Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከታሪክ ሠሪነት ወደ ታሪክ ሰሚነት የተሸጋገረ ትውልድ

ከታሪክ ሠሪነት ወደ ታሪክ ሰሚነት የተሸጋገረ ትውልድ

ቀን:

ኢትዮጵያ አገራችን በጀግኖች አባቶቻችን አማካይነት ድንበሯን አስከብራ የኖረች ባለታሪክ አገር መሆኗን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በዓለም ፊት ቀና ብለን እንድንሄድና የአፍሪካም ኩራት እንድንሆን አስችሎናል፡፡ የያኔው ትውልድ የጠላትን እጅ እያስከነዳ በመጣበት እግሩ እንዲመለስ አድርጓል፡፡ እንደ ዛሬው በእጁ ብር ያልጨበጠው፣ በእግሩ ያጌጡ ጫማዎችን ያልተጫማው – ያ ትውልድ፡፡ እንደ ውቅያኖስ ጥልቅ፣ እንደ ሰማይ ሩቅ፣ እንደ ሰለሞን ጥበብ ረቂቅ የሆነ ታሪክን ሠርቶልን አልፏል – ያ ትውልድ፡፡

የአሁኑ ትውልድስ?

የአሁኑ ትውልድ ታሪክ ሠሪ እንጂ ሰሚ እንዳይሆን ምን እየሠራ ነው? ይህ የዕለቱ ዋና ጭብጤ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ የአያትና የቅድመ አያቶቹን ታሪክ ጥንቅቅ አድርጎ የማወቅ ጉጉቱ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን የማረምና የማስተካከል፣ እንዲሁም ባለራዕይ የመሆን ፍላጎቱ፣ ራሱንና አገሩን የመለወጥ ተነሳሽነቱ አነስተኛ መሆኑን በተለያዩ ሁኔታዎች ለመረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ለዚህ ሐሳቤ ግብ መምቻነት እስኪ የሚከተለውን ጉዳይ እንመልከት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ተከራይቼ የምኖረው አየር ጤና ነው፡፡ በዕረፍት ሰዓቴ አልፎ አልፎ ካራ ወደሚገኘው ጓደኛዬ ቤት እሄዳለሁ፡፡ አንድ ቀን የአየር ጤናን አደባባይ እንደ ተሻገርሁ ፊቴን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሳዞር ሱፐር ማርኬት የሚያክል ጫት ቤት ተመለከትኩ፡፡ በአሥር ሜትር ልዩነት ሌላ ጫት ቤት፡፡ አሁንም ሃያ ሜትር ርቀት ሳንጓዝ ሌላ ጫት ቤት፡፡ በዚህ ሠፈር ከሦስት ዓመት በላይ የኖርኩ ቢሆንም እንደ ዛሬው ግን የጫት ቤቶችን ሁኔታ ልብ ብያቸው አላውቅም፡፡

ከዚህ በፊት ሳሙናና ምላጭ ይሸጥባቸው የነበሩ ሱቆች በሙሉ የጫት መሸጫ ሆነዋል፡፡ ካራ ረፒ ትምህርት ቤት እስከምደርስ ድረስ ቢያንስ ከአርባ በላይ ጫት ቤቶችን ቆጠርሁ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ጫት ቤቶች ውስጥ ታሽገው የሚውሉት ወጣቶች መሆናቸው ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ወጣት ጉልበት ሥራ ላይ ቢውል አገራችን እንደ ቻይና ድህነትን ገርስሶ ለመጣል ግማሽ መንገድ አትጓዝም ነበር?

ጫት ቤት ቁጭ ብለን፡-

    “ኧረ ጫት ገመዱ

    ኧረ ጫት ማሠሪያው

    ጠላ’ማ ምን ይላል

    ደፍተውት ቢሄዱ?”

እያልን ከምንዘምር ምናለበት፡-

   “ሥራ ነው መሠረት

   የእኛ ሕይወት ስንቁ

   ዛሬም ነገም መሥራት

   ሁሉንም ሳይንቁ” እያልን ብንዘምር?

ለነገሩ አሁን አሁን ሠፈሩ ወደ ጫት ቤት የመልሶ ማልማት ተቀይሯል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ወጣቶች የጫት ደንበኛ ሆነው ከሠፈሩ ጋር ቁርኝት ፈጥረዋል፡፡ ምርቃና ላይ የደረሱት ግን ተሰድደዋል፡፡ ከተሰደዱት ወጣቶች አንዱ የእኔ ጓደኛ ነበር፡፡ እናስተምርበት ከነበረው የግል ትምህርት ቤት እንደወጣን እሱ ወደ ጫት ቤት ጎራ ይላል፡፡ በእርግጥ ሥራ ከሚገባበት ቀን የማይገባበት ይበልጣል፡፡ እሱ የሚቅምበት ጫት ቤት ደግሞ ልዩ አሠራር አለው፡፡

“በዱቤ እናስቅማለን” የሚለው የጫት ቤቱ መለያ ባህሪ ነው፡፡ ጓደኛየም የዱቤ በመቃም ሪከርድ በመበጠሱ ባለቤቱ የሁለት ወይም የሦስት ቀናት ጫት በነፃ እንደሚያስቅሙት ነግሮኛል፡፡ የዱቤ ሪከርዱ ግሽበት ላይ ሲደርስ ባለቤቱ ሙሉ ደመወዙን ተቀበሉና የቀረውን ዕዳ አፉ ብለው አሰናበቱት፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን በእሳቸው ቤት ሁለተኛ በዱቤ እንደማይቅም መንገራቸው ነበር፡፡ ይህንን ዜና የሰማ ዕለት ዕርር ድብን አለ፡፡ ከልቡ አዘነ፡፡

መጨረሻ ላይ ከትምህርት ቤት ተሰናበተ፡፡ አየር ጤናንም ለቀቀ፡፡ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባላውቅም እንደ ግሪሳ ወፍ የሚከተለው የጫት ሱስ ግን የሚለቀው አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ከምቀርባቸው አስተማሪዎች መካከል ከስድስቱ አራቱ የሚቅሙ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በእርግጥ እነሱ አሁንም ይቅማሉ፡፡ ከቀን ወደ ቀን ፊታቸው ላይ የማነበው ተስፋ የመቁረጥ፣ ራዕይ ያለመኖርና የተጎሳቆለ ሕይወትን ነው፡፡ ትውልዳችን ወዴት እያመራ ነው? ታሪክ ሠሪ ወይስ ሰሚ እየሆነ? “ጃፓን እንደምን ሠለጠነች” በሚለው የከበደ ሚካኤል መጽሐፍ ላይ የጃፓን ሥልጣኔ መሠረቱ ዜጎቿ፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የወጣቱ ትውልድ ባለራዕይ መሆን፣ አገሩን ከድህነት ለመለወጥ ያለው ቁርጠኝነት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡

አሁን ደግሞ ሌላ አባሪ ላቅርብ

ባለፈው ጊዜ ወደ ሥራ ቦታ ለመምጣት የታክሲ ሠልፍ ይዥ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ከኋላዬ ያሉ ሁለት ወጣቶች በጀርባቸው ቦርሳ ይዘዋል፡፡ የተማሪነት መገለጫ ዩኒፎርምም ለብሰዋል፡፡ ከጨዋታቸው ወደ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ ባለ አንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ተረድቻለሁ፡፡ በጨዋታቸው መካከል ‘40 በ60’ ሲሉ ሰማሁና ልቤን መታ ስላደረገው ጨዋታቸውን ለማዳመጥ ቀልቤን ሙሉ በሙሉ ወደ እነሱ አደረግሁ፡፡ ‘40 በ60’ ለምን ቀልብህን ገዛው? ካላችሁኝ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዋናው ችግር የቤት ጉዳይ በመሆኑና 40 በ60 ኮንዶሚኒየም ቤትን በተመለከተ ምን አዲስ ነገር አለ በማለት ነበር፡፡

ጨዋታቸው ደስ አለኝና ወደ ኋላ ዛር ብዬ “40 በ60 ምንድነው?” አልኩት አንደኛውን ተማሪ፡፡ ተሳሳቁና “የምንማረው የግል ትምህርት ቤት ነው፤” አለኝ ተማሪው፡፡ “የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ኮንዶሚኒየም ቤት ማስመዝገብ ጀመሩ?” አልኳቸው በቀልድ ቢጤ፡፡ ሁለቱም ተሳሳቁ፡፡ ከዚያ አንደኛው ተማሪ “ተመቸሽኝ” አለኝ፡፡ “ተመቸሁህ?” አልኩት ፈገግ ብዬ፡፡ በነገራችን ላይ ያሁኑ ትውልድ ሳይታወቅ ፆታውን የቀየረ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ወንድን “አንተ” ከማለት ይልቅ “አንቺ” እያልን መጥራት የተለመደ ሆኗል፡፡ ወደ ጨዋታችን ልመልሳችሁ፡፡

“40 በ60 በወሬያችሁ ተመችቶኛል፤” አልኳቸው ወደ ቀድሞው ጨዋታችን እንደመለሱልኝ በመፈለግ፡፡ “ያው 40 በ60 ሲባል 60 በመቶ አሳይመንት፣ 40 በመቶ ደግሞ የጽሑፍ ፈተና ነው፤” አለኝ፡፡ “60 በመቶ አሳይመንቱን እንዴት ነው የምትሠሩት?” አልሁት፡፡ “አሳይመንቱ የሚሰጠን በቡድን ነው፡፡ ከመካከላችን አንድ ጎበዝ ተማሪ ይሠራውና እናስገባለን፡፡ ሁሉም ተማሪ ግን ከ50 በላይ ነው የሚያመጣው፡፡ ከጽሑፍ ፈተናው ቢያንስ 15 ብታመጣ 65 በመቶ ታመጣና ወደ 12ኛ ክፍል ታልፋለህ፤” አለኝ፡፡ ውስጤ እርር አለ፡፡ አይ የትምህርት ጥራት፡፡ መጪው ትውልድ ተማራማሪና ችግር ፈቺ የሚሆነው በዚህ ሁኔታ ነው? ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ የሚሸጋገሩት እንዲህ ነው? ተማሪዎች በመማሪያ መጻሕፍቶቻቸው ውስጥ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች በዚህ ሁኔታ ተምረውና ተፈትነው? ትውልዱ ጠንቅቆ የሚያውቀው የቱ ጋ ነው? ወደፊት ሕይወቱ እንዲያስብ የሚያደርገው የቱ ጋ ነው?

በሁለቱም ልጆች አዕምሮ ውስጥ ያለው ስለባርሴሎና በዘንድሮው ዓመት እንደ ሶቪዬት ኅብረት መንኮታኮት፣ ስለአርሴና ማንቼ ነው፡፡ ይባስ ብለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በእሑድ መዝናኛ ፕሮግራሙ ስላቀረባቸው የዕድሜ ባለፀጋ እናትና የሜሲ አድናቂ ስለሆኑ ሴትዮ አንስተው መጨቃጨቅ ጀመሩ፡፡

“ሴትየዋ ግን አይገርሙም?” አንደኛው ተናገረ፡፡

“ምን ይገርማል?” ሌላኛው መልሶ ጠየቀ፡፡

“ሜሲን ከልጄ አስበልጨ ነው የምወደው ነው’ኮ ያሉት?” አለ፡፡

“እሺ አንተ አሁን እሱን ከእናትህ አታስበልጠውም?”

“እ… እሱስ ልክ ነህ…” መለሰለት፡፡

አሁን ይህን ምን ይሉታል? በእርግጥ የዚህ ችግር ተጋሪ የኛ እናቶችና አባቶቻችን መሆናቸው ደግሞ ችግሩን የባሰ ያደርገዋል፡፡ የልጅ ልጆች ያዩ እናት “መሲን ከልጄ አስበልጨ ነው የማየው፤” ያሉት ሐሳብ ቀኑን ሙሉ ሲገርመኝ ነው የዋለው፡፡ በዚህ ዕድሜና አቅማቸው እንኳ ሌሊት እየወጡ የሜሲን ጨዋታ እንደሚከታተሉ ሲነግሩን በእውነት ዝብርቅርቅ ያለ ሐሳብ ነበር የተሰማኝ፡፡ የእኚህ ሴትዮ ልጆች አርሴ፣ ማንቼ እያሉ ለትምህርታቸው ደንታ ባይኖራቸው ተጠያቂው ማነው? የአገሩን ታሪክ ሳያውቅ ቢቀር፣ ስለአገሩ ዕድገት፣ ራዕይና ተነሳሽነት ባይኖረው ዘወትር ስለአውሮፓ ሲያልም ቢውል ጥፋቱ የማን ነው?

የጹሑፌ መግቢያ ያደረግሁት የአያትና የቅድመ አያቶቻችን ታሪክና ጀግንነት ነበር፡፡ የእነሱ ጀግንነትና ባለራዕይነት እንዳለ ሆኖ በትውልዱ መካከል ግን ሰፊ ልዩነት እንዳለ ተረዳሁ፡፡ በእነዚህ ተማሪዎችም ላለመፍረድ ዳዳሁ፡፡  እናቶቻችን ለአርሴናል፣ ለባርሴሎና፣ ለሜሲ፣ ወዘተ እያሉ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ከሆነ ልጆቻቸውን ከዚህ መሰልና ሌሎች ሱሶች የማይቆጣጠሩ ከሆነ፣ የቀን ተቀን ትምህርታቸውንና የመሳሰሉትን የማይከታተሉ ከሆነ ተጠያቂዎች ወላጆች ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ከሁሉ በፊት መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ቢሆንም፣ ራሳችን በተለይ እኛ ወጣቶችም ከዚህ መሰል ሱሶች መውጣት እንዳለብን እገምታለሁ፡፡

ከዚህ ሁሉ የፀዳ ትውልድ ሆነን አገራችን በኢኮኖሚዋ የዳበረች፣ በፖለቲካዋ ሁኔታዋ የተከበረች እርስ በራሳችን የምንከባበርና የምንረዳዳ ትውልዶች መሆን አለብን፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ የቅድመ አባቶቻችን በሠሩልን ታሪክና ጀብዱ እኛ የአሁኑ ትውልዶች ድህነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆን አለብን፡፡ ከሱስ የፀዳ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ዜጋ መሆን አለብን፡፡ ታሪክ ሠሪ እንጂ ሰሚ መሆን የለብንም፡፡ ደረታችንን ነፍተን ባለፈ ታሪካችን “እኛ እኮ የጀግና ሕዝብ ዘር ነን” ከማለት ይልቅ ራሳችን በራሳችን ስም የሚጻፍ ታሪክ መሥራት አለብን፡፡

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  

     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...