የዳንጎቴ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራ ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. አሥር ሰዓት ላይ ከጸሐፊያቸውና ከሾፌራቸው ጋር ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ረጂ በተባለ አካባቢ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ መገደላቸው ተሰማ፡፡
በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ተቀጣጥሎ በነበረው ሕዝባዊ አመፅ ሳቢያ ንብረቶቻቸው ከተጎዱባቸው ፋብሪካዎች መካከል ዳንጎቴ አንዱ ነው፡፡
ግድያውን የፈጸሙ አካላት ማንነታቸው ያልታወቀ ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም አልተረጋገጠም፡፡
የዳጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮት አስታውቀዋል፡፡