“ሚኒስትር ሐሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጪ አይደለም!”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በጽሕፈት ቤታቸው ለመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በሥራዎቻቸውና በአሠራራቸው ዙሪያ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ገለጻና ማሳሰቢያ በሰጡበት አጋጣሚ የተናገሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ከእንግዲህ እያንዳንዱ ሚኒስትር ለካቢኔ ስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዓቢይ ከስብሰባው በኋላ ሹማምንቱን ከአዳራሽ ይዘው በመውጣት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴና በዘመነ ደርግ የተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸው በታላቁ ቤተ መንግሥት የሚገኙና ዝግ የነበሩ የተለያዩ ክፍሎችን አስከፍተው እንዲጎበኟቸው ማድረጋቸውን፣ በዚህም አጋጣሚ የነገሥታቱን የግብር ቤቶች፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ የተገደሉበትንና የደርግ ጄኔራሎች የተረሸኑባቸውን ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት መገበኘታቸው ታውቋል፡፡