Wednesday, June 12, 2024

ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጋር የተጀመረው ድርድር አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ጋር የፖለቲካ ድርድር መጀመሩ፣ ድርድሩም ኦዴግ አገር ውስጥ ገብቶ እንዲሳተፍ በሚችልበት መርሆዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ኦዴግ የተጀመረውን ድርድር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ካወጣ በኋላ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ድርድሩ መጀመሩን በይፋ አረጋግጧል፡፡

በመንግሥት የተወከሉ የፖለቲካ አመራሮች በአሜሪካ ከአመራሮቹ ጋር ግንቦት 3 እና 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገናኝተው መምከራቸውን ያሳወቀው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የተጀመረው ውይይት ለሰፊው ውይይት ፈር ቀዳጅ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በመንግሥትና በኦዴግ አመራሮች መካከል በአሜሪካ የተደረገው ውይይት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ለውጦች ላይ ያተኮረ እንደነበር የኦዴግ መግለጫ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ የማሻሻያ ዕርምጃዎች እንዲሠሩ፣ እንዲጎለብቱና ጥልቀት እንዲኖራቸው ኦዴግ እንደሚፈልግ በመግለጫው ያመለከተ ሲሆን፣ ይህንኑም በመንግሥት ለተወከሉት አመራሮች ማሳወቁን ጠቁሟል፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እ.ኤ.አ. በ2013 የተመሠረተ ሲሆን፣ ግንባሩን የመሠረቱትም በፓርላማ አሸባሪ ድርጅት ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በመመሥረት ለረዥም ዓመታት በአመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ታዋቂ ግለሰቦች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል አቶ ሌንጮ ለታና ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች የኦነግ መሥራች የነበሩ ሲሆን፣ ኦነግ ያራምደው የነበረው ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ነፃ የማድረግ ዕቅድ ጊዜው ያለፈበትና የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅምንም የማያስከብር በመሆኑ የፖለቲካ ትግል ሥልታቸውን በመቀየር የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) እ.ኤ.አ. በ2013 መሥርተዋል፡፡

አቶ ሌንጮ የተመሠረተው ኦዴግ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የኦዴግ መሠረታዊ የፖለቲካ ዓላማም እውነተኛ ዴሞክራሲና ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የሰፈነበት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንደሆነ ከድርጅቱ ድረ ገጽ መረዳት ይቻላል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከኦዴግ ጋር ድርድር መጀመሩንና በቀጣይ የሚካሄዱት የፖለቲካ ድርድሮች በአዲስ አበባ እንደሚሆኑ፣ ለዚህ ሲባል ከፍተኛ የኦዴግ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ በቅርቡ እንደሚገቡ ይፋ አድርጓል፡፡

የድርድሩ ፖለቲካዊ አንድምታ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በ2011 አምስት የፖለቲካ ድርጅቶችን በአሸባሪነት መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ኦነግ፣ ግንቦት 7 እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) መሆናቸው ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ጋር ድርድር የጀመረው የኦዴግ አመራሮች ፓርላማው ኦነግን በአሸባሪነት በፈረጀበት ወቅት የኦነግ አባላት እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ ኦነግ በአሸባሪነት ከተፈረጀ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከድርጅቱ በመልቀቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ በመወሰንና ይህንንም ወደ ተግባር በመቀየር፣ እ.ኤ.አ. በ2013 ኦዴግን በመመሥረታቸው የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን ልብና ይሁንታ እንዳገኙ ይነገራል፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚቀርበው እ.ኤ.አ. በ2015 ተመሳሳይ ድርድር ተጀምሮ የነበረ መሆኑ ነው፡፡

ይህንን የፖለቲካ ጉዳይ የሚከታተሉ የሪፖርተር ምንጮችም አሸባሪ ተብለው በፓርላማው የተፈረጁ ፓርቲዎች ወደ ሰላማዊ ትግል ለመምጣት የማያወላዳ ፍላጎት ካላቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መንግሥት ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ይገልጻሉ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁኔታን በማጥናት አሸባሪ የሚለው ፍረጃ መነሳት የሚችልበትን ሁኔታ በመንግሥት የተቋቋመ ኮሚቴ በማጥናት ላይ መሆኑን፣ እነዚሁ የሪፖርተር ምንጮች ይናገራሉ፡፡

ኮሚቴው ከኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ የዴሞክራሲ ጉዳዮችና የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰኔ 2003 ዓ.ም. አምስት የፖለቲካ ድርጅቶችን በአሸባሪነት መፈረጁ የሚታወስ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስት የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡

እነዚህም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና ግንቦት 7 ናቸው፡፡ የተቀሩት ሁለቱ አልሸባብና አልቃይዳ የተባሉ ሃይማኖታዊ ዘውግ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 25 መሠረት፣ በመንግሥት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ካዳመጣና ከተወያየ በኋላ ነበር ውሳኔውን በአንድ ተቃውሞ ያፀደቀው፡፡

በወቅቱ በፓርላማው አንድ የግልና አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ተቃውሞውንም ያቀረቡት መድረክን በመወከል የፓርላማ መቀመጫ አግኝተው የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ ነበሩ፡፡

በወቅቱ የመንግሥትን የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ ነበሩ፡፡ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብም ኦነግ የተባለው የፖለቲካ ድርጅትን ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበር በርካታ የሽብር ጥቃቶችን በኢትዮጵያ ላይ መፈጸሙን፣ ለአብነትም ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ 106 የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም 56 ንፁኃን ዜጎችን እንደገደለ ተናግረው ነበር፡፡

ኦብነግ የተባለው ድርጀትም በተመሳሳይ በወቅቱ በሶማሊያ ይንቀሳቀስ ከነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ጋር በመተባበር በተለያዩ መንገዶች ባደረሳቸው የሽብር ጥቃቶች ከ132 በላይ የንፁኃን ሕይወትን መቅጠፉን፣ ወ/ሮ አስቴር በወቅቱ ለፓርላማው ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ አስረድተው ነበር፡፡

ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት በበኩሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት አውታሮችን ለማፍረስና ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለመግደል ገንዘብ በመመደብና በማስታጠቅ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል፡፡

የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 25 እንደሚደነግገው በመንግሥት አቅራቢነት ፓርላማው አሸባሪ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን አሸባሪ ብሎ ሊፈርጅ ይችላል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 25 ሥር በአሸባሪነት ለመፈረጅ መመዘኛ መሥፈርቶች ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም የሽብር ወንጀል ፈጽሞ መገኘት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም መዘጋጀት፣ የሽብር ድርጊትን መደገፍ፣ ማበረታታትና በማናቸውም መንገድ ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኘ ድርጊት ናቸው፡፡

ፓርላማው በመንግሥት የቀረበለትትን የውሳኔ ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ በተደረገ ክርክር የተቃውሞ ሐሳባቸውን ያቀረቡት በወቅቱ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ‹‹የውሳኔ ሐሳቡ የተወሰኑ ድርጊቶችን እንጂ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታን ያገናዘበ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንዲሁም ተቻችሎ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በር ይዘጋል፤›› ሲሉ ተቃውመውት ነበር፡፡

የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 25 ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ከመያዙ በተጨማሪ፣ እንደ ፍረጃው ሁሉ በመንግሥት በሚቀርብለት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ፓርላማው ፍረጃውን ማንሳት እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን አስጨናቂ የፖለቲካ ቀውስ አልፎ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰየመው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ቀደም ብሎ በወሰነው መሠረት ከአምስት ሺሕ በላይ እስረኞችን በይቅርታና በምሕረት የለቀቀ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 25 መሠረት አሸባሪ ለተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የአሸባሪነት ፍረጃው እንዲነሳ የሚያስችል ጥናት መጀመሩ ይነገራል፡፡

የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር ቃል ከገቧቸው ፖለቲካዊ አንድምታ የያዙ ውጥኖች መካከል፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በሰላም ለመሥራት እስከተስማሙ ድረስ አብረው እንደሚሠሩ የተናገሩት ይገኝበታል፡፡ ይህንኑ ፍላጎታቸውንም እስካሁን ድረስ በተለያዩ መድረኮች ደጋግመው እያነሱት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -