– የህንድ ኤምባሲ ለንግድና ለሥራ ቅጥር ቪዛ ከክፍያ ነፃ መስጠት ጀምሯል
በየጊዜው ከንግድ ማኅበራት የተውጣጡ አባላት ወደ ውጭ በመጓዝ ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮሩ ጉዞዎችን ማካሄድ እየተለመደ መጥቷል፡፡
በአብዛኛው በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ልውውጥ ላይ የሚያተኩረው የንግድ ጉዞ፣ በዓመት በአማካይ ለሦስት ጊዜ ያህል በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት በመደበኛነት ወደ ደቡባዊ ንፍቅ አገሮች ማለትም ወደ እስያ የሚደረጉ ጉዞዎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸው በተጓዳኝ፤ በአገር ውስጥና በውጭ ኩባንያዎች መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር ዕድል እየፈጠረ መጥቷል፡፡
በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ያህል ወደተለያዩ አገሮች ጉዞ እንደሚደረግ አቶ እንዳልካቸው ገልጸው፣ በተለይ ከቻይና፣ ከህንድና ከቱርክ ጋር የሚደረገው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ላይ ያተኮረ ጉዞ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በህንድ ጉጅራት ከተማ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ጉዞ ከ30 እስከ 40 ተጓዦች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በህንድ ተመሳሳይ ጉዞ ተደርጎ 23 የኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ተሳትፈው እንደነበር፣ ካኖሪያ የተባለውና የመዳመጫና የጅንስ ጨርቅ አምራች ኩባንያ ወደዚህ እንዲመጣ ማስቻሉን አቶ እንዳልካቸው ጠቅሰዋል፡፡ ሺርቫላብ ፒቲ ግሩፕ (ኤስቪፒ) የተባለው ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በተሰጠው የ50 ሔክታር መሬት ላይ በአፍሪካ ግዙፍ የተባለውን ድርና ማግ ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት መምጣቱ ሲነገርለትም ቆይቶ ነበር፡፡ ኩባንያው በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻውን ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ መንግሥት እምነት ጥሎበት የነበረ ሲሆን፣ በኩባንያው ላይ ተመርኩዞም የአምስት ዓመት ዕቅዱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይሁንና ለዘርፉ ኩባንያው ያደርጋል የተባለው አስተዋጽኦ እስካሁን ሊታይ አልቻለም፡፡ ኩባንያው ግን እስከ 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የኢንቨስትመንት ካፒታል ይዞ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይሁንና እንደ ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደዚህ መጥተው ሳይሳካላቸው መቅረቱ ሲታይ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱ ላይ የተደባለቀ ስሜት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ከህንድ ጋር ያለው ግንኙነት በአብዛኛው በንግድ ላይ ያመዘነ እንደሆነ የገለጹት አቶ እንዳልካቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው ብትን ጨርቅ ውስጥ 90 ከመቶው ከህንድ እንደሚመጣ ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ህንዶች ከኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎችን እንዲሁም ቅመማቅመሞችን በመግዛት ይታወቃሉ፡፡ ቦሎቄ፣ ዝንጅብል፣ እርድና ሌሎችም ቅመማቅመሞችን በብዛት ከኢትዮጵያ ይገዛሉ፡፡
በሌላ በኩል ግን በሁለቱ አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ላይ የሚታየው ግንኙነትን ይበልጥ ሊያስፋፋ ይችላል የተባለ አጋጣሚ ከህንድ ኤምባሲ ተሰምቷል፡፡ በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ ሰሞኑን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የህንድ መንግሥት ለኢትዮጵያ የንግድና የሥራ ቅጥር ተጓዦች ከክፍያ ነፃ ቪዛ መስጠት ጀምሯል፡፡
ይህ ዕድል ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ለጂቡቲ ተጓዦችም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚሰጥ ኤምባሲው ይፋ አድርጓል፡፡ ሁለቱ አገሮች ምንም እንኳ የዓለም የንግድ ድርጅት አባላት ባይሆኑም፣ የህንድ መንግሥት ባላደጉ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ አመልካቾች በዓለም ንግድ ድርጅት የንግድና የአገልግሎት ማዕቀፍ ውስጥ ከክፍያ ነፃ በሚሰጠው ዕድል ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሆነም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በጉጅራት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም የደርሶ መልስ ጉዞ፣ በፎረሙ ለሚኖራቸው ቆይታና የሆቴል ወጪን ጨምሮ ንግድ ምክር ቤቱ ወጪያቸውን በመጋራት 13 ሺሕ ብር በማስከፈል ሲመዘገብ ቆይቷል፡፡
በመጪው ወር በህንዷ ጉጅራት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም የግብርና፣ የኮንስትራክሽን፣ የመሠረተ ልማት፣ የምሕንድስና፣ የኢነርጂ፣ የትምህርት፣ የመረጃና ኮሙዩኒኬሽን፣ የቴሌኮም፣ የጤናና ፋርማሲ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የመዋቢያ፣ የቱሪዝምና የመስተንግዶ፣ የነዳጅ፣ የዘይትና የጋዝ ምርቶችና ውጤቶች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መረጃ ይጠቁማል፡፡