Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ አሴት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጓል

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሕንፃዎች እየገነባ ነው

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቋሚ ሀብት ለማፍራት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በጀመረው እንቅስቃሴ ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ አምስት የሕንፃ ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ባንኩ ከአዲስ አበባ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዱከም ከተማ ያስገነባውን ለሁለገብ አገልግሎት የሚውል ሕንፃ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ባስመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ባንኩ ቋሚ ሀብት ለማፍራት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማሳደግ ላይ ነው፡፡

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንዣ የምረቃ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ከሌሎች አቻ ባንኮች አንፃር ሲታይ ባንካቸው በሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ አነስተኛ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቋሚ ሀብት ለማጎልበት በተቀየሰው ስትራቴጂ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ የሕንፃ ግንባታዎችን እየገነባ ይገኛል፡፡ ከዚህም ሌላ ለራሱ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃና የኮንዶሚኒየም ግዥዎች በማካሄድ የሀብት መጠኑን ከፍ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን እያደገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በዱከም ከተማ የተመረቀው ባለአምስት ወለል ዘመናዊ ሕንፃም የዚሁ ስትራቴጂ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

 

ባንኩ ሕንፃውን ለማስገንባት ዱከም ከተማን የመረጠበትን ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ዱከም ከተማ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ በሚገኘው አውራ ጎዳና ላይና የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ጣቢያ መገኛ በመሆኗ ነው፡፡ እንዲሁም ባንኩ ከተማዋ ተመራጭ የኢንዱስትሪ መንደርና የኢንቨስትመንት ቀጣና እንደሆነች ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ግንባታውን ለማከናወን ሲነሳ በጥናት በመታገዝና ለግንባታ የሚሆነውን መሬት የከተማው አስተዳደር ያወጣውን የሊዝ ጨረታ በማሸነፍ ግንባታውን ሊያካሂድ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ይዞታ ቦታው ጠቅላላ ስፋት 2,353 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ሕንፃው በ1,100 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል፡፡ በሕንፃው ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች አጠቃላይ የወለል ስፋትም ከ4,938 ካሬ ሜትር በላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሌሎች ተጓዳኝ ወጪዎችን ሳይጨምር ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቷል፡፡ በ730 ቀናት ወይም በሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የግንባታ መጓተት ሳይገጥመው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ስለመጠናቀቁ አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡

የዱከም ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ሆርዶፋ በከተማዋ ውስጥ በተያያዘለት የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀ ሕንፃ ስለመሆኑ ተናግረው፣ እንዲህ ያለው አሠራር ለሌሎች ባለሀብቶችም ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎች ባለሀብቶችም ግንባታዎቻቸውን በወቅቱ እንዲተገብሩ ጭምር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሕንፃው ለተለያዩ ተቋማት ቢሮዎች፣ ሱቆች፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ካፍቴሪያና ሌሎችን አገልግሎቶችን ጭምር ታሳቢ በማድረግ የተገነባ ነው፡፡ ከዚህ ግንባታ ውጭ ባንኩ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስበትና ትልቁ አሴቱ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው በአዲስ አበባ የሚገነባው ባለ37 ወለል ሕንፃ ግንባታ ነው፡፡ ይህ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበትና ሠንጋተራ አካባቢ እየተገነባ ያለው ሕንፃ፣ በአሁኑ ወቅት ስትራክቸር ሥራው 33ኛ ወለል ላይ ደርሷል፡፡ ቀሪው የአራት ወለል ስትራክቸር ሥራ ከተሠራ በኋላ ሰኔ 2010 ዓ.ም. የሕንፃው የማጠናቀቂያ ሥራዎቹ እንደሚጀመሩ ከአቶ ክብሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደ ትንሳዔ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው ከዚህም በኋላ ቋሚ ሀብት በማፍራቱ ተግባር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡ ባንካቸው ካስቆጠረው ዕድሜ አንፃር ቋሚ ሀብት በማፍራቱ ረገድ ብዙ ያልተራመደ መሆኑን ሊቀመንበሩ ጠቅሰው፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ቋሚና ዘላቂ ዕድገቱን ለማስቀጠል እንዲቻል የባለአክሲዮኖችን ካፒታል ወደ ቋሚ ንብረት የመለወጥ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ሌሎች ተወዳዳሪ ባንኮች ቋሚ ሀብት ከመያዝ አንፃር ብዙ ርቀት መሄዳቸውን የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ አሁን ባንካቸው የጀመረው ዕርምጃም ውጤት እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የባንኩ ትልቅ አሴት ይሆናል የተባለው ግንባታ በሐዋሳ ከተማ ልዩ ስሙ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለዘጠኝና ባለአሥራ አንድ የሆኑ መንትያ ሕንፃዎች ናቸው፡፡ መንትያ ሕንፃዎቹ ሁለት ቤዝመንት ያላቸው ሲሆን፣ በ1,980 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንዳረፉ ተገልጿል፡፡ ግንባታውም ከ304 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው 30 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

በዚሁ ክልል ጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤ ከተማ የሚገኘውና በ594.38 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ባለሦስት ወለል ሕንፃ 21.7 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለሥራ ያበቃ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ በሆሳዕና ከተማም በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው ሕንፃ የማጠናቀቂያ ሥራ ብቻ ይቀረዋል፡፡ መሠረታዊ የግንባታ ሥራው አብቅቶ የማጠናቀቂያ ሥራው የቀረው ይህ ሕንፃ፣ በ587.5 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እንደሆነም የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡

ባንኩ ሀብቱን ከማሳደግ አኳያ ወስጀዋለሁ ካላቸው ዕርምጃዎች ውስጥ ከወራት በፊት ጠንካራ የጨረታ ፉክክር የተደረገበትና አሸናፊ ሆኖ ወደ ባንኩ ንብረትነት የዞረው አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውና በ2,926 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በመከታ ሪል ስቴት የተገነባው ሕንፃ ነው፡፡ ይህንን ሕንፃ ባንኩ በ680 ሚሊዮን ብር በመግዛት የቋሚ ሀብቱን ለማሳደግ የጀመረው እንቅስቃሴ ሌላ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም ሌላ የባንኩን አሴት ማሳደግን ተቀዳሚ ግቡ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች በርካታ ቢሮዎችን በግዥ ወደ ባንኩ ንብረትነት እንዳዞረም የባንኩ መረጃ አሳይቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ላፍቶ፣ ሀያት፣ ሃያ ሁለት፣ ቱሉዲምቱ፣ ሰሚት፣ ልደታና የካ አባዶ አካባቢዎች የገዛቸውን ቢሮዎች ለምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በጅግጅጋና በመተማ ዮሐንስ የሚገኙት ሕንፃዎችን መግዛቱን ገልጿል፡፡

ንብ ባንክ ሲመሠረት በ717 ባለአክሲዮኖች፣ 20 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ይዞ ሲሆን፣ በወቅቱ በከፈተው ብቸኛ ቅርንጫፍ 27 ሠራተኞችን ቀጥሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ባንኩ እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከ4000 በላይ ባለአክሲዮኖች፣ ከ4,500 በላይ ቋሚ ሠራተኞች፣ ከ210 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ጠቅላላ የሀብቱ መጠን 25 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ የተቀማጭ ሒሳቡ መጠን ከ20.1 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ የባንኩ መረጃ የብድር መጠኑም ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች