Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርማሳሰቢያ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ማሳሰቢያ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ቀን:

 

በኃይሉ ዘውገ ቦጂያ (ሲኒየር ኮንሰልታንት)

በቅድሚያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየምዎ የተሰማኝን ጥልቅ ደስታ ልገልጽልዎት እወዳለሁ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን፡፡ ለሁሉም የአገራችን ሕዝቦች የዕድገት፣ እንዲሁም የመልካም ለውጥ ዘመን እንዲሆን ያለኝን ምኞቴን በተጨማሪ እገልጸላሁ፡፡

በመቀጠልም በተሰየሙበት ቀን ባቀረቡት ድንቅ የሆነው ንግግርዎ በአገሪቱ የሚያስፈልገውን የኢትዮጵያዊነት ዕድገትና የአንድነት ስሜት በመቀስቀስዎ ላመሰግንዎት እወዳለሁ፡፡ ካነሱዋቸው ጉዳዮች መካከል ትኩረቴን ከሳቡኝ አንዱ የወጣቶች ሥራ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚሁ መልካም ተግባር ሊጠቅም ይችላል ብዬ በጥልቅ የማምንበትን ሐሳቤን በአጭሩ እንዳቀርብ ፈቃድዎን እጠይቃለሁ፡፡

በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአገራችን መላው ሕዝብ እናቶች፣ ሕናት፣ ወጣት፣ ሽማግሌውና ጎልማሳው ሁሉ በልተው ጠግበው ሲደሰቱ ይታየኛል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ትናንሽ ዱንቡሽቡሽ ያለ መልክ ያላቸው የአገራችን መላው ሕፃናት ወተት በኮዳቸው፣ ሳንድዊች በቦርሳቸው፣ ቺዝበርገር በእጃቸው ይዘው እየገመጡ ወደ ትምህርት ቤታቸው በደስታ ሲሯሯጡ ይታየኛል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የወፋፈሩ ወጣት ሴቶችና ወጣት ወንዶች ክብደት መጨመር የሚያሳስበን ሆኖ፣ እንደ አገራዊ ችግር ስንወያይበት ይታየኛል፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ በማለዳ ወደ ሥራቸው የሚተጉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣት ወንድና ሴት ሠራተኞች በመንገድላይ የምግብ መሸጫ የተዘጋጁ በፍጥነት የሚደርሱ ከእንቁላል፣ ከሥጋ፣ ከወተት የሚሠሩ ምግቦችን በቦታው ሲበሉ ለምሳቸው ጠቅልለው በደስታ ወደ ሥራ ሲጓዙ ይታየኛል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በየዕለቱ መጨመሩ ቀርቶ ሲስተካከል ይታየኛል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የወተት ዋጋ መውረድ አሳሳቢ ሆኖብን ለማስታረቅ ስንተጋ ይታየኛል፡፡

በጥቂት ዓመታት ውስጥ በገጠርና በከተማው አካባቢ ዘመናዊ መካከለኛ ፋብሪካዎች የከብቶች፣ የዓሳ፣ የበግ፣ የፍየል፣ የዶሮ ዕርባታ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም የወተትና የወተት ምርቶች ማምረቻዎች በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ የአገሪቱ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለዕድገት አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ይታየኛል፡፡ እነዚህም ምርቶች በገጠርና በከተማ አከፋፋይ፣ ቸርቻሪ ነጋዴዎች፣ ግብት አቅራቢ ድርጅቶች፣…. ተመልምለው ለመላው አገሪቱና ለዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡ በማቅረብ የሀብት ተካፋይ ሲሆኑ ይታየኛል፡፡

ይህ የኢኮኖሚ ሰንሰለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ባለው የኢኮኖሚ አቅም በመሸፈን በኑሮዋቸው ተደስተው፣ መላውን የአትዮጵያን ሕዝብ ለማስደሰት ሲተጉ ይታየኛል፡፡

ይህ ሁሉ ተዓምር ከየት ይመጣል?

ይህ የሚመጣው የአገራችን አርሶ አደር ወገናችን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ዕገዛ ሳይደረግለት በራሱ ልምድ ብቻ፣ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ካደረገበት የእንስሳት ዕርባታ የኢኮኖሚ ዘርፋችን ነው፡፡

ይህ ዘርፍ የሚገባውን ትኩረትና የመንግሥት ዕገዛ ቢያገኝም ተገቢው የስትራቴጂ ለውጥ አልተደረገለትም፡፡ በተለይም ካለው አቅም አንፃር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ የመፍጠር፣ እንዲሁም ለዜጎች የምግብ ዋስትናና የውጭ ምንዛሪ የማምጣት ኃይሉን በሚጠቅም ሁኔታ አላገኘም፡፡ ሆኖም ይህ መስክ በቀላሉ የሚከተሉትን ጥቅሞች በእርግጠኝነት ሊያስገኝልን የሚችል ነበር፡፡

 • የአገሪቱን ዘመናዊ ኢንዲስትሪ በፍጥነት ያሳድጋል፣
 • የባህላዊውን የከብት አረባብና አያያዝ በዘመናዊ ሁኔታ እንዲተካ ያስችለናል፣
 • የምግብ ዋስትና እንድናጎለብት ይረዳናል፣
 • አልሚ ምግብ ለዜጎች ለማቅረብ ያስችለናል፣
 • ሕፃናት ወጣቶች በተገቢውም መንገድ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያስችላል፣
 • ሥራ አጥነትን በከፍተኛ ደረጃ እንድንቀንስ ይረዳናል፣
 • ለአገራችን የጀርባ አጥንት ይሆናል፣
 • በኑሮው ገቢ ጨምሮ የተደሰተ ሕዝብ ያስገኛል፣
 • ለአገሪቱ የተረጋጋ ሰላም ይፈጥራል፣
 • የተጠናከረና የተሻሻለ የአካባቢ ይዞታ ለመፍጠር ያስችላል፣
 • በኢኮኖሚ ዘርፎች ተመጋቢነት ያለው ሁኔታ ፈጥሮ የአገሪቱን ዕድገት ያፋጥናል፣

የእንስሳት ዕርባታ የኢኮኖሚ ዘርፋችን የአገራችን ዓብይ ጉልበት ከፍተኛ (Comparative Advantage) ባለንበት መስክ ሲሆን፣ ከሌለው አስበልጠን ለመሥራት ባህሉና ልምዱን ያካተትንበት ነው፡፡ ስለዚህም ለዚህ ቅድሚያ ልንሰጥ የሚገባበት ደጋፊ ጉልበቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ለእንስሳት ፍቅር ያለው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ባህሉና ድንቅ ክህሎቶች ያላቸው ሕዝቦች አሉ፡፡
 2. ለመኖ ማምረቻ ግብዓት በሰፊው ለማስገኘት የሚያስችል ሰፊ አመቺ መሬት በአገሪቱ ሁሉም ክፍል ይገኛል፡፡
 3. ለሚሊዮን ከብቶችና እንስሳት መገኘት ምክንያት የሆነ የውኃ መጠን አሁንም ያለን በመሆኑና የወደፊት ውኃን የማልማት ዕቅዳችን ደጋፊ ሆኖ ይገኛል፡፡
 4. ለከብቶች ማድለብ ጠቃሚ የሆነው ሞላሰስ በብዛት በአገሪቱ መገኘቱ ወደፊትም የመገኘቱ ተስፋ አለ፡፡
 5. መኖ ለማምረት ሠልጥነው ለሥራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች በየሥፍራው አሉ፡፡
 6. ለእንስሳት ተዋፅዖ ሊፈጠር የሚችል የተትረፈረፈ ገበያ አለ፡፡
 7. ለእንስሳት ተዋፅዖ ሊፈጥር የሚችል የውጭ ገበያ በጎረቤት አገሮች በዓረብ አገሮች፣ በአውሮፓም ይገኛል፡፡
 8. ከተፈጥሮ በሚመረት መኖ የመጠቀሙ ተግባር የዜጎችን የሥራ ባህል አሸጋጋሪ ይሆናል፡፡
 9. ወደፊት የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሎች ታዳሽ የኃይል አቅርቦቶች ጋር ተዛምዶ ከፍተኛ እሴት ሊፈጠርበት የሚቻልበት መስክ ነው፡፡

ይኼንን ሁሉ በተወሰነ መንገድ ጥቅም በመስጠት ላይ የሚገኘውን በማዘመን ከላይ የጠቀስነውን አብነት ለመቀየስ ከየት እንጀምር?

ሀ. ይህ ዘርፍ በአገሪቱ ሁሉ ትኩረት እንዲያገኝ ‹‹የእንስሳትና ዓሳ ዘርፍ የማዘመን የለውጥ እንቅስቃሴ›› ላይ በቂ ግንዛቤ በሁሉም አካባቢ እንዲኖር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመር፡፡

ለ. ይኼንን ዘርፍ የሚመለከት በአዲስ ቅኝት ስትራቴጂካዊ ፕላን እንዲዘጋጅ በአስቸኳይ ማስደረግ፡፡

ሐ. የሚዘጋጀው ስትራቴጂካዊ ፕላን የባለድርሻ ፍላጎት ባካተተ ሁኔታ ሆኖ ከአገሪቱ የአሁኑ የዕድገት ፍላጎት አንፃር መታየት አለበት፡፡

መ. የሚዘጋጀውን ስትራቴጂካዊ ፕላን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ለሁሉም የእንስሳት ዓይነት መኖ የሚያቀነባብሩ በመንግሥትና በባለሀብቶች የጋራ ትብብር የሚመሠረቱ ታላላቅ ፋብሪካዎችን ማቋቋም ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ የእነዚህ ፋብሪካዎች በመንግሥትና በባለሀብቶች የጋራ ትብብር እንዲሆን ሐሳብ የቀረበበት ምክንያት የዚህ ዓይነቱ ምርት ስትራቴጂካዊ የመሆን ጠባይ ስላለው፣ በገበያ ላይ ዋጋው እንዳይንጠለጠል ለመቆጣጠር ይረዳል (ከዚህ በፊት ግለሰቦች መስክ ላይ የፈጠሩትን ችግር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተጠቀሰ)፡፡

ሰ. ይኼንን መኖ ተጠቅሞ ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉ ክፍሎችን ሁሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ መካከለኛ ፋብሪካዎች፣ አነስተኛ ፋብሪካዎች፣ ጥቃቅን አምራቾች፣ እንዲሁም በትርፍ ጊዜያቸው ከብቶችንና ዶሮዎችን የሚንከባከቡ ዜጎችን አቅም፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ የገበያ፣ ትስስር ሊያሳድጉ የሚችሉ የቀጥታ ትምህርቶችን፣ ኮርሶችን፣ ሥልጠናዎችን፣ እንዲሁም ሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች  በመቋቋም መርዳት ከመንግሥትና ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል፡፡

ሸ. በዚህ መስክ የተሰማሩትን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያጎለብቱ መርዳት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ቀ. ይህ ዘርፍ የተፋጠነ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስቻይና አጠናካሪ የሆኑ የሕግ ድጋፎችን የሚያስገኙ ሕጎችና ደንቦች እንዲቀረፁ ማስደረግ፡፡ ለምሳሌ የቀረጥ፣ የውጭ ንግድ ድጋፍ፣ ወዘተ….

ይሀ የአገራችን ዓብይ የሆነ ዘርፍ የሚያድግ ከሆነ፣ በትንሹ በግምት የሚከተለውን ያህል ቁጥር የሰው ኃይል ሊቀጠርበት ይችላል፡፡ (በመላው የአገራችንን ክፍሎችን በማካተት የተቀመረ)

ተራ ቁጥር

የምርት ዓይነት

የሰው ኃይል መጠን

1

የዶሮ መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

 25,000

2

የከብት መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

 90‚000

3

የወተት መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

 75‚000

4

የሚደልቡ ከብቶች መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

 50‚000

5

የበጎች መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

  25‚000

6

የፍየሎች መኖ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሚሠሩ

  25‚000

7

የዶሮ ንግድ የሚያከናውኑ

  5‚000

8

የከብቶች ንግድ የሚያከናውኑ

  5‚000

9

የበግና የፍየል ንግድ የሚያከናውኑ

  1‚5000

10

የግመል ንግድ የሚያከናውኑ

   1‚000

11

በከብት ዕርድ የሚሠማሩ

  2‚500

12

በበግና በፍየል ዕርድ የሚሠማሩ

  5‚000

13

የወተት ተዋፅዖ አገልግሎት አቅራቢዎች

 75‚000

14

የሥጋ ተዋፅዖ አገልግሎት አቅራቢዎች

 100‚000

15

የተሻሻለ ፈጣን ምግብ አቅራቢዎች

 100‚000

16

ዓሳ ምርት አቅራቢዎች

2‚500

 

ጠቅላላ ድምር

601,000        

 

ለዘለዓለም አይቻልም ተብሎ ሲታሰብ የነበረውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ገንብተን የማይቻለውን መቻላችንን አስመስክረናል! ይህንንም መሥራት እንችላለን! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!  

ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው የፎከስ ቢዝነስ ኮንሰልቲንግ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የጀርመን ተመላሾች ማኅበር የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አሶሼት አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...