Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት መሪን ጨምሮ 47 ሰዎችን በሞት መቅጣቷ የቀሰቀሰው ቁጣ

ሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት መሪን ጨምሮ 47 ሰዎችን በሞት መቅጣቷ የቀሰቀሰው ቁጣ

ቀን:

ሳዑዲ ዓረቢያ ቅዳሜ ታኅሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ተደማጭነት ያላቸውን የሺዓ ሙስሊም የሃይማኖት መሪ ኒምር አል ኒምርን ጨምሮ 47 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች፡፡ ይህም በሳዑዲ ቁጣን ሲቀሰቅስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሳዑዲ እየተወገዘች ነው፡፡ ቀድሞውንም በየመን ጉዳይ ፊትና ኋላ በሆኑትና የውክልና ውጊያ እያደረጉ በሚገኙት በሳዑዲና በኢራን መካከልም ውጥረቱን አጋግሏል፡፡

ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፣ 47ቱ ሰዎች የተገደሉት ሽብርተኛ ተብለው ሲሆን፣ ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም የሳዑዲ ዜግነት አላቸው፡፡ ከተገደሉት አራቱ የሺዓ ሙስሊም እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሱኒ ናቸው፡፡ የሳዑዲን መንግሥት የሚመሩት የሱኒ ባለሥልጣናት የሞት ፍርዱ የአልቃይዳ አባል ናቸው በተባሉና እ.ኤ.አ. በ2011 በሳዑዲ ተነስቶ በነበረው የፀደይ አብዮት የተሳተፉ ናቸው ቢሉም፣ በሳዑዲ ዜጎች በተለይም በሺዓ ሙስሊሞች ተቀባይነትን አላገኙም፡፡ በሺዓ እምነት ተከታዮች ዘንድ ተደማጭነት የነበራቸውና ‹‹መንግሥት ሁሉንም የእምነት ተከታዮች በእኩል ይመልከት፣ ዜጎች ተበድለዋል፤›› በማለት መንግሥትን የሚኮንኑት ሼክ አል ኒምር መገደል ተቃውሞውን አባብሶታል፡፡

አል ኒምር እ.ኤ.አ. በ2011 የዓረብ የፀደይ አብዮት በሳዑዲ በተለይም በምሥራቁ ክፍል ዋና ሚና ነበራቸው፡፡ በሺዓ ማኅበረሰብ አባላትም ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ተደማጭና የማሳመን ችሎታ ያላቸው ሲሆኑ፣ በሳዑዲ መንግሥት ላይም ቀጥታ ትችት የሚሰነዝሩ ነበሩ፡፡ የእሳቸው መገደል ከሳዑዲ አጋሮች በስተቀር መካከለኛው ምሥራቅ በሳዑዲ ላይ እንዲቆጣ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሟቾች ሽብርተኞች ናቸው ቢሉም፣ ኢራንን ጨምሮ የሺዓ እምነት ተከታዮች ተቃውመዋል፡፡ አሜሪካም የሞት ፍርዱ በተለይ በአል ኒምር ላይ የተወሰደው ዕርምጃ በሳዑዲ አለመረጋጋት ሊያመጣ ይችላል ብላለች፡፡

ኢራን የሳዑዲን ባለሥልጣናት ግብታዊና ኃላፊነት የጎደላቸው ስትል ወቅሳለች፡፡ ከዚህ ባለፈም በአገሮቹ መካከል ቀድሞውንም የነበረው ፍጥጫ ተባብሷል፡፡ ሳዑዲ የኢራንን ዲፕሎማት ከአገሯ አስወጥታለች፡፡ ኢራን ደግሞ፣ ‹‹ሳዑዲ ዓረቢያ ዋጋ ትከፍልበታለች፤›› ስትልም ተናግራለች፡፡ የአል ኒምር መገደልን ተከትሎ በቴህራን ለተቃውሞ የወጡ ሠልፈኞችም የሳዑዲ ኤምባሲን አቃጥለዋል፡፡ ድርጊቱን የኢራን መንግሥት እንዲሁም አሜሪካ የተቃወሙ ሲሆን፣ ኢራን በሳዑዲ ኤምባሲ ላይ ጥቃት የፈጸሙትን እንደምትቀጣ አስታውቃለች፡፡

የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሒዝቦላህ ‹‹የአል ኒምር ግድያ ሳዑዲን ሁሌም የሚከተላት ጠባሳ ሆኖ ይቀጥላል፤›› ሲል፣ የቀድሞ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢራን ቀኝ እጅ ኑሪ አል ማሊኪ ደግሞ፣ ‹‹ግድያው የሳዑዲን መንግሥት ሥልጣን ያነቃንቃል፤›› ብለዋል፡፡

በባህረ ሰላጤው የሳዑዲ ቀኝ እጅ የሆኑት ባህሬንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ደግሞ ሳዑዲ በሽብርተኞች ላይ የወሰደችው ዕርምጃ ተገቢ ነው ሲሉ ድጋፋቸውን ለሳዑዲ ቸረዋል፡፡ ባህሬን የኢራን ዲፕሎማት ከአገሯ እንዲወጡም ትዕዛዝ አስተላልፋለች፡፡

አሶሼትድ ፕሬስ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሚስ ጆን ኪርባይን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ የሳዑዲ መንግሥት ሰብዓዊ መብትን ማክበርም ሆነ መጠበቅ አለበት፡፡

የሳዑዲ መንግሥት ፍርዱ ፍትሐዊ መሆኑን ማረጋገጥና ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ለሚጠይቀው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አለበት የሚሉት ኪርባይ፣ አያይዘውም የአል ኒምር መገደል በሳዑዲ የእምነት ልዩነትን ያባብሳል፣ ውጥረትን ያነግሣልም ብለዋል፡፡

በሳዑዲ መጠነኛ ተቃውሞ እየታየ ነው፡፡ በምሥራቅ ሳዑዲ ዓረቢያ በምትገኘው ኳቲፍ እንዲሁም የሳዑዲ አጎራባችና አብዛኛው ሕዝቧ ሺዓ መሪዎቿ ደግሞ ሱኒ በሆኑባት ባህሬን ተቃውሞዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡

የሳዑዲ ከቢር አል ሙፍቲ ሼክ አብዱላዚህ አል ሼክ በሳዑዲ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት የፈጸመውን የሞት ፍርድ መደገፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ፍርድ ነው፡፡ የመሪዎች ሥራ ደኅንነትንና መረጋጋትን መጠበቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች የሞት ፍርድ መፈጸሙን ቀድመው ነው የተቃወሙት፡፡ ሳዑዲ እ.ኤ.አ. በ1980 የመካ መስጊድን ወረው የነበሩ 63 ጂሃዲስቶችን በሞት ከቀጣች በኋላ የአሁኑ በቁጥር ትልቁ ነው፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር ሳራ ሊህ፣ የሳዑዲ ዕርምጃ በአገሪቱ የሃይማኖት ክፍፍልን፣ እንዲሁም የከፋ ውጥረትን ያመጣል ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ ከ150 በላይ ሰዎችን በመቅላት አሊያም በጥይት በመደብደብ እንዲሞቱ ወስና ተፈጻሚ ሆኗል፡፡ ይህም በአገሪቱ በሁለት አሥር ዓመታት ውስጥ ከነበረው የሞት ፍርድ ትልቁ ነው፡፡

የሳዑዲ ዕርምጃ ከኢራን ጋር የነበራትን የሻከረ ግንኙነትም አባብሶታል፡፡ የሳዑዲ መንግሥት ባለፈው እሑድ ከኢራን ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጡን አሳውቋል፡፡ በኢራን የሚገኙትን ዲፕሎማቱን የጠራ ሲሆን፣ በሳዑዲ የሚገኙት የኢራን ዲፕሎማት ከሳዑዲ እንዲወጡም ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ኢራን ሳዑዲ በቀጣናው ውጥረት እየፈጠረች ነው ስትል ትወነጅላለች፡፡ አሜሪካ በበኩሏ አገሮቹ እንዲረጋጉና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲወያዩ ጥሪ አቅርባለች፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን ጠንካራ ጉልበት ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በተነሳ ቁጥር ሁለቱም ወገኖች ራሳቸውን ለሚመስለው ወግነው በሰው ምድር ይዋጋሉ፡፡

የ47ቱን ሰዎች መገደል በተለይም የአል ኒምር በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት ባለፉት 30 ዓመታት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ አደገኛ ያደርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በኢራን ቴህራን የሳዑዲ ኤምባሲ የተቃጠለ ሲሆን፣ በሳዑዲ ሪያድ የኢራን ዲፕሎማት መገኛ ሥፍራ ፍንዳታ አጋጥሞታል፡፡ በሁለቱም ወገኖች በኩል ጉዳት አልደረሰም፡፡

በኢራንና በሳዑዲ መካከል ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አለመግባባት አለ፡፡ አገሮቹ በሶሪያና በየመን የሚያራምዱት የተቃረነ ሐሳብም ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡

የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሩሃኒ፣ በኢራን የሳዑዲ ኤምባሲ ላይ የደረሰውን ጥቃት ትክክል እንዳልሆነና፣ የፈጸሙት እንደሚቀጡ ተናግረው፣ ሳዑዲ ‹‹ገጽታዋን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አበላሽታለች፡፡ በተለይም በዓረቡ ዓለም እስላማዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽማለች፤›› ብለዋል፡፡

የኢራን የበላይ ጠባቂ አያቶላህ አል ኾሚኒ የሳዑዲ ምዕራባውያን ደጋፊዎች፣ ሳዑዲን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹ይህ የሃይማኖት መሪ ሕዝቡ መሣሪያ አንስቶ መንግሥትን እንዲወጋ አልጠየቀም፡፡ በድብቅ መንግሥትን ለማጥቃትም አልሞከረም፡፡ ሁሉም በሚያውቀውና በሚሰማው መንገድ በቀጥታ የሳዑዲ መንግሥት ትክክል አለመሆኑን ተናግሯል፤›› ሲሉም ኾሚኒ ተደምጠዋል፡፡

ሼክ አል ኒምር በሳዑዲ ከሚኖሩት ሙስሊሞች 15 በመቶውን የሚሸፍኑት የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ነበሩ፡፡ የሃይማኖት መሪ ሲሆኑ፣ ክሳቸው የታው ግን ቦምብ በማፈንዳት፣ መሣሪያ በመታጠቅ ጥቃት ከሚሰነዘሩት ጋር በማበር በሽብር ተወንጅለው ሞት ተፈጻሚ የሆነባቸውም አሸባሪ ተብለው ነው፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሳዑዲው ንጉሥ አል ኒምርን ከመገደል ማዳን ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ጣልቃ አልገቡም፡፡ ይህም ለሳዑዲ ችግር ይዞ መጥቷል፡፡ ሳዑዲ ከኢራን ከመቃረኗ በተጨማሪ የሺዓ ሙስሊሞች ባሉባቸው ሁሉ ውግዘትና ተቃውሞ ገጥሟታል፡፡ ከዚህ ባለፈም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን፣ አሜሪካና እንግሊዝ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሃይማኖት መሪው በሞት መቀጣት ሌላ ቀውስ ያስከትላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡               

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ