Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይናው ሴራሚክ አምራች በአምፑል ምርቶችም ለመሠማራት መዘጋጀቱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሴራሚክ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል

በቻይናው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በ26 ሔክታር (260 ሺሕ ካሬ ሜትር) መሬት ላይ የተንጣለለው የሴራሚክ ውጤቶች ማምረቻ፣ በቻይናው ዲ ዩዋን ሴራሚክስ ኩባንያ የሚመራ ፋብሪካ ነው፡፡ ፋብሪካው ምርት በጀመረ በአንድ ዓመት ውስጥ ገበያው ውስጥ ተሰቅሎ የቆየውን ዋጋ ማረጋጋት እንደቻለም ይነገርለታል።

ፋብሪካው በቀን 60 ሺሕ ካሬ ሜትር የወለልና የግድግዳ ሴማሪክ የማምረት አቅም እንዳለው፣ በአሁኑ ወቅትም በአራት የምርት ዓይነትና መጠሪያ የተመደቡ ምርቶችን ለገበያ እንዳዋለ ፋብሪካውን ለጎበኘው ሪፖርተር ያብራሩት የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ዣንግ ሁይ ጂያንግ ናቸው፡፡ ከሠራተኞቹ መካከል 1,100 ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን እንደሆኑና የዕለት ተዕለት የምርት ሒደቱን እነዚሁ ኢትዮጵያውያን እንደሚያቀላጥፉት ገልጸዋል፡፡ ከ1,100 ሠራተኞች ውስጥ 102 ቻይናውያን ሲሆኑ፣ ፋብሪካው 200 ተጨማሪ ሠራተኞችን ለምርት ማሸጊያ ፋብሪካው እንዲሠሩ የመቅጠር ዕቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ የሥራ ላይ ደኅንነት ጥበቃና ለሠራተኞች የሚሰጠው ትኩረት መሻሻልን የሚሹ ችግሮች ናቸው። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ግን ሠራተኞች የሥራ ላይ ደኅንነት መጠበቂያዎችን፣ በተለይም የብናኝ መከላከያ የአፍ ጭንብሎችን በአግባቡ እንደማይጠቀሙበት፣ በስብሰባ ቢነገርም ተግባራዊ ስለማያደርጉ ፋብሪካው ማስጠንቀቂያ እንስኪጻፍበት ድረስ ማስቸገራቸውን በመግለጽ ይሞግታሉ።

ወደ ምርት የማምረት አቅሙ ስንመለስ፣ ምንም እንኳ የማምረት አቅሙን በቀን ወደ 80 ሺሕ ካሬ ሜትር የማሳደግ ዕቅድ ቢኖረውም፣ እያመረተ ያለው በቀን 40 ሺሕ ካሬ ሜትር ሴራሚክ እንደሆነ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅም ሆኑ የኩባንያው ሽያጭና ገበያ ተጠሪ ሊዩ ሊው ይገልጻሉ፡፡ ይህም ማለት 60 ሺሕ ቶን በቀን ማምረት ማለት 90 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸውን ከ660 በላይ ቤቶች በአማካይ በአንድ ቀን ውስጥ መሸፈን ማለት እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ከ98 በመቶ ያላነሰውን የጥሬ ምርት ከአገር ውስጥ የሚጠቀመው ይህ ፋብሪካ፣  ለሴራሚክ ምርት ግብዓት የሆኑትን ስድስት ዓይነት የሸክላ አፈር ባህርይ ያላቸውን ወሳኝ ግብዓቶችን ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች እንደሚያገኝ ታውቋል፡፡

ከውጭ በሚገባ 150 ቶን የድንጋይ ከሰል ወርኃዊ የኃይል ፍጆታውን የሚያሟላው ይህ የሴራሚክ ፋብሪካ፣ ከዚህ በተጨማሪ ከ65 ሺሕ እስከ 70 ሺሕ ኪሎ ዋት በሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭም ለምርት ሥራው ያውላል፡፡ የፋብሪካው ሥራ መጀመር ከውጭ በገፍ የሚገባውን የሴራሚክ ውጤት በአገር ውስጥ ከመተካት ባሻገር በዋጋ ማረጋጋት በኩልም ሚናውን እንደተወጣ ሊዩም ይገልጻሉ፡፡

ፋብሪካው ምርቶቹን ለገበያ ማቅረብ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ 60 በ60 ሚሊ ሜትር የሚባለውን መጠን የሚወክለው ሴራሚክ፣ ከ420 እስከ 450 ብር በካሬ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ ይሁንና የፋብሪካው ሥራ መጀመር ግን ይህንን ዋጋ በግማሽ ያህል እንደቀነሰውና በአሁኑ ወቅት የገበያው ዋጋ እስከ 220 ብር እንደወረደ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ሆኖ በአገር ውስጥ ገበያ ከዚህ ቀደም በገፍ የገባና የተከማቸ ምርት በስፋት ስለሚገኝ፣ ከዋጋ ማረጋጋቱም ሆነ በአገር ውስጥ የተመረተውን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የማዳረስ ፈተና ፋብሪካውን እንደገጠመው ሊዩም ሆኑ የሴራሚክ ኩባንያው ወኪል አከፋፋዮቹም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የመንግሥት የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶችና የሪል ስቴት ገንቢዎች በሰፊው ግዥ እንደሚፈጽሙ ተብራርቷል።

ፋብሪካው ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ወደ ጎረቤት አገሮችም ምርቶቹን መላክ እንደጀመረ ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የመጀመርያውን አራት ሺሕ ካሬ ሜትር ወይም ሁለት የጭነት መኪና ሙሉ ምርት ወደ ጂቡቲና ብሔራዊ የነፃነት በዓሏን እያከበረች ወደምትገኘው ሶማሌላንድ መላኩ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ባሻገር ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ሌሎችም የጎረቤት አገሮች በቅርቡ የምርቶቹ መዳረሻዎች እንደሚሆኑ የፋብሪካው ተጠሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተያዘው ወር ለሶማሌላንድ ብቻ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ምርት የመላክ ዕቅድ እንዳለ ሊዩ አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ካለው የ1.5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የሴራሚክ ምርት ክምችት አኳያም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያዎች የማቅረብ ችግር እንደሌለበት ተጠቅሷል።

ከሴራሚክ ምርቶቹ ባሻገር እዚያው ዱከም በሚገኘው ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ሁሉንም ዓይነት ኤልኢዲ የኤሌክትሪክ አምፑሎችን የሚያመርት ፋብሪካ እየተከለ እንደሚገኝም ኩባንያው አስታውቋል። ይህም ፋብሪካ ምርቶቹን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች እንደሚያውል ተገልጿል። የዚህ ፋብሪካ ዕውን መሆንም በኢትዮጵያ በየምዕራፉ በመከፋፈል፣ ኢንቨስት ለማድረግ፣ የመደበውን የ278 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችለው ሊዩ ተናግረዋል። እስካሁን ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለመጀመርያ ምዕራፍ ኩባንያው ኢንቨስት ስለማድረጉም ጠቅሰዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች