Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ፈልጎ ያልመጣ ሕፃን በየመንገድ ወድቆ መጎዳት የለበትም››

ወ/ሮ ማርታ ወልደአረጋይ፣ የፍቅር ለሕፃናትና እናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች

ወ/ሮ ማርታ ወልደአረጋይ የፍቅር ለሕፃናትና እናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ናቸው፡፡ በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው የፍቅር ለሕፃናትና እናቶች ድርጅት በችግር ምክንያት ጎዳና ላይ የወጡ እናቶችን መደገፍና መልሰው እንዲቋቋሙ መንገዶችን ያመቻቻል፡፡ ወ/ሮ ማርታ በዚህ ተግባር ከመሰማራታቸው አስቀድሞ በአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ባለቤታቸውም በአንድ የመንግሥት ድርጅት ተቀጣሪ ናቸው፡፡ የሁለቱም የወር ገቢ ከቤተሰባቸው የሚያልፍ ባይሆንም የማንንም ድጋፍ ሳይሹ ነበር ድርጅቱን አቋቁመው የጎዳና ላይ ሕፃናትንና እናቶችን መርዳት የጀመሩት፡፡ እንደ አብዛኞቹ የበጎ አድራጎት ተቋማት ምክረ ሐሳብ አዘጋጅተው በየመሥሪያ ቤቱ ዞረው የመንግሥት ድጋፍ አልጠየቁም፡፡ በየቤቱ ዞረውም ያላችሁን አዋጡ ብለው አላስቸገሩም፡፡ ያላቸውን ሸጠው እነዚህን ኑሮ ገፍቶ ጎዳና ያወጣቸውን ዜጎች መርዳት ከጀመሩ ሦስት ዓመት ደፍነዋል፡፡ ድጋፍ አጣን ብለው ተስፋ ሳይቆርጡ እስካሁንም ቆይተዋል፡፡ የቅበላ አቅማቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ የአመሠራረት ሒደትና አሠራር በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን የድርጅቱን መሥራች ወ/ሮ ማርታ ወልደአረጋይን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር ድርጅቱን ለመመሥረት ምን አነሳሳዎ?

ወ/ሮ ማርታ፡– ሁላችንም እንደምናውቀው ብዙ ሰዎች በችግር ምክንያት ጎዳና ላይ ይወጣሉ፡፡ በየመንገዱ ሕፃናት ልጆችን ይዘው ፀሐይ እየመታቸው የሚቀመጡ እናቶችን ስመለከት በጣም አዝናለሁ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ጊዜያዊ ዕርዳታ ማድረግ ምንም እንደማይፈይድ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም ባለኝ አቅም የተወሰኑ ሰዎችን ሕይወት ለመቀየር ቆርጬ ተነሳሁ፡፡ በምን መንገድ ልደግፋቸው እንደምችል ለማወቅም በአካባቢዬ የማያቸውን ችግረኛ እናቶች እየተዘዋወርኩ እጠይቅም ነበር፡፡ እናቶቹ መሥራት እየቻሉ ነገር ግን ልጆቻቸውን የሚያሳድሩበት ቦታ ስለሌላቸው እንደሚለምኑ አወኩ፡፡ አብዛኞቹ ባል የገፋቸው፣ ጓደኛ የከዳቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም ባለኝ አቅም የተወሰኑ ሰዎችን መርዳት ጀመርኩ፡፡ እኔና ባለቤቴ የነበረንን መሬት ሸጠን በመጀመሪያ አሥር እናቶችንና አሥር ሕፃናቶችን መርዳት ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡– ድርጅቱን ለማቋቋም እንደ መነሻ የሆናችሁ ቦታ ሸጣችሁ ያገኛችሁት ገንዘብ ምን ያህል ነበር? ላሰባቹት ስራስ በቂ ነበረ ወይ?

ወ/ሮ ማርታ፡– የራሳችንን ቤት ስላለን የነበረንን ትርፍ ቦታ ነው የሸጥነው፡፡ ሰሚት አካባቢ የሚገኝ 72 ካሬ ነው፡፡ በቦታው ላይ ቤት ለመገንባት መሠረት አውጥተንለትም ነበር፡፡ 700 ሺሕ ብር ነበር የሸጥነው፡፡ ከዚያ ላይ ወደ 220 ሺሕ ብሩን ለዚሁ ድርጅት አዋል ነው፡፡ ዋናው ባለን ነገር መጀመሩና ለጋስ መሆኑ ላይ ነው፡፡ እናቶች ሥራ የማይሠሩት ልጆች ስለያዙ ነው፡፡ የሚያስቀምጡበት ቦታም የላቸውም፡፡ ስለዚህ እዚህ እዚያ ብለው መስራት እንዲችሉ ልጆቻቸው በዴይኬር እንዲቆዩ በማድረግ ነው የምናግዛቸው፡፡ ሥራ ሠርተው እንዲቀየሩም ጥቂት ገንዘብና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ገዝተን እንሰጣቸዋለን፡፡ በመጀመሪያ 18 እናቶችን ነበር የተቀበልነው፡፡ ነገር ግን ስምንቱ የጎዳና ሕይወት መርጠው ወደ ጎዳና ተመለሱ፡፡ የተቀሩት አሥሮቹ ሥራ እንዲሠሩ ሙያ እንዲማሩ አደረግን፡፡ ልጆቹ በኛ ደይኬር ውስጥ ሲኖሩ ምግብ፣ ልብስም ሕክምናም እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ከራሳችን የሚተርፍ ገንዘብ የለንም ሌላ ገንዘብ ያስፈልገንም ለዚሁ ነው፡፡ የባለቤቴና የኔ የወር ገቢ ከአሥር ሺሕ አይበልጥም፡፡

ሪፖርተር፡– በደይኬራችሁ ምን ያህል ሕፃናት ይዛችኋል?

ወ/ሮ ማርታ፡– በአሁኑ ወቅት 40 ሕፃናት 35 እናቶች አሉን፡፡ ዘመዶቻችንና አንዳንድ ድርጅቶች መጠነኛ ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ ውጭ የሚገኙ ዘመዶቻችን ጓደኞቻችን ገንዘብ እያዋጡ ይልኩልናል፡፡ ከጎዳና ላይ ያነሳናቸው እናቶች ሥልጠና ወስደው እዚያው እንዲያገለግሉ እናደርጋለን፡፡ ምግብ ያበስላሉ፣ ሞግዚት ናቸው፣ ጽዳትም ይሠራሉ ለዚህም መጠነኛ ክፍያ ይታሰብላቸዋል፡፡

ሪፖርተርበድርጅቱ ሥር የሚገኙ እናቶች ምን ምን ዓይነት የኋላ ታሪክ ያላቸው ናቸው?

ወ/ሮ ማርታ፡– በጣም የሚገርም ታሪክ ያላቸው አሉ፡፡ በጎዳና ሕይወት ሳሉ ተደፍረው የወለዱ አሉ፡፡ የተደበደቡም አሉ፡፡ ከዓረብ አገር ተመላሽ የሆኑ ዜጎችም አሉ፡፡ የአንዷን ታሪክ በምሳሌነት ባነሳ፤ ዓረብ አገር ሄዳ ምን እንዳረጓት አታውቅም ወደዚህ ልከዋት ዝም ብላ መጥታለች፡፡ እሷ ራሷን አታውቅም ከዚያም አንዱ መንገድ ላይ ያገኛትና አንስቶ ይወስዳታል፡፡ ሰውየው ይደፍራትና ታረግዛለች፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ ማርገዟን ሲያውቅ አውጥቶ ይጥላታል፡፡ ከዚያም ራሷን ማወቅ ትጀምራለች፡፡ ዘመዶቿን አፈላልጋ አግኝታም እነሱ ጋር ሄደች፡፡ ነገር ግን የአራት ወር እርጉዝ ነበረች እነሱም ደስተኛ አልነበሩም ስለዚህ ከቤት አስወጧት፡፡ ከእነሱ ጋር ወጥታ ሰው ቤት ተቀጥራ እየሠራች ሳለ እርግዝናዋ እየገፋ መሥራት አስቸገራት፡፡ የልጇን አባት እንኳ አታውቅም ለመኖር በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ገባች፡፡ ጎዳና ላይ ወድቃ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ አንድ ሰውዬ አስጠግተዋት መደሪያ አገኘች፡፡ ሕፃን ልጅ ጋር ተሯሩጦ ለመሥራት በጣም ከብዷት ሳለ ነበር እኛ ያገኘናት፡፡ በአሁኑ ወቅት የጀበና ቡና እያፈላች ትሸጣለች፡፡ ቅቤም ከክልል ከተሞች እያስመጣች ትሸጣለች፡፡ ልጇም እያደገችላት ነው፡፡ ሌሎችም እንዲህ ያሉ ብዙ አሉ፡፡

ሪፖርተርየተጠናከረ ገቢ ሳይኖራቹ ስትንቀሳቀሱ የተለያዩ ችግሮች በሥራቹ እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡ ዋና ዋና ችግሮቻችሁ ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ማርታ፡– አንደኛው ችግራችን ቦታ ነው፡፡ የምንሠራው ተከራይተን ነው፡፡ ኪራዩ ለኛ በጣም ውድ ነው፡፡ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት የ20 ሕፃናትን ሕክምና ይዘውልናል፡፡ ሕፃናቱ በነፃ እንዲታከሙ ዕድል ፈጥሮልናል፡፡ ሌሎቹን ግን በጤና ጣቢያና በመንግሥት ሆስፒታሎች እናሳክማለን፡፡ የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ልዩ ትኩረት የሚሹ እናቶች ነበሩ፡፡ መድሐኒትና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡– ሕፃናቱ ስንት ዓመት እስኪሞላቸው ነው ከእናንተ ጋር እንዲቆዩ የሚደረገው?

ወ/ሮ ማርታ፡– ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ያሉ ሕፃናትን እንቀበላለን፡፡ ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን የእናት ጡት መጥባት ስላለባቸው ያስቸግሩናል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ብዙም አያስፈልጋቸውም ምግብ ተመግበው መዋል ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሕፃናት ተቀብለን እኛ ጋር ስናቆይላቸው እናቶች እንደልብ ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ አንድ ሕፃን አራት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከኛ ጋር ይቆያል እናቱም እንደዚሁ ከእኛ ጋር ትቆያለች፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን እናትየው ራሷን እንድትችል፣ ገንዘብ እንድትቆጥብ እናደርጋለን፡፡ የቤት ኪራይ፣ የልብስ የምግብ ወጪ የለባትም ሠርታ የምታገኘውን መቆጠብ ግዴታዋ ነው፡፡ እስካሁን 12 እናቶች እኛ ጋር ተረድተው ራሳቸውን ችለው ወተዋል፡፡ በቅርቡ የመጣች አንዲት እናት 35 ሺሕ ብር መቆጠብ ችላለች፡፡ ሁሌ ጥገኛ እንዲሆኑ አንፈልግም፡፡ የእኛ ሥራ እናቶችን መደገፍና ማቆም ነው፡፡ እንዳይሠሩ፣ ጥገኛ እንዲሆኑ ምክንያት የነበሩ ልጆቹ ነበሩ እኛ ልጆቹን እንይዛለን፡፡ ተሯሩጣ ሠርታ ወደኛ ትመጣለች፡፡ ሠርታ ያገኘችውን ትቆጥባለች፡፡ ልጆቹ አራት ዓመት ሲሞላቸው የመንግሥት መዋዕለ ሕፃናት መግባት ይችላሉ፡፡ ትምህርት ሲጀምሩ ማንኛውንም የትምህርት ግብዓት አሟልተን የምንልካቸው እኛ ነን፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እናትየው እራሷ ነው የምትችላቸው፡፡

ሪፖርተር፡– በምን ዓይነት የሥራ መስኮች እንዲሠማሩ ይደረጋል? ከማስቀጠር አንፃርስ የሚያጋጥማችሁ ችግር ምንድነው?

ወ/ሮ ማርታ፡– እኛ የበለጠ ትኩረት አድርገን የምንሠራው ራሳቸውን የሚችሉበትን የግል ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ በረንዳ ላይ ቡና አፍልቶ የመሸጥ፣ በፌርሙዝ እያዞሩ የመሸጥ፣ የጉልት ንግድ፣ የመኪና እጥበት ይሠራሉ፡፡ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እናደርጋለን፡፡ በተለይም ከሰው ጋር እንዴት ተግባብቶ መሠራት እንዲችሉ እናግዛቸለን፡፡ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ በምናደርገው ጥረት የምንሰጣቸውን መነሻ ገንዘብ አተን እንቸገራለን፡፡ የመኪና እጥበት ሥራ ያስጀመርነውም መነሻ ገንዘብ ሳያስፈልገው የሚሠራ ነገር ስናፈላልግ ነው፡፡ እኔ የምኖረው በጋራ መኖሪያ ቤት ነበርና ግቢ ውስጥ ያሉ መኪናዎችን ለማጠብ ኮሚቴዎችን አነጋገርኩና በስተመጨረሻ ፈቃድ አገኘን፡፡ ከዚያም መኪናዎን እንጠብልዎ የሚል ጽሑፍ በየመንገዱ ሳንቲም እየሰበሰቡ ዜጋን ጥገኛ ከማድረግ ማሠራት እንደሚሻል መልዕክት ያለው ጽሑፍ አካተን በየቤቱ በተንን፡፡ ወደ 30 መኪኖች በቋሚነት አገኘን፡፡ ሌሎች ተባራሪ የእጥበት ሥራዎችም ብዙ አሉ፡፡ አንድ ተባራሪ የሆነ መኪና በ35 ብር ሒሳብ ያጥባሉ፡፡ በኮንትራት የሚታጠብ ከሆነ በአሥር ብር ሒሳብ፣ በየሳምንቱ የሚታጠቡ መኪኖችን ደግሞ በ25 ብር ሒሳብ ታሪፍ አውጥተን እንሠራለን፡፡ ገንዘብ ያዥ፣ ጸሐፊ መርጠን ያገኙትን ገንዘብ ባንክ ወስደው እንዲያስቀምጡ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡– ወደፊት ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?

ወ/ሮ ማርታ፡– በአንድ ጊዜ መድረስ የምንችለው ሰዎች ቁጥር ብዙ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ፈልጎ ያልመጣ ሕፃን በየመንገድ ወድቆ መጎዳት የለበትም፡፡ የሚገርምሽ ነገር ሕፃናት ወደኛ ከመምጣታቸው በፊት አዋራ፣ ጸሐይና ብርዱ የተፈራረቀበት ቆዳቸው እንደመበለዝ ይላል፡፡ የእነዚህን ሕፃናት በተመቸ ሁኔታ የማደግ መብት ማስከበር እንፈልጋለን፡፡ ጠንካራና ጤናማ አገር መረከብ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ እናቶችንም እንደዚሁ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የተላቀቁ የራሳቸው ገቢ ያላቸው ባል ቢከዳቸው ባይከዳቸው ሳይቸገር መኖር የሚችሉ እንዲሆኑ እናግዛቸዋለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎችን በአቅም ማነስ ሳንወሰን በብዛት ተቀብለን ልንደግፋቸው፣ የማህበረሰቡ ሸክም ከመሆን ልናወጣቸው እንፈልጋለን፡፡ መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልን ቦታ ብናገኝ የማገገሚያ ጣቢያ የመክፈት ፍላጎት አለን፡፡ በዚያ የማገገሚያ ጣቢያ እናቶች ለሕይወት ያላቸው አመለካከት እንዲስተካከል ማድረግ የሚችል የሥነ ልቦና ለውጥ እንዲያመጡ የመሥራት ሐሳብ አለን፡፡ ንፁህ ሆነው፣ ንፁህ ለብሰው ጥሩ በልተው፣ ጥሩ መኝታ ላይ ተኝተው መንፈሳቸው አንዲታደስ እንፈልጋለን፡፡ ያሉበት የኑሮ ውጣ ውረድ በጣም ከባድ ስለሆነ ከሰው ጋር ተግባብቶ መኖር ያስቸግራቸዋል ቁጡ ናቸው፡፡ ይማረራሉ፡፡ በዙ ነገር ለማድረግም ይወስናሉ፡፡ ስለዚህም የሳይኮ ሶሻል ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ከዚያም ተፈላጊ በሆኑ የሥራ መስኮች የክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ የሙያ ችሎታ ካላቸው ጥሩ ባህሪ ካመጡ ማንም ይፈልጋቸዋል፡፡ ከመሬት ነው የምናነሳው፣ አገር ነው የምንገነባው፣ ራዕይ ያለው ሰው ነው የምናወጣው፤ ለዚህም የሚመለከተው አካል ሊደግፈን ይገባል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...