Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

ዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

ቀን:

ኢየሩሳሌም ዓለም አቀፍ ከተማ ነች፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሁለት ሉዓላዊ አገሮች የይገባኛል ጥያቄ ስለሚያነሱባት ነው፡፡ እስራኤልና ፍልስጤም ዋና ከተማቸው እንደሆነች ዕውቅና ለማግኘት የሚፋተጉባት ጥንታዊት ከተማ ነች፡፡

እ.ኤ.አ. በ1517 ከተደረገው የኦቶማን ቱርክና የግብፅ ማምሉክ ሡልጣን ጦርነት እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ (እ.ኤ.አ. 1918) ድረስ፣ ኢየሩሳሌም በኦቶማን ቱርክ ሥር ትተዳደር ነበር፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ1917 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ ላይ ኢየሩሳሌም በፍልስጤም ባለአደራነት በእንግሊዝ ትተዳደር ነበር፡፡

በዚህም ወቅት በተለይ የክርስቲያን ሕዝቦቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚሹ የአውሮፓ አገሮች ተነሳሽነት፣ በርካታ መንግሥታት የቆንስላ መሥሪያ ቤቶቻቸውን በኢየሩሳሌም ከፈቱ፡፡

- Advertisement -

ይሁንና በዚህች ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንደ ቆዳ ወጥረው የያዟት ኢየሩሳሌም ሰላማዊ ሆና መቆየት የቻለችው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ እንግሊዝም የሰዎችን ሕይወት የነጠቁ የአይሁዶችንና የዓረቦችን ግጭቶች መቋቋም ባለመቻሏ፣ ዓለም አቀፉ አካል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጣልቃ እንዲገባ በማድረግ ፍልስጤምን የዓረብና የአይሁዶች ግዛት በማድረግ ከፈሏት፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የኢየሩሳሌም ጣጣ የጀመረው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢየሩሳሌምን ‹ልዩ አስተዳደር› በማቋቋም በሥሩ እንድትተዳደር አደረገ፡፡ ይኼንን ውሳኔ አይሁዶች ሲቀበሉት፣ ዓረቦቹ ፍልስጤማውያንና ሌሎች የዓረብ አገሮች ሕገወጥ በማለት ውድቅ አደረጉት፡፡

ዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

 

ከዓመታት በኋላ እስራኤል የኢየሩሳሌምን ባለቤትነትና ዋና የእስራኤል መዲናነት የሚደነግግ ሕግ እ.ኤ.አ. በ1948 አወጣች፡፡ እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል በመሆን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ዕውቅናን ብታገኝም፣ በኢየሩሳሌም ላይ አለኝ ለምትለው መብት ግን ማንም ዕውቅና ሊሰጣት አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አገሮቹ ኢየሩሳሌምን ለማስተዳደር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቀመጠውን ውሳኔ በመጥቀስ ዕርምጃውን አንቀበልም በማለታቸው ነው፡፡

ነገር ግን ዮርዳኖስ በወሰደችው ዌስት ባንክን የማጠቃለል ዕርምጃ፣ ምዕራብ ኢየሩሳሌምን የግዛቷ አካል እንደሆነች አወጀች፡፡ ይሁንና ይህም የዮርዳኖስ አካሄድ ከፍልስጤምና ከታላቋ ብሪታንያ ውጪ ከየትኛውም የዓለም አገሮች ዕውቅና አልተቸረውም፡፡

ከስድስቱ ቀናት ጦርነት በኋላ እስራኤል የኢየሩሳሌም ሕግ ለምዕራብ ኢየሩሳሌም እንደሚሠራ በማወጅ የግዛቷ አካል አደረገችው፡፡ ይኼንንም የተቀበለው አልነበረም፡፡

የኢየሩሳሌምን አስተዳደር በሚመለከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓላማ የፍልስጤምም ሆነ የእስራኤል ዋና ከተማ በመሆን እንድታገለግል ሲሆን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል መግባባትን ለማምጣት በርካታ ውጤት አልባ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በአብዛኛው ሲካሄዱ የነበሩ ውይይቶች ደግሞ ፍሬ ማፍራት እንዳይችሉ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ስታደርግ የነበረውን ሠፈራ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያወገዘውም ቢሆን ለማቆም ፈቃደኛ ሳትሆን በመቆየቷ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

 

ከስድስቱ ቀናት ጦርነት ማግሥት በጦርነት በያዘችው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ ዜጎቿን በተለይም አይሁዶችን የምታሰፍረው እስራኤል፣ አሜሪካን እንኳን የማያስደስት ድርጊት እያደረች ቢሆንም ግድ የሰጣት አይመስልም፡፡

ይባስ ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር እ.ኤ.አ. በ2017 በስልክ ባደረጉት ንግግር፣ አማካሪዎቻቸውን ባስደነገጠ ሁኔታ ዕውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ እስራኤል እያደረገች ያለችው ሠፈራ ፍልስጤማውያንን ያላግባብ በመተንኮስ እያበሳጨ ነው ሲሉም ትራምፕ ወቅሰው ነበር፡፡

ሆኖም ካሁን በፊት በተደጋጋሚ አሜሪካ ለእስራኤል እንደምታዳላ ሲሰነዘሩ የነበሩ ወቀሳዎችን በግልጽ ባረጋገጠ ሁኔታ ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የአሜሪካ ኤምባሲ በኢየሩሳሌም ተከፈተ፡፡ በኤምባሲው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ አማካሪና የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር ከነባለቤታቸው የተገኙ ሲሆን፣ የአሜሪካ ትሬዠሪ ኃላፊ ሰቲቨን ምኑቺንና የተለያዩ አገሮች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ይህም አጋጣሚ ከእስራኤል 70ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር መገጣጠሙ በእስራኤሎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል፡፡

ይኼንን ክስተት ጨምሮ የእስራኤልንና የፍልስጤምን ጉዳይ የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ የአሜሪካ ኤምባሲ በኢየሩሳሌም መከፈቱ ሌሎች አገሮችን ሊያበረታታ ይችላል የሚሉ አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ጓቲማላ፣ ፓራጓይና ሆንዱራስ አሜሪካን ተከትለው ኤምባሲያቸውን በኢየሩሳሌም ሊከፍቱ ይችላሉ የሚሉ ግምቶችን እየሰጡ ነው፡፡

ይሁንና በኢየሩሳሌም ኤምባሲ ተከፈተ ማለት በቀጥታ የኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲናነት ዕውቅና መስጠት አይሆንም ብለው የሚከራከሩ ወገኖችም አልጠፉም፡፡ ይህም ሊሆን የማይችልበት ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተወሰኑ ተከታታይ ውሳኔዎች መሠረት፣ ኢየሩሳሌምን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሊሰጡ የሚችሉት በፍልስጤምና በእስራኤል ስምምነት ብቻ እንደሚሆን ተደንግጓልና ነው፡፡

ምንም እንኳን የአሜሪካ ኤምባሲ በኢየሩሳሌም መከፈቱ የመጀመርያው ቢሆንም፣ ኢየሩሳሌም ግን የኤምባሲዎች መቀመጫ ለመሆን አዲስ አይደለችም፡፡ ኢየሩሳሌም የ16 ኤምባሲዎች መናኸሪያም ነበረች፡፡

ዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

 

በኢየሩሳሌም ኤምባሲያቸውን ከፍተው የነበሩና በኋላም በተለያዩ ምክንያቶች ከዘጉ አገሮች ውስጥ ሦስቱ የአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ፣ አሥራ አንዱ የላቲን አሜሪካ አገሮች ናቸው፡፡ በኢየሩሳሌም ኤምባሲ የነበራቸው የአፍሪካ አገሮች ኮትዲቯር፣ ዛየር (የአሁኗ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) እና ኬንያ ሲሆኑ፣ የላቲን አሜሪካ አገሮች ደግሞ ቦሊቪያ፣ ካምቦዲያ፣ ኮስታሪካ፣ የዶሚኒክ ሪፐብሊክ፣ ኤኳዶር፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ፓናማ፣ ኡራጓይ፣ ቬኒዙዌላና ጓቴማላ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ ሁለት በኢየሩሳሌም ኤምባሲ የነበራቸው አገሮች ኔዘርላንድስና ሄይቲ ነበሩ፡፡

ይሁንና የአፍሪካ አገሮች ከአልጄርሱ የገለልተኛ አገሮች እንቅስቃሴ (Non-Aligned Movement) ስብሰባ በኋላ ከእስራኤል ጋር በተፈጠረ ቅሬታ፣ እ.ኤ.አ. በ1973 ኤምባሲያቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተው ወጡ፡፡ የተቀሩት 13 አገሮች እስራኤል ኢየሩሳሌምን መዲናዋ በማድረግ ያፀደቀችውን ሕግ ተከትለው ኤምባሲዎቻቸውን እየዘጉ ወጡ፡፡

ይሁንና ማንኛውም አገር አምባሳደርም ሆነ ተወካይ ወደ እስራኤል ሲጓዝ ኢየሩሳሌምን ሳይረግጥና በኢየሩሳሌም የከተሙትን የእስራኤል ባለሥልጣናት ሳያገኝ አይመለስም፡፡ እያንዳንዱ አምባሳደርም በእስራኤል ሲመደብ የምደባ ወረቀቱን ኢየሩሳሌም ለሚገኙት የእስራኤል ፕሬዚዳንት በአካል ተገኝቶ ማቅረብ የግድ ይለዋል፡፡

ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የአሜሪካ ኤምባሲ በእየሩሳሌም መከፈትን በመቃወም ሠልፍ የወጡ በርካታ ሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ በእስራኤል ወታደሮች በተፈጸመ ጥቃት 52 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ2,500 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቡድንም በእስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት ለማጣራት እየሞከረ ባለበት ጊዜ፣ አሜሪካ ይኼንን እንቅስቃሴ ለመግታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ የሚናገሩ ዘገባዎች በብዛት እየወጡ ነው፡፡ ፍልስጤምም ‹ጭፍጨፋ› ብላ በፈረጀችው ጥቃት ምክንያት በእስራኤል መንግሥት ላይ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የጦር ወንጀለኝነት ክስ ልትመሠርት በዝግጅት ላይ እንዳለችም እየተነገረ ነው፡፡

ይሁንና ይህ ክስተት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ድክመትና የጋራ ደኅንነት (Collective Security) ውድቀትን የሚያሳይ፣ ምናልባትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ዓይነት የከንቱነት ዕጣ ፈንታ እንዲገጥመው ማድረግ የሚችል እንደሆነ በርካቶች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡

ጠንካራ ነኝ በሚል መኮፈስ የቆየው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ፣ ፋሺዝምና ናዚዝም ሲንሰራፉ ለአባላቱ ጥበቃ ማድረግ ሳይችል በመቅረቱ ለውድቀት ተዳርጓል፡፡ በዚህም ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ስትወርር፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ በተሰብሳቢዎች ፊት ቀርበው፣ ‹‹ዛሬ እኛ ነን፣ ነገ ደግሞ የእናንተ ዕጣ ፈንታ ይሆናል፤›› ሲሉ የተናገሩት እውነት ትንቢት ሆኖ ከአራት ዓመታት በኋላ በፋሺዝምና በናዚዝም ምክንያት በመጣ ሰበብ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይን ጨምሮ ሁሉም የአውሮፓ አገሮች ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገቡ፡፡

አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤልንና የፍልስጤምን ጉዳይ በብልኃት ካልፈታ፣ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጥርስ አልባ አንበሳ ሆኖ የመፍረስ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው እንደሚችል ካሁኑ እየተነገረ ነው፡፡

በማግሥቱ የተጀመረውን የዓረብ ሊግ ስብሰባ የከፈቱት የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ሳልማን በበኩላቸው አሜሪካን በድርጊቷ የኮነኑ ሲሆን፣ በምዕራብ ኢየሩሳሌም ለወደሙና ለተጎዱ እስላማዊ ቅርሶች መጠገኛ እንዲሆን የ150 ሚሊዮን ዶላር በመንግሥታቸው በልግስና መዘጋጀቱንም አሳውቀዋል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የጋራ ደኅንነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም መዛወር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...