- Advertisement -

መንደፋደፍ ብቻ!

ጉዞ ከኮተቤ ወደ ፒያሳ ተጀምሯል፡፡ ገና ከመምሸቱ ሰው ቢተቃቀፍ አልሞቀው ብሏል። ‹‹አቤት ብርዱ ምን ይሻለኛል እቱ?›› ጋቢና የተቀመጠው ከጎኑ ያለችዋን እየጠየቀ ነው። ‹‹ብርድ ብርቅ ነው?›› ትለዋለች መልሳ። ‹‹እሱስ ልክ ነሽ። የብርድና የሙስና ብርቅ የለውም። ስለሌለውም ‘ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ሆ ስላልን በሳምንታት ዕድሜ ሌባ አይደነግጥም’ አሉ ሲባል ነው የሰማሁት?›› ይላታል። ‹‹ይኼኔ የሮናልዶ ቁርጭምጭሚት ወለቀ ተብሎ በቴሌቪዥን ሰምተን ቢሆን ጨዋ ሌባ ሳንባባል ክው ብለን ነበር፤›› ሲል ደግሞ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ጎልማሳ ነገሩን አዞረው፡፡ ‹‹ቁርጭምጭሚት ይወልቃል እንዴ?›› እያለች አንዲት ባለመነጽር ወይዘሮ ጠጋ ብላ ትጠይቀኛለች። ‹‹ታዲያ ሌባ እስኪደነግጥ ስንት ሳምንት እንጠብቅ?›› የሚለው ደግሞ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት ነው።

‹‹የምን ሳምንት? ስንት ዓመታት እንጠብቅ አትልም?›› ብላ ደግሞ ሳያስበው የድምጿ ግርማ ኮከብ የሚያረግፍ አጠገቡ የተቀመጠች ቆንጆ አስበረገገችው። ‹‹አስደንግጭኝ አልኩሽ እንዴ? ልብ ካለሽ ሌቦቹን ማስደንገጥ ነው፤›› አላት። ‹‹ልብ የሌለው አለ?›› ስትለው በቀኝ ተደርቦ የተቀመጠ በአረቄ ሲጉሞጠሞጥ ያመሸ የሚመስል ደግሞ፣ ‹‹እንክት አድርጎ ነዋ። ልብማ ድሮ ቀረ። የዛሬን አያድርገውና ድሮ በዚህን ሰዓት በቁማችን ጠርሙስ ሙሉ አረቄ ደቅደቅ ደቅደቅ ስናደርግ ታክሲ አጣለሁ የለ፣ መብራት ጠፍቶ በጨለማ እሰናከላለሁ አናውቅ። አከራዮቻችን እንዳሁኑ ከመጠጥና ከመብል ፍቅራቸው ወደ ገንዘብ ዞሮ ከሚጠጣበት ለምን አይከራይበትም? ዓይነት በወር በወር ይጨምሩብን ይሆን ብሎ ሥጋት የለ። እንዲያው ምን አለፋሽ ልብ አልኖረን ብሎ በሁለት መለኪያ ተጠናቀን ከዶሮ እኩል ይኼው ቤት እንገባለን፤›› ሲል ተሳፋሪዎች ተሳሳቁ። አንዳንዱ የኑሮው ጨለማ አልነጋ ሲለው ሲጨልጥ በማንጋት ሊያካክስ ይከጅለዋል። ጉዟችንም ተጀመረ። እኛም እንደ መንገዱ ተጀምረን ይኼው አላለቅንም!

ወያላው ከጎኑ ክርኑን ከሚያስደግፍበት መቀመጫ ላይ ለሚተዋወቃት ሴት ሰፋ ያለ ቦታ መርቶ፣ ‹‹እንዴት ነሽ እባክሽ?›› ይላታል። ‹‹እስቲ ዛሬ እንኳ ጋብዘኝ?›› ትለዋች ጤንነቱን መጠየቅ ትታ። ‹‹አንቺ በቃ ካለጋብዘኝ አታውቂም?›› ይላታል። ‹‹አንተስ ሰላም በጠፋበት በዚህ ጊዜ አሥር ጊዜ እንደ ጀማሪ አፍቃሪ አሁንም አሁንም ደህና ነሽ ማለት አይሰለችህም?›› አለችው። ‹‹እንኳን አሥር መቼ ሁለት ጊዜ ጠየቅኩሽ?›› ሲላት፣ ‹‹ትናንት ተገናኝተን ጠይቀኸኝ መልሼልሃለሁ። አለቀ! ወር ሳይሞላህ እንዳትጠይቀኝ፤›› ብላ ተቆናጠረችበት። ‹‹ጉድ ነው እንደ ቤት ኪራይ ጤና ይስጥልኝም ወር በገባ ሆነ ደግሞ?›› ብሎ አጠገቧ ተጨናንቆ የተቀመጠ ወጣት አሽሟጠጠ። ‹‹አዎ! በኪራይ ኖረን በመዋጮ እየተቀበርን እስኪ አሁን በየቀኑ ጤና ይስጥልኝ ስንባባል አያቅርም?›› አለችው መለስ ብላ። ‹‹አይምሰልሽ ደሃ ከጤናው በቀር ሀብት የለው፤›› ወያላው ስብከት ጀመረ።

‹‹እኔስ ገንዘብ ቢሰጠኝ ነበር የምመርጠው። ጤና በኪራይ ቤት በቀን አንዴ እየተበላ በራሱ ካንሰር በለው፤›› ብሎ መሀል ረድፍ የተሰየመ ኮልታፋ ጨዋታውን አፋፋመው። ‹‹ኧረ ተመስገን ነው እናቴ። ይኼንንስ ማን አየብን?›› ብለው አጠገቡ የተቀመጡ አንዲት አዛውንት ሲናገሩ፣ ‹‹ድሮስ ማን ያይብናል እማማ? ነው ወይስ ጉዳይ ለማስፈጸም የኩላሊት ጉቦ ስጡን መባል ተጀመረ?›› አላቸው። ‹‹ኩላሊት? እኮ ይኼ እዚህ ከሙሃሂቴ ከፍ ብሎ የምነካው ጎኔ ሥር ያለውን ማለትህ ነው?›› አዛውንቷ የምራቸውን ደነገጡ። ‹‹እህ ሌላ አለ?›› አላቸው ግራ ገብቶት ግራ እያጋባቸው። ‹‹ሞልቶ! የበግ አለ። የበሬ አለ። የላም አለ፤›› ሲሉ ፈገግ አስባሉን። ይኼን ጊዜ ኮልታፋው፣ ‹‹አይ እማማ። እሱማ ድሮ በደጉ ጊዜ ቀረ። አሁን ማን ይሙት የበግ ኩላሊት እንደ ልባችን እንደ ለመድነውና እንዳሻን የምናገኝ ቢሆን ኖሮ የገዛ ኩላሊታችንን እየበላን እንጨርሰው ነበር?›› ሲላቸው እስኪያስነጥሳቸው ከት ብለው ሳቁ። ቆይ ግን ኩላሊት በመብላት ኩላሊት ይጠገናል እንዴ? ግራ አጋባን እኮ ሰውዬው!

ወያላው ከኪሱ ሻማ አወጣና ለኮሰ። ‹‹ምን ይላል ይኼ? ማንን ሊያሳጣ ነው?›› ትለኛለች ከጎኔ የተሰየመችው ወይዘሮ። ‹‹ሒሳብ ወጣ ወጣ…›› አለ ወዲያው። ‹‹በሻማ? ኧረ እንዳታቃጥለን አንተ ሰውዬ፤›› አዛውንቷ ቀወጡት። ወያላው፣ ‹‹ታዲያ ምን ላድርግ? ሞባይሎቻችሁን እያበራችሁ ተባበሩን ሲባል የባትሪ ቻርጅ ያልቅብናል ትላላችሁ፤›› ብሎ ስሞታ ከማቅረቡ ጎልማሳው፣ ‹‹ቻርጅ እናደርገው የለም እንዴ ቤታችን ስንገባ? ምን ሰበብ ታበዛለህ?›› ብሎ ዓይን የሚወጋ ነጭ መብራት ከስልኩ ፈነጠቀ። ‹‹መብራት ሲኖር አይደል ቤት የምንገባው? ስልኩን መሙላት ቀርቶብን እራታችንን አሙቀን በበላን?›› ብላ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንዷ ብሶቷን አስደመጠች። ወዲያው ያ ዓይን የሚወጋ መብራት፣ ‹‹ለካ እሱም አለ?›› ከሚል አስታዋሽ ድምፀት ጋር ታጅቦ ጨለመ።

ወያላውም እፍ ሊላት የነበረችውን ሻማ እንዳትጠፋ እያባበለ በመያዝ እንድንተባበረው ጠየቀ። ‹‹እግዚኦ ሥልጣኔ። ብለን ብለን በመኪና እየተጓዝን ሻማ እንለኩስ?›› ሲለኝ ያ አረቄ ውኃው የሆነ ደግሞ በትንፋሹ ልሰክር ጫፍ ደርሻለሁ። ‹‹ቆይ ግን እኛ ራሳችን የምንለኮሰው መቼ ነው?›› ብሎ ደግሞ መጨረሻ ወንበር ያ ጣልቃ መግባት የሚወደው ወጣት ይጠይቃል። ‹‹በነገር ነው በእሳት?›› ትለዋለች ከጎኑ። ‹‹እንዴ እስካሁን አልተለኮስንም እንዴ?›› ከፊት ጎልማሳው ያደናግራል። ‹‹ምናለበት እስኪ አሁን ህዳሴያችን ግቡን እስኪመታ ብንታገስ?›› አዛውንቷ ላይ ተደርቦ የተቀመጠ ሰላላ ድምፅ ያስተዛዝናል። ‹‹ከዛስ? አታፍሩም እኮ በቀጥታ ከጨረቃ መብራት ይቀጠልልናል ትሉን ይሆናል እኮ?›› ብሎ ኮልታፋው የሚያውቀው ያህል ይደፍረዋል። እንደ አያያዛችን ገና ብዙ ሳንደፋፈር አንቀርም!

- Advertisement -

ጉዟችን ቀጥሏል። ሾፌሩ ሬዲዮ ከፍቶ የሰዓቱን ዜናዎች ያስደምጠናል። ‹‹አይ አንተ ፈጣሪ ሩሲያን ከተረሳችበት አስታውሰህ እንዲህ በየአርስተ ዜናው ስሟን ያስናኘህ አምላክ እባክህ እኛንም አስታውሰን! እባክህ?!›› ጎልማሳው እጆቹን ዘርግቶ ፈጣሪውን ውረድ ይላል። ይኼን ጊዜ አጠገቡ የተቀመጠው ወጣት ‹‹ደስ አይልም?›› ብሎ ፀሎቱን አቋረጠው። ‹‹ምኑ?›› ሲለው ‹‹ለጉልቤም ጉልቤ ሲያዝበት ደስ አይልም?›› አለው። ጎልማሳው፣ ‹‹ማን ማን ላይ ነው የታዘዘው?›› ብሎ መልሶ ሲጠይቀው፣ ‹‹ምሥራቅ ምዕራብ ላይ ነዋ። አሜሪካ እንዲህ አድርጋ፣ አሜሪካ እንዲህ ቆንጥጣ፣ አሜሪካ እንዲህ ስቃ፣ አሜሪካንን ትን ብሏት ከሚል ዜና ዕድሜ ይስጠውና ፑቲን ገላገለን። ግድ የለም እኛም አንድ ቀን  . . . .›› ብሎ ሳይጨርሰው፣ ‹‹በል በል ወንድም እኛ ከዚህ በላይ ማዕቀብ የሚችል ትከሻ ይለንም። እንኳን አዲስ ለሚጣል ማዕቀብ ኑሮንም አልቻልነው፤›› ብሎ ጎልማሳው አቋረጠው።

‹‹እስኪ ስላቁን ተውትና አንዴ ዜና እንስማበት?›› ብሎ ጋቢና የተቀመጠው ድምፁን ሲጨምረው ደግሞ ኮልታፋው፣ ‹‹ማነህ ወያላ? ‘ሰው በዜና ብቻ አይኖርም በስላቅና በሽሙጥ ጭምር እንጂ’ ብለህ ጥቅስ ለጥፍማ፤›› ይለዋል። ‹‹አንዳንዶቻችሁ የምታስወነጭፉት ሚሳይል ምን ላይ እንደሚያርፍ እያስተዋላችሁ…›› ብሎ ወያላው ማስጠንቀቂያ ሲወረውር መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ተኮራኩረው የሳቁ እስኪመስል ድረስ አሽካክተው፣ ‹‹ፀረ ሚሳይል መግዛት ነዋ። ደግሞ ለዚህም ተበደሩና ግማሹን ቆርጣችሁ ኑሯችሁን አደላድሉበት አሏችሁ፤›› አለች ከመሀላቸው አንዷ። ‹‹ማንን ነው? ይኼ ጆሮዬ እኮ እንቢ አለ በቃ፤›› ብለው አዛውንቷ ኮልታፋውን ጠየቁት። ‹‹እንኳን ቀረብዎ እማማ። እንኳን አልሰሙ…›› ብሏቸው፣ ‹‹ምናለበት ጆሮ እንደሚያከራክር ሁሉ ሆድም የሚያንገራግር ሆኖ ቢፈጠር?›› አለ ወደኛ ዞሮ። አንዳንዱማ ይችልበታል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እኔ ግን ነገሬ ሁሉ እንዲህ አልጨበጥ ያለበት ሚስጥር ነው የማይገባኝ፤›› ይላል አንዱ። አሁን ወደ ጨለመ አካባቢ ስለሆንን ማንም ማንን አያይም። ‹‹ማን የሚጨበጥለት አይተሃል?›› ይላል ኮልታፋው። ‹‹ዓለም ዘጠኝ ናት፤›› ትላለች ሌላዋ። ‹‹እኛ ነና አሥር ካልሞላች ያልነው። ሃያ ያደረሱዋት ግን ዘጠኝን አልፈው አሥራ ዘጠኝ ላይ ናቸው። ሰላሳ ናት ያሉዋት ሃያ ዘጠኝ ላይ ናቸው። በአሥር ተለክፈን ዘጠኝ ላይ ክችች ያልነው እኛ፤›› ብሎ ጎልማሳው ይተነትናል። ‹‹እናንተ ከመሙላት ምን አላችሁ? የሚሉት አዟውንቷ ናቸው። ‹‹እንዴት?›› ያ ድምፀ ሰላላ ይጠይቃል። ‹‹ሕይወት ቁም ነገሯ መሙላት መጉደሉዋ አይደል? ቁም ነገሯ ሚዛን ነው። ዓለም በበኩሏ እናንተ እንደምትሉት የሞላ የጎደለ ነገር የለባትም። ታክሲ አደረጋችኋት እንዴ ጎድላ የምትሞላው? አንዳንዶቻችሁ ጭራሽ ታክሲ ላይ እንዳያችሁት ትርፍም ያምራችኋል። ጉድ እኮ ነው!›› ብለው ለራሳቸው ጥቂት ቃላት አጉተምትመው ሲያበቁ፣ ‹‹ለጊዜያችሁ ክብር ሳትሰጡ፣ ለገንዘባችሁ ሳታዝኑ፣ ለጤናችሁ ሳትሳሱ፣ በወጣችሁ በገባችሁበት ሁሉ ያለዕቅድ ውላችሁ እያደራችሁ እንዴት ይሞላላችኋል ልጆቼ? ነግቶ እስኪመሽ ማሳበብ። ወይ ከመሀላችሁ የሚነግሥና የሚለውን በተግባር ሊያሳየን የሚችልበት ዕድል ያለው ሰው አናይ። በዚያ ላይ ኑሮ እንደምታዩት…›› ሲሉ የሚያወሩት ግራ ስለገባን አንዱ ቶሎ ብሎ፣ ‹‹ምን ይሻላል ነው የሚሉት እርስዎ?›› አላቸው። ‹‹ሚዛን ጠብቁ›› አሉት።

‹‹አቤት?›› ሲል አሁንም ደገሙለት። ‹‹ሚዛን!››  .  . . እና ይኼው ከዚያ ዕለት አንስቶ ከታክሲ ጥበቃው ጎን ለጎን ሚዛን ጥበቃ ልምምድ ላይ ነን። ቤት ስንገባ ደግሞ ቁራጭ ሻማ ፍለጋ እንንደፋደፋለን፡፡ ታክሲው ፒያሳ ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲለን ለአዛውንቷ ቅድሚያ ሰጥተን በፀጥታ አንድ በአንድ ወረድን፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ድባብ ይሁን ወይም ሌላ ነገር ፒያሳ በሰው ደመቅ ብላለች፡፡ አዛውንቷ ወደ አዲሱ ገበያ የሚወስዳቸውን ታክሲ ለመያዝ ሲያመሩ እኛም ወደየፊናችን ተንቀሳቀስን፡፡ በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ለእያንዳንዱ ጅማሬ ፍፃሜ አለው፤›› ሲል ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹እያንዳንዱ ፍፃሜም ጅማሬ ነበረው፤›› አለው፡፡ ‹‹እንዲህ በነገር እየተከታከትን ኑሮን ካልገፋነው እንዴት ይዘለቃል›› የሚል የአንድ ጎልማሳ ድምፅ ከሩቅ ሲሰማ እኛም ተበታተንን፡፡ መንደፋደፍ ብቻ! መልካም ጉዞ!    

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

የተገራ ስሜት!

እነሆ መንገድ ከስታዲዮም ወደ ጦር ኃይሎች። በጥበቃ የተገኘ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ ሚኒ ባስ ታክሲ ውስጥ ተሳፍረናል፡፡ ምሁር መሳይ ተሳፋሪ አጠገቡ ለተቀመጠ የዕድሜ እኩያው ማብራሪያ...

ሄድ መለስ!

እነሆ ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ከረጅም ሠልፍና ጥበቃ በኋላ የተገኘ ዶልፊን ሚኒባስ ታክሲ በወያላው አስተናባሪነት በየተራ ተሳፍረን መቀመጫችን ስንይዝ፣ ጋቢና የተሰየመ ተሳፋሪ በእጅ...

የሁለት ዓለም ሰዎች!

ዛሬ ከአዲሱ ገበያ ወደ መርካቶ ልንጓዝ ነው። በዝነኛው የአገራችን ሙዚቀኞች ምሥል ያሸበረቀችው አሮጌ ታክሲ በትርፍ ሰዓቷ በማስታወቂያ ሥራ የምትተዳደር ትመስላለች። በዚህ ጊዜ በአንድ የሥራ...

የህሊና ዕዳ!

ዛሬ የምጓዘው ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ ነው። በማለዳው ውርጭ ተሠልፈን ባገኘነው ዛኒጋባ መሳይ ሚኒባስ ታክሲ መንገዳችን ከመጀመሩ በፊት በየተራ ተሳፍረን ቦታ ቦታችንን ይዘናል፡፡ እንደ መቶ...

አሳረኛው ኑሮ!

የዛሬው ጉዞ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ይሆን ዘንድ ግድ ሆኗል፡፡ ለምን? በኑሮ  ምክንያት፡፡ የታክሲ መሠለፊያው ወሬ የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ ስለሚመጣው ተጨማሪ ታሪፍ ነው፡፡ ‹‹የእኛ ኑሮ...

ሻካራው ነፍሳችን!

በገና በዓል ማግሥት ጉዞ ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ አራብሳ፡፡ ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ወዲያ ወዲህ የሚለው ሳይቀር አካባቢውን ሞልቶታል። ብዙኃኑ ሕዝብ የሠልፍ አጥር ሠርቶ ታክሲ ይጠብቃል።...

አዳዲስ ጽሁፎች

የጤናው ዘርፍ ባለፉት ስድሥት ወራት

የወባ በሽታ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዋነኛ የጤናና የማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ያወጣው መረጃም 263 ሚሊዮን ሰዎች የወባ...

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በባለሙያ ዓይን

(በጎ ጎኖችና እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮች) በዮሐንስ መኮንን በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዋና ዋና ኮሪደሮችን በማዘመን ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ ያደርጋታል የተባለ ፕሮጀክት በ43 ቢሊዮን...

በልዩነት ውስጥ ሆነንም እስኪ እንነጋገር

በገነት ዓለሙ ዴሞክራሲ መብቶችና ነፃነቶች የሚሠሩበት የሕዝብ አስተዳደር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተፈጥሮ የተገኙ፣ ሰው በመሆናችን ብቻ...

ለጤናማ የትራፊክ ፍሰትና ለመንገድ ደኅንነት ቅጣት መጣል ብቻውን መፍትሔ አይሆንም!

በአዲስ አበባ ከተማ ለተሽከርካሪዎች ምቹ የሆኑ መንገዶችን እየተመለከትን ነው፡፡ ከአዳዲሶቹ መንገዶች ባሻገር አንዳንድ ነባር መንገዶች የማስፋፊያ ሥራ ታክሎባቸው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ከኮሪደር ልማቱ ጋር...

የግጭት አዙሪት ውስጥ ሆኖ የአፍሪካ ማዕከል መሆን ያዳግታል!

የአፍሪካ ኅብረት 38ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ብዙ ትዝ የሚሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እጅግ በጣም አሰልቺ፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና ታላቅ ተጋድሎ ተደርጎበት ከከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ...

አገሬ ምንተባልሽ – ልብ ያለው ልብ ይበል

በቶማስ በቀለ ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን