Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየ “መብቴ ነው!” የመጀመርያ ምዕራፍ

የ “መብቴ ነው!” የመጀመርያ ምዕራፍ

ቀን:

አንቀጽ 29

በሪያድ አብዱል ወኪል

‹‹አንዲት አገር ጋዜጣ አልባ መንግሥት ይኑራት ወይስ ጋዜጦች ኖረው መንግሥት አልባ ትሁን የሚለውን ጉዳይ የመወሰን ምርጫው ለእኔ የተተወ ቢሆን፣ ሁለተኛውን ስመርጥ ለቅጽበት እንኳ ባላመነታሁ ነበር፡፡›› ከአሜሪካን መሥራች አባቶችና ፕሬዚዳንቶች አንዱ የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን፡፡

ኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር በ1990ዎቹ የመጀመርያ ዓመታት ላይ አቶ መለስ ዜናዊ በውጭ አገር በሰጡት አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ስላሉት የግል ኅትመት ዘርፎች ወቅታዊ ይዞታ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ችግሮቻቸው›› ያሏቸውን ነጥቦች ነቃቅሰው ‹‹እነሱ ግማሽ መንገድ ከመጡ እኛ ግማሹን መንገድ ሄደን ልንቀበላቸው ዝግጁ ነን፤›› ብለው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ግማሹን መንገድ ሄዶ ባይቀበላቸውም በጋዜጠኞቹ ብርታት በቁጥር ብዛትም ሆነ በይዘት ጥራት የሚመሠገኑ ኅትመቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሐሳብና ንግግር ነፃነትን ከማወጁ ቀደም ብሎ በነበረው አገራዊ የሽግግር ወቅት ‹‹መሠረታዊ መመርያና መርሆ›› በመሆን ባገለገለውና የአሁኑን ሕገ መንግሥት መሠረት በጣለው፣ እንዲሁም ‹‹እጅግ ዴሞክራሲያዊ ሰነድ ነበር›› ተብሎ በብዙዎች በሚወደሰው ‹‹የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር›› የመጀመርያው ክፍል የመጀመርያ አንቀጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲህ በዝርዝር ደንግጎ ነበር፡፡

‹‹በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 1948 ዓ.ም. የፀደቀውንና የታወጀውን ቁጥር 217 A (111) ውሳኔ መሠረት በማድረግ፣ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ያለ አንዳች ገደብ ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል፡፡ በተለይም እያንዳንዱ ግለሰብ፡-

ሀ- የዕምነት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በሰላም የመሰብሰብና የመቃወም ነፃነት   አለው፡፡

ለ- የሌሎችን ሕጋዊ መብቶች እስካልተጋፋ ድረስ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ አንዳች ገደብ የመሳተፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማደራጀት መብት አለው፡፡››

በሽግግር ወቅት ቻርተሩና (የፕሬስ ሕግጋቱ ይቆዩንና) በድኅረ 83 የቅድመ ኅትመት ምርመራ (Censorship) በሕግ ቀሪ መደረግን ተከትሎ ‹‹እንደ አሸን›› ፈልተው የነበሩት እንኳንስና ርዕሰ አንቀጻቸው ስመ መጠሪያቸው ያስፈሩ የነበሩት ኅትመቶች ከመንግሥታዊው እንከናቸውን ያለመታገስ ኩርኩም ባሻገር ራሳቸውን ጠልፈው ባይጥሉ ኖሮ፣ ዛሬ እንዲህ በሁለትና በሦስት ጋዜጦችና መጽሔቶች ብቻ ተገድበን ባልቀረን ነበር ብዬ በፅኑ አምናለሁ፡፡ ይህም ቢሆን የሚገኘው በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች ብቻ ሊያውም መቶ ሺሕ እንኳ በማይሞላ ኮፒ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የኢትዮጵያ ኅትመቶች የኅትመት ነፃነቱ በተፈለገውና ማደግ በነበረበት ልክ እንዳያድግ የራሳቸው አሉታዊ አበርክቶ ነበራቸው ለማለት ያህል ነው፡፡ አስባችሁታል ግን እዚሁ አገራችን ላይ ‹‹የመንግሥት›› ተብለው የሚገለጹትን ከቁጥር ሳናስገባ በአንድ ወቅት ከአራት መቶ ያላነሱ የጋዜጣና መጽሔት ኅትመቶች ነበሩ፡፡ የእኔ ትውልድ ግን ይኼንን መታደል አላጣጣመውምና እነሆ ከልጅነት እስከ ዕውቀቱ ሦስትና አራት ጋዜጦችን ብቻ እያነበበ አለ፣ እሱንም አንባቢ ከሆነ ነው ታዲያ፡፡

ይኼንን የምጽፈው መዋቀሱን ፍለጋ ሳይሆን በኢትዮጵያችን ከሚከበሩ ‹‹ዓለም አቀፍ መታሰቢያ ቀናት›› አንዱ በሆነውና በሰሞነኛው ‹‹የዓለም የፕሬስ ቀን›› መነሾነት፣ ምን ያህል ከዓለም ወደ ኋላ እንደቀረንና ምን ዓይነት ድንዛዜ ውስጥ እንዳለን ላልተገለጸልን ገላልጦ ለማሳየት በሚል እሳቤ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚም ስለዚህ መብት ለታገሉና በእጅጉ ለተንገላቱ ብሎም ራሳቸውን ሰውተው የጀግና ሞት ለሞቱ የትናንትናና የዛሬ ትንታግ ብዕረኞች እኛም ስለእናንተ ውዳሴያችን ብዙ ነው ለማለትም ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የጋዜጠኛውና የጦማሪው፣ የአታሚና የአሳታሚው መብት ብቻ ነው ማለት ሳይሆን፣ እነሱ ‹‹የግንባር ሥጋ›› ቢሆኑም መብቱ የአንባቢውና የሁሉም ዜጎች ነው፡፡ ይህም ሐሳብን መግለጽ ብቻ ሳይሆን መብቱን ማወቅና መጠቀምን ብሎም የጋራ ጥቅሙን በግልም ሆነ በጋራ ማስጠበቅንም ያካትታል፡፡

የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በዚህ ረገድ የተዋጣለት ቢሆንም፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያለን ሰዎች ከፖሊስና ከፀጥታ ተቋማት እስከ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትና (አስተውሉ! ዓቃቤ መንግሥት አይደለም ያልኩት ዓቃቤ ሕግ እንጂ!) ፍርድ ቤት ድረስ ያለን ባለሙያዎች ለዚህ ተግባራዊነት አልተጋንም፡፡ በተለይ ደግሞ የሰብዓዊም ሆነ የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነቶች ጠባቂ ተደርገው የሚቆጠሩትና የየትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል አመኔታ ሊያገኙ ይገባ የነበሩት የፍርድ ቤቶቻችን ችሎት ላይ ‹‹ወደ ማዕከላዊ እንዳንመልስህ የሚሉ ዳኞች እስከተሰየሙና ወደፊትም እስከቀጠሉ ድረስ ችግሮቹ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ ንፍዘት ይሆናል፡፡ ሊቁ እንደ ነገረን መፍትሔው ችግሩን ከፈጠረው አስተሳሰብ ለየት ያለ አስተሳሰብ ማምጣትን ይሻል፡፡

በነገራችሁ ላይ አሁን ባለን የሕዝብ ቁጥር ብዛት በቅርቡ ‹‹ከአፍሪካ ሁለተኛ›› መባላችን አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ ይኼን ለሚያህል ቁጥሩ ሰፊ ለሆነ ሕዝብ ያሉን ጋዜጦችና መጽሔቶች ስንት ናቸው? እነዚህ ኅትመቶችስ በምን ያህል ቅጂ ነው የሚባዙት? ከአዲስ አበባ በምን ያህል ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይነበባሉ? የንባብ ባህላችንንስ ምን ያህል አጎልብተውታል? ወይስ ‹‹ተማረ›› የተባለውም ካልተማረውና በፊደል ካልተሞረደው እኩል ለኅትመቶቻችን ፊት ነስቷል? ዳሩ ‹‹እንቶኔ›› የሚባል ጋዜጣ እኔ መሥሪያ ቤት እንዳይገባ ብሎ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን የግል ግዛቱ የሚያደርግ ከዕውቀት የተጣላ ባለሥልጣን በተፈጠረባት አገር፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘቱም አይታሰቤ ነውና በሆድ ይፍጀው እንለፈው፡፡

ሰው ያስባል ሰው ይፈጽማል

ሰው አሳቢ ፍጡር ነው፡፡ ‹‹የሰው ልጅ›› ተብሎ የሚጠራው የአዳምና የሔዋን ዝርያም በፍጥረተ ባህሪው የማሰብና የህሊና ነፃነቱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹እንዲህ እንዳታስብ›› ወይም ‹‹እንዲህ ብቻ አስብ›› ብለን የሐሳብና የምናብ አድማሱን ልናጠብበት አንችልም፡፡ ስለዚህም የማሰብ ነፃነቱ አዕምሯዊ ነውና አምባገነን መንግሥታት በገነኑበት ወቅትም አይገደቤ ፍፁማዊ መብት (Absolute Right) ሆኖለሁልጊዜ አብሮት ይኖራል፡፡ እንደኔ እምነት ይህ መብት የመብቶች ሁሉ ቀዳማይ ነው፡፡ 

ሕግም ይኼንን መብቱን እንደ ሌሎች ሰዋዊ መብቶቹ ሁሉ ዕውቅና ይሰጥለታል እንጂ አይሰጠውም፣ ወይም አይፈጥርለትም፡፡ ይጠብቅለታል እንጂ አይነሳውም፣ ወይም አይወስድበትም፡፡ የአዳምና የሔዋን ልጅ አሳቢ ፍጡር ቢሆንም፣ ሐሳቡ ግን የራሱ ብቻ ሆኖ አይቀርም፡፡ ሕጋዊ ጥበቃና ዕውቅና ማግኘቱ ግለሰቡ ያንን ሐሳቡን በተለያየ መንገድ ይፋ አውጥቶ እንዲወያይና እንዲያወያይ፣ ለሌሎች ምልከታና እምነቱን እንዲገልጽ ብሎም መሰሎቹን በዙሪያው እንዲያሰባስብና ለዚሁ ሐሳብ ፍፃሜና ተግባራዊነትም እንዲተጋ ያደርገዋል፡፡

ስለዚህም ‹‹ማንኛውም ሰው ያለ አንዳች ተፅዕኖና ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውንና ያመነበትን አመለካከት የመያዝ መብት…›› ያለው ስለመሆኑ በሕግ ታውቆ ቢደነገግም፣ ጥበቃ የሚያሻውና ጥያቄውም የሚመጣው ለውስጣዊው ‹‹የፈለገውን ሐሳብ የመያዝ መብት›› ሳይሆን የመብቱ ዋነኛ ማራመጃ መሣሪያ ለሆነው ‹ሐሳቡን ለሌሎች የመግለጽና የማስተላለፍ በሌሎች የተገለጸውንም የማግኘትና ከሌሎች የመቀበል መብት” ላይ ነው፡፡ የጠቃሚያዊነት (Utilitarianism) መርህ አራማጅና የነፃነት ተሟጋቹ ዮሐንስ ስቱዋርት ሚል ‹‹ስለነፃነት›› በሚለው ታዋቂ ሥራው ውስጥ፣ ‹‹የንግግር ነፃነት የማሰብ ነፃነትን ያህል ቦታ ሊሰጠው ይገባል፤›› ይለናል፡፡ ምክንያቱም አንድን ነገር ማሰቡና በውስጥ መያዙ ሳይሆን ያንን ውስጣዊ ሐሳብ በንግግር መግለጹ ነው፡፡ ምናልባት የሌሎችን ሰዎች መብት ሊነካ የሚችለው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹Rights Limits Right.›› ወይም ‹‹መብት መብትን ይገድባል!›› እንዲሉ የእኛ የመናገር መብት የሌላውን ሰው ሌላ ዓይነት መብት (ለምሳሌ የክብርና መልካም ስም መብት) መንካትና መጣስ እንዳይኖርበት በሕግ ገደብ የሚበጅለት ይሆናል ማለት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግጋትም ይሁን በአኅጉራዊውና አገራዊ ሕጎች ውስጥ የሚጠቀሰውና ‹‹ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሐሳብ የመያዝ መብት….›› የሚለው የሕጉ አገላለጽ ሦስት ነገሮችን በታሳቢነት ያካተተ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም፣

1. በፍጥረተ ባህሪው የሰው ልጆች አዕምሮ ከተፈጥሮና ፈጣሪ የሚይዘውና አብሮት እያደገ የሚሄድ ሐሳብ አለ፡፡

2.. ከሌላ ውጫዊ እንደ ንባብና ትምህርት ካሉ የተለያዩ የዕውቀት ምንጮች የሚቀበላቸው ሐሳቦች ይኖራሉ፡፡

3. እርሱ በራሱ የሚያስበውንና ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ ምንጮች ጋር የሚያዳምረው ሐሳቡም በተጨማሪነት አለለት፡፡

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በኢትዮጵያ ሕግጋተ መንግሥታት

በኢትዮጵያ የሐሳብ ነፃነት (Freedom of Thought) በተሟላ መንገድ በሕግ የታወቀበትና ይኼንኑ ሐሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት (Of Expression) የታወጀበት፣ የፖለቲካና የሕግ መሠረቱም የተጣለበት የሕግ ሰነድ (ከላይ የተጠቀሰው ‹‹የሽግግር ወቅት ቻርተር›› እንዳለ ሆኖ) የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በምዕራፍ ሁለት ሥር በተገለጹት አምስት ዋነኛ መርሆዎች የማዕዘን ድንጋይነት የተገነባ ሲሆን፣ በአሥረኛው አንቀጽ ሥር ከእነዚህ ዋነኛ መርሆዎች አንዱ ሆኖ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ተጠቅሶ እናነባለን፡፡ ከእነዚህ መብቶች ውስጥ ደግሞ አሁን ለንባብ የቀረበው ያሻንን ሐሳብ የመያዝና ይኼንንም በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚመለከተው ክፍል ይካተታል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ሥር የተቀመጡ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ኢትዮጵያ በፊርማዋ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ሲሆኑ፣ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች አተረጓጎም አንፃር መተርጎም እንዳለባቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (1) እና አንቀጽ 13 (2)ን አዋህደን በማናበብ መረዳት ይቻለናል፡፡ በዚህ መሠረትም በምዕራፉ አንቀጽ 27 እንዲሁም አንቀጽ 29 በተለያዩ ንዑሳን አናቅጾች ሥር ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ከነሕጋዊ ገደቦቹ ተዘርዝሮ አለ፡፡ ይህም አንቀጹ እንደ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ሁሉ ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ማነፃፀሪያዎች አኳያ የመመዘንና የመተርጎምን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ድንጋጌው በ ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› መብትነት ብቻ መገለጹ ትግበራው ላይ የሚፈጥረው የራሱ ችግር ቢኖረውም ቅሉ፡፡

የመጀመርያው ድንጋጌ ‹‹የሃይማኖት የእምነትና የአመለካከት ነፃነት›› በሚል ርዕስ ሥር ቢጠቃለልም፣ ከሃይማኖታዊ ምልከታዎች የተቃኘና ከሁለተኛው የማይርቅ በመሆኑ ‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው፤›› የሚለውን ኃይለ ቃል ብቻ ይዘንና መብቱ የሚያካትታቸውን መብቶችንም አቆይተን፣ የሁሉ አቀፍነት ባህሪ ወዳለው ወደ ተከታዩ ድንጋጌ እንሂድ፡፡

ክፍል ሁለት

ዴሞክራሲያዊ መብቶች

አንቀጽ 29

የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት

1. ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡

2. ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡

3- የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠቃልላል፡፡

ሀ) የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣

ለ) የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን፣

4. ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶችን በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡

5. በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፡፡

6. እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሐሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ሕጎች ብቻ ይሆናል፡፡ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና የመልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊጣሉ ይችላሉ፡፡ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናሉ፡፡

7. ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡

በዚህ እጅግ ነፃ (Liberal) በሆነ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውስጥ የተሠመረባቸው አገላለጾች በተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ያልታደሉ ናቸው፡፡ እንደ ማሳያም በንዑስ አንቀጽ 3(ሀ) ሥር ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን›› የሚገልጸው ድንጋጌ በተደጋጋሚ ኃላፊነት በጎደላቸው የመንግሥት አካላት ሲጣስና ጋዜጠኞችም በዚሁ ፍራቻ ሳቢያ ራሳቸውን ‹‹በቅድሚያ እየመረመሩ›› እስከ መጻፍ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ በድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ (4) ሥር የተገለጸው የ‹‹ሕጋዊ ጥበቃ ይደረግለታል›› ኪዳንም ከወረቀት ወደ መሬት ወርዶ አይቼዋለሁ የሚል አልተገኘም፡፡

በንዑስ አንቀጽ 3 (ለ) ሥር የተመለከተውን ‹‹የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን›› ለምርመራ ጋዜጠኝነት አራማጅ ባለሙያዎች እንተወውና አፋጣኝ ምላሽ፣ የአመለካከትና መዋቅራዊ ለውጥ ወደሚሻው ችግር ብሎም የንግግር ነፃነታችን ዓብይ እንከን ስናልፍ በንዑስ አንቀጽ አምስት ሥር የሰፈረውን እናገኛለን፡፡ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ይለናል ድንጋጌው፡፡

በቅድሚያ ስለዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መታወቅና ግልጽ መሆን የሚኖርበት ነገር ‹‹መገናኛ ብዙኃኑ በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብ ይካሄዱ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ይሁኑ እንጂ፣ በአፍ ልማድ እንደምንለው ‹‹የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን›› አለመሆናቸውን ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ነው ሌሎች ነጥቦች የሚመጡት፡፡ መንግሥት እነዚህን በሕዝብ ባለአደራነት የያዛቸውን የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ‹‹የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ›› እንዲችሉ አድርጎ ለመምራት ምን ያህል ቁርጠኝነቱ (Political Commitment) አለው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሒደት የምናገኘው ይሆናል ጊዜ የማያሳየን ምንም ነገር የለምና!

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕገ መንግሥታት ታሪክ ውስጥ ሁለተኛው የሆነውና በ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው የንጉሠ ነገሥቱ የዘውድ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 41 ሥር፣ እንዲሁም የሶሻሊስቷ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የነበረው የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 47 ሥር ይኼው የሐሳብና የንግግር ነፃነት መብት በመሠረታዊ ሰብዓዊ መብትነት ታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ሁለቱም ሥርዓቶች በየወቅቱና በተለያየ ስያሜ ለአንድ ግብር ባቋቋሟቸው ‹‹የጽሕፈትና የኅትመት ገምጋሚ ሚኒስቴሮች›› በኩል የእጅ አዙር አፈና ያካሂዱባቸው እንደነበር ደርሰን ባናይም፣ በንባብ የምናብ ዓለም ማወቅ አይሳነንም፡፡

በዘመነ ኢሕአዴግ እንዲህ ያሉ የፊት ለፊት ቀንበሮችና የአምጣ ልገምግምልህ ጫናዎች በሕግም በተግባርም (ቀጥተኛውን ‹‹ተግባር›› ማለቴ ነው!) የተነሱ ቢሆንም፣ አመለካከቱና ልማዳዊው የተውሶ አሠራር ሕግጋቱን እንጂ ሕግጋቱ እነዚህን አፋኝ አመለካከቶችና ነባር ልማዳዊ አሠራሮች ሊቀይሩ ስላቃታቸው ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ዛሬም ነፃ አልወጣም ብዬ መጻፍ እችላለሁ፡፡ ያልተለወጠና ምናልባትም በአጭር ጊዜ የማይለወጥ አመለካከት መኖርና የጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ዕጦት፣ ለዚህ መብት ተግባራዊ አለመሆን እንቅፋት ሆነው የመቀጠላቸው ነገርም አጠያያቂ አይደለም፡፡

ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ተቋማት

አገሮች የእርስ በእርስ ግንኙነቶቻቸውንም ሆነ ከዜጎቻቸው ጋር የሚኖሯቸውን የተናጠልና የጋራ ግንኙነት በተመለከተ የሚያደርጓቸው ስምምነቶች፣ የሚገቧቸው ውሎችና በረዥም ጊዜ ሒደት ያስለመዷቸውን አሠራሮች፣ እንዲሁም እንደ ‹‹የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት›› ዓይነቶቹ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የሚያወጧቸውን የሕግ፣ የመርሆና የመግለጫ ሰነዶችን ዓለም ዓቀፍ ሕግጋት አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡

እንደ ሌሎች ሰዋዊ መብቶች ሁሉ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕጋዊ ዕውቅና በመስጠቱና ጥበቃ በማድረጉ በኩል እ.ኤ.አ. የ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማቋቋሚያና መተዳደሪያ (The ‘UN’ Charter) ቀዳሚው ሲሆን፣ ይኼው ተቋም በጠቅላላ ጉባዔው ‹‹ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ›› (UDHR) የሚባለውንና እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 10 ቀን 1948 አፅድቆ ይፋ ያደረገው ባለ 30 አንቀጹ ታሪካዊ ሰነድም ከዚሁ ምድብ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

ይህ መግለጫ የልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ (Customary International Law) አካል ሆኖ አገሮች ላይ የገዥነት ሥልጣንና ውጤት ያለው በመሆኑ የሐሳብና ንግግር ነፃነትን በተመለከተ በአንቀጽ 19 ሥር ዘርዘር ያሉ መብቶች ዕውቅና ተችሯቸዋል፡፡ የዚህ ሰነድ ተቀፅላ የሆነውና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR) የተባለው ሰነድም የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን አጣቅሶ፣ በዚሁ አንቀጽ 19 ሥር የሐሳብና ንግግር ነፃነትን ጠቅሶ እንዲህ ያሳርጋል፡፡

በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት የተደነገጉት መብቶች የአጠቃቀም ሁኔታ ልዩ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶችንም ጭምር ይዘዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የተወሰኑ ገደቦች ሊደረጉበት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ገደቦቹ በሕግ የተደነገጉና

ሀ- የሌሎችን መብቶችና ክብር ለማስጠበቅ፣

ለ- ብሔራዊ ፀጥታን፣ የሕዝብ ደኅንነትን፣ ወይም ጤናን ወይም ሥነ ምግባርን ለማስከበር አስፈላጊ መሆን አለባቸው፡፡

ወደ አኅጉራችን አፍሪካ ስንመጣ የምናገኘው ‹‹የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር›› ተብሎ የሚታወቀውን አኅጉር አቀፍ ሰነድ ሲሆን፣ ይህም በአንቀጽ ስምንትና ዘጠኝ ሥር እነዚህኑ መብቶች ይደነግጋል፡፡ ሕጋዊ ከሆኑና በሕግም ከተገለጹ ገደቦቹ በቀር ማንም በዘፈቀደ (Arbitrarily) የግለሰቦችን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ሊያጨናግፍ እንደማይገባም ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 16 ሥር አገሮች በቻርተሩ ስለሐሳብና ንግግር ነፃነት ለተቀመጡ ማንፀሪያዎች (Standards) እና መርሆዎች (Principles) ተፈጻሚነት ከፍተኛውን ጥረት በማድረግ ወደ ተግባራዊነት እንዲቀይሯቸውም ያሳስባል፡፡

ከሌሎች አጠቃላይ የሰዋዊ መብቶች ጎን ለጎን ለዚህ የሐሳብና ይኼንኑ ሐሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት ጥበቃ የሚያደርጉ ዓለም፣ አኅጉርና አገር አቀፍ ተቋማት ብዙ ቢሆኑም፣ መብቱ ከላይ በጠቀስኳቸው ሁለቱ ዋነኛ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ‹‹አንቀጽ 19›› ሥር የተደነገገ በመሆኑ፣ ይኼንኑ ለስሙ መጠሪያ አድርጎ ለሐሳብ ነፃነት የሚተጋ አንድ ዓለም ዓቀፍ ተቋም አለን ‹‹Article XIX›› የሚባል፡፡

ይህ በለንደን የከተመውና በብዙዎቹ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች አይወደዴ የሆነው ተቋም “Global Campaign for Freedom of Expression” በሚለው መለዮውም ይታወቃል፡፡ በአንድ ኅትመቱ ‹‹መረጃ ማግኘት ለሕዝቦች አስፈላጊ ነገር ብቻ ሳይሆን የመልካም መንግሥት መኖር ማሳያ አስኳልም ነው፡፡ መጥፎ መንግሥት ግን ለህልውናው ስለሚሰጋ መረጃን ሚስጥር ማድረግ ያስፈልገዋል፤›› በማለት ሐሳብና ትችትን የሚፈራ መንግሥት ለዜጎች የሐሳብ ነፃነት ብርቱ ሥጋት መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹ጠቅላይ›› የሆነ መልዕክቱንም አስተላልፎ ነበር፡፡

በተከታዩ ቁም ነገር ጽሑፌን ላጠቃልል ወደድኩ፡፡ በሕገ ፍልስፍና ትምህርት ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆነው ዮሐንስ ኦስቲን የተባለው የሕግ ፈላስፋ “Separation Thesis” በሚባለው ችኮ አስተምህሮው ‹‹የሕግ መኖር አንድ ነገር ነው፡፡ ሕጉ ጥሩ ነው ወይስ መጥፎ የሚለው ደግሞ ሌላ ነገር፤›› ቢልም፣ እኔ ግን በኢትዮጵያችን ያለውን መሬት የረገጠ እውነት በማስተዋል እንዲህ እላለሁ፡፡ ‹‹የሕግ መኖር አንድ ነገር ነው፡፡ ሕጉ ተግባራዊ ይደረጋል ወይስ አይደረግም የሚለው ደግሞ ሌላ ነገር፡፡›› የወቅቱ ጥያቄም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ሕጉን መተግበር ወይም አለመተግበር፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

 ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በጉራጌ ዞን የወለኔ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...