Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የገና ዋዜማ በአዲስ አበባ ገበያ

ትኩስ ፅሁፎች

“ምን አሸዋ ቢያልቡ…”

በቀደም ደወለች፤
አወጋች አወጋሁ
በስተመጨረሻ
“ደና ሰንብች” ብየ፤ የስልኬን አፍ ዘጋሁ፡፡

ከዚያም ቀናት አልፈው
ወራት እንደ ቅጠል፤ እግሬ ሥር ረግፈው
ልጅ ሆና የማውቃት፤ እናቷን አከለች
ዘጠኝ ወር አርግዛ፤ ሞት ተገላገለች፡፡

“ምን አሸዋ ቢያልቡ
ነፋስ ቢጋልቡ
ዳመናውን ጠርበው፤ ሀውልት ቢገነቡ
በመርፌ ቀዳዳ፤ ዳይኖሠር ቢያስገቡ
ሞትና ክስመት ነው፤ የተፈጥሮ ግቡ”
ብዬ እንዳልጽናና
በሞቷ ገጽ ፊት፤ ሐሳብ ሁሉ መና
ምክር ሁሉ ኦና
እንባን አይገድብም፤ የሰው ፍልስፍና፡፡

በፍራሻችን ሥር፤ ቃሬዛ ተጣብቆ
በልብሳችን ገበር፤ ከፈን ተደብቆ
የእድሩ ጥሩንባ፤ ከሙዚቃው ልቆ
በዘንድሮ ጣቶች፤ ከርሞ ላይነካ
“ደና ሰንብች” ማለት፤ ዘበት ኖሯል ለካ፡፡

(ይህ ግጥም፤ ለእህቴ ለክብርት ሥዩም፤ እንዲሁም እሷን ለመሰሉ፤ ለመውለድ ባምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ገብተው በቃሬዛ ለሚወጡ ያገሬ እናቶች መታወሻ ይሁንልኝ፡፡)

**********

ጎርፍና ግፍ

ሰሚ ካጡ የሶማሌ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ አንድ ሰው የጠፋች የአካባቢው ግመል ፍለጋ ጫካ ይገባል፡፡ ከብዙ መከራ በኋላ ያቺን ግመል አግኝቶ ከተማ ገባና ግመሏን ለባለቤቱ ሳይመልስ ሐሳቡን ቀይሮ ራሱ ያልባትና ይጋልባት ጀመር፡፡ ግመሏን ከአውሬ ለማዳን ጫካ ገብቶ የነበረው ሰውዬ እርሱ ራሱ ግመሏን መውሰዱ ብዙዎችን አስገረማቸው፡፡ ትንሽ ቆየና ከዚያች ከአንዷ ግመል ወተት እያለበ በግመሏ ላይ ተቀምጦ እየዞረ ለአካባቢው ሰው ወተት መሸጥ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የግመሏ ወተት በአንድ ጊዜ ሀብታም ሊያደርገው አልቻለምና ሌላ ነገር አሰበ፡፡ በወተቱ ውስጥ ውኃ እየጨመረ ቀላቅሎ መሸጥ፡፡ ‹‹ሰውም ምነው የሰውየው አመሉም ወተቱም ተቀየረሳ›› እያለ ዝም ብሎ ይገዛ ጀመር፡፡ (ይገዛ የሚለው ቃል ጠብቆ እንዳይነበብ አሳስባለሁ)

ሰውዬውም በግመል ወተቱ ላይ ውኃን እያበዛው፤ የግመሉም ቁጥር እየጨመረ ሄደ፡፡ እየቆየም በግመልና በግመል ወተት ከሚታወቁት የሀገሩ ነጋዎች በላይ እኔ ነኝ ያለ፣ ቢጠሩት የማይሰማ ሀብታም ሆነ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ‹‹ይኼ ሰው ትናንት ምንም አልነበረውም፡፡ የጠፋ ግመል ሊፈልግ ጫካ ገባ፤ ተመልሶ መጣ፤ ከተማ ገባ፤ በአንድ ጊዜ ተመነደገ›› እያሉ ይገረሙ ነበር፡፡ ወተት ብቻ ተሽጦ እንዴት በሁለት ዓመት ሦስት መቶ ግመል ሊገዛ ቻለ፡፡ የሚለው የሕዝቡ ሁሉ ወሬ ሆነ፡፡

ሰውዬው ግን ምንም አልመሰለው፤ በወተቱ ውስጥ ውኃውን እየጨመረ ቀጠለ፤ እንዲያውም እበላ ባይ ቱልቱላዎችን ቀጠረና የእርሱ ወተት ሰው ጠጥቶት የማያውቅ መሆኑን እንዲለፍፉ አደረ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ወተቱን ለመልኩ ብቻ ይጨምርበትና የቀረው ውኃ ያደርገው ነበር፡፡ ‹‹ኧረ ሕዝቡ እያማረረ ነው፤ በአንድ በኩል በድንገት ተነሥህ፤ ከተማ ገብተህ ቢጠሩህ የማትሰማ ሀብታም ሆንክ፤ ይኼንን ስንታገሥህ ደግሞ ወተቱን ቀንሰህ ውኃውን እያበዛህ መሸጥ ጀመርክ፡፡›› ሲሉት ‹‹ተውት ባካችሁ፣ ለመሆኑ የእኔን ወተት ከመግዛት ውጭ ሕዝቡ ምን አማራጭ አለው፤›› ይል ነበር፡፡

በወተቱ ውስጥ የሚጨመረው ውኃም እየበዛ፣ ግመሎቹም እየበዙ ሄዱ፡፡ ግመሎቹም ሀገሩን ሞሉት፡፡ የሚያድሩበትና የሚግጡበት ልዩ የከተማ መሬት ተሰጣቸው፡፡ ወንዝ ዳር የሚገኝ ለም መሬት፡፡

አንድ ቀን ሸበሌ ወንዝ አጠገብ ግመሎቹን አሠማርቶ እርሱ አንድ ዛፍ ጥላ ሥር ሻሂ ከልጁ ጋር ይጠጣ ነበር፡፡ በዚህ መሐል ከደጋ የዘነበ ዝናብ ወንዙን ሞላውና በግራ በቀኝ ሲግጡ የነበሩትን ግመሎች ጠራርጎ ወሰዳቸው፡፡ የጎርፉን ድምጽ ሰምተው አባትና ልጅ ከጥሻው ሲወጡ ግመሎቻቸው ሁሉም ተወስደዋል፡፡ እሪታውን ሰምተው የተሰበሰቡ የሀገሩ ሰዎችም በአግራሞት የሆነውን ነገር ይመለከቱ ነበር፡፡

‹‹አየህ›› አሉት አንድ አዛውንት ‹‹ያ በወተቱ ላይ እየጨመርክ የሸጥከው ውኃ ተጠራቅሞ፣ ተጠራቅሞ ጎርፍ ሆኖ ግመሎቹን ወሰዳቸው፡፡ ግፍ እንደዚህ ነው፡፡ ሲሠራ ቀላል ይመስላል የተጠራቀመ ዕለት ግን ጎርፍ ሆኖ ይወስዳል፡፡ ተው ብንልህ አልሰማ ብለህ ነበር፤ አንተ በግፍ ግመል ስትሰበስብ የግፉ ውኃ ሌላ ቦታ እየተሰበሰበ መሆኑን ረስተህዋል፡፡ ቀን ጠብቆ ግን ይሄው ጎርፍ ሆኖ መጣ›› አሉት፡፡ ግፍና ጎርፍ፡፡ (በዳንኤል ክብረት)

******

የገና ጨዋታ ልማድ

መጀመሪያ ሁለት ሰዎች ይመረጡና የቡድን አባት ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ “የቡድን አባቶች” ይልና፣ “ከአንበሳ ከነብር፣ ከእንጀራ ከጠላ፣ ከገደል ከሾተል” ይላል፡፡ የቡድኑ አባት “አንበሳ” ያለ እንደሁ ለርሱ አንበሳ ያለው ሲሰጥ ቀሪው ለሌላው ቡድን ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ ምርጫው ሲያልቅ የቡድን አባቶች እሩሯን መሐል ሜዳ ላይ ገብተው ምግ ተያይዘው ይለጋሉ፡፡ እንደፍጥነቱ ጥንጓን ወይም እሩሯን የያዛት ለመለጋት ሲለቅ አንደኛው ቀለብ ያደረጋት እንደሆን እንደፍጥነቱ ይለጋታል፡፡ ከዚያ በኋላ ብርታትን የሚጠይቅ ጨዋታ ይሆንና እንደጥጓን ከወዲያ ወዲህ እየሮጡ ጥንጓን ወደ ተወሰነው ግብ ለማግባት የሚደረገው ትግል ራስን እስከመርሳት የሚያደርስ ነው፡፡ የግብ ብልጫ ያገኘው ሆ እያለ አሸናፊነቱን በመግለጥ ከተጫዋቾቹ ስም እየጠራ እንደ ሰውዬው ሁናቴ በመልኩ ዓይነት እየገጠመ ይሰድበዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስድቡ ያማርርና እመደባደብ ላይ ይደረሳል፡፡ ምሳሌ ያህል እንዲታወቅ በጨዋታው ላይ የሚገጠሙትን ግጥሞች ከዚህ በታች እጠቅሳለሁ፡፡ ለቀጭን ጌታው አቶ እገሌ ይችን እግር ብዬ እኔ አልሄድባትም እየቆራረጥሁ እጥላለሁ የትም ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንደአንበጣ ወዘና የሌህ ማሣይ የጨጓራ ቋንጣ ዘወር በል ከፊቴ በሽታዬ መጣ ለአጭር ጌታው አቶ እገሌ አሎሎ ቁመት ዶሮ ሙሃይት ሰው እንዴት ይወልዳል አስመስሎ ጃርት ለረጅም ይህን ረጅሙን ጎሚዶ ጎሚዶ ገሚሱን በርጩማ ገሚሱን ማገዶ ለለንቦጫሙ እኔ እሰድብሃለሁ አንተ ስማኝ ብቻ ከንፈርህ ቅልብስ ነው እንደማር ስልቻ፡፡

  • “የታሪክ ማስታወሻ” ከተሰኘው የደጃዝማች ከበደ ተሰማ መጽሐፍ የተወሰደ
  •  

ቻይናዊው ገበሬ የቦይንግን ተመሳሳይ ሬስቶራንት ሊያደርጉ ነው

በቻይና ኤንያን በተሰኘ ከተማ አንድ ቻይናዊ በቤት ውስጥ የሠሩትን የቦይንግ 737 ተመሳሳይ ሬስቶራንት ሊያደርግ መሆኑ ተዘገበ፡፡ ይህን የቦይንግ አምሳያ የሠሩት ዋንግ ሊን የባሉት የ61 ዓመት ቻይናዊ ገበሬ ምንም ያልተማሩ ሲሆን በእርሻቸው የቦይንግ አምሳያ እንዲገነባ ያደጉት እርሻቸው ላይ የሚሠሩ ሌሎች ገበሬዎችን በማስተባበር ነው፡፡ አዛውንቱ ምንም እንኳ ያልተማሩ ቢሆኑም እ.ኤ.አ 2014 ላይ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግና የአልሙኒየም ሥራ ትምህርት መጀመራቸው ረድቷቸዋል፡፡ ገበሬው እንዳሉት 115 ጫማ ርዝመት እንዲሁም 125 ጫማ የክንፍ ርዝመት ያለውን ይህን የቦይንግ 737 አምሳያ ለመሥራት 22,000 የአሜሪካ ዶላር ወጪ አድርገዋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ ውስጡን ሬስቶራንት እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ማስተካከል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  •  

በተለያየ ዓመት የተወለዱት መንትዮች

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ውስጥ መንቶች በተለያየ ዓመት መወለዳቸው ተሰማ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በሳንዲያጎ ሆስፒታል አንዲት እናት መንቶች ስትገላገል የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ በፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ ስትገላገል ሁለተኛውን ወንድ ደግሞ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ዕለት በመገላገሏ ነው፡፡ የነፍሰጡሯ እናት በዚህ መልኩ በተለያየ ቀን መገላገል ልጆቹ ባለቀው የፈረንጆቹ ዓመት 2015 እና በአዲሱ 2016 እንዲወለዱ አድርጓል፡፡ ሕፃናቱ መንታ እንደመሆናቸው ብዙ ነገራቸው የሚመሳሰልና ብዙ ነገር የሚጋሩ ቢሆንም የልደት ቀናቸው ግን አንድ አይሆንም፡፡ በሳንዲያጎ ሆስፒታል በተለያየ ዓመት የተወለዱት ሕፃናት ሌላም አስገራሚ ነገር አላቸው፡፡ የመጀመሪያዋ በሳንዲያጎ ግዛት በ2015 የተወለደች የመጨረሻዋ ሕፃን ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ በ2016 የተወለደ የመጀመሪያው ሕፃን ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል፡፡ ለ34 ዓመታት በነርስነት ያገለገሉት ሴንቲ ኮቴንላ በአገልግሎት ዘመናቸው እንደዚህ ያለ ነገር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ‹‹ይህ በጣም ያልተለመደና ልዩ ነገር ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡ 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች