደብ ከነገ በስቲያ ዓርብ ግንቦት 10 ቀን ያበቃል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ አከናውኖ፣ ምርጫውን በሚመለከት ተፈጥሮ የቆየውን ብዥታ እንዲጠራ በማድረግ፣ አዲስ የአስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ አይዘነጋም፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ለቀጣዩ አራት ዓመታት ሊያስተዳድር የሚችል ሕጋዊ አመራር ባለመመረጡ የተነሳ፣ ጉዳዩ ያሳሰበው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ለመጨረሻ ጊዜ በሰጠው ምክረ ሐሳብና ማስጠንቀቂያ ምርጫው በተባለው ቀንና ሰዓት እንደሚከናወን ተስፋ የሚያደርጉ የዘርፉ ሙያተኞች፣ ክልሎች የሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይጠይቃሉ፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ይፋ ሳያደርግ ተወዳዳሪዎችን ማንነት መናገር ተገቢ እንደማይሆን የሚናገሩት ታማኝ የፌዴሬሽን ምንጮች፣ አንዳንድ ክልሎች ቀድሞ ያቀረቧቸውን ዕጩዎች ደግመው ለመላክ መወሰናቸው ማረጋገጫ እያገኙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለዓመታት የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማስተዳደር ዕድሉን ያገኙም ሆነ አሁን ያሉ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚኖሩ ውጫዊ ተፅዕኖዎች እንደተጠበቁ፣ ባለድርሻ ነኝ የሚለው ጭምር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረትና ጥንቃቄ ማድረግ ባለመቻሉ፣ እግር ኳሱ በመልካም አስተዳደር ዕጦት እየታመሰ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በእግር ኳሱ ዕድገቱ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ እየሆነ እንደሚገኝ ጭምር ይናገራሉ፡፡
ችግሩን ለማስተካከል ቢረፍድም፣ ነገር ግን ባለመምሸቱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን እንዲያስተዳድሩ የሚላኩ ዕጩዎችን የመለየት ሙሉ ኃላፊነት ያለባቸው ክልሎች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ለየለት ውዝግብና ቀውስ እንዳይገባ ለተቋሙ ይመጥናሉ የሚሏቸውን ማቅረብ የዜግነት ግዴታቸው ስለ መሆኑም ያሳስባሉ፡፡
ዕጩዎች በተቻለ መጠን በሰብዕናቸው የተከበሩ፣ ችሎታና ብቃት ያላቸው፣ የስፖርቱ ፍቅር የሠረፀባቸውና ቁርጠኝነቱ ያላቸው፣ ከሙስናና መሰል ተግባሮች የፀዱ፣ የእግር ኳሱን የወደፊት አቅጣጫ ማመላከት የሚችሉ ሊሆኑ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡