Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከ225 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሻው የመንገድ ግንባታ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን የዕቅዱን 92 በመቶ ማከናወን መቻሉን የገለጸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ከ255 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪዎች የሚጠይቁ የመንገድ ግንባታዎች አከናውናለሁ አለ፡፡

  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለሚያከናውናቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች ከሚያስፈልገው 225 ቢሊዮን ብር ውስጥ 80 በመቶው ወይም 193.9 ቢሊዮን ብሩ በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ወደ 7.2 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በጀት ለመንገድ ጥገና ከኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ የሚገኝ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቀሪው 20 በመቶው ወይም 61.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከልማት አጋሮች ከሚገኝ የብድርና ድጋፍ ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡

  ከ2008 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ያስፈልጋል የተባለው ገንዘብ ለመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ለመንገድ ልማት ዘርፍ ከወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርማሽን የዕቅድ ዘመን ለመንገድ ልማት ዘርፉ ያስፈልጋል ተብሎ ታቅዶ የነበረው 125 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ሆኖም በአምስቱ ዓመታት ውስጥ ለመንገድ ልማት የወጣው ወጪ 158.05 ቢሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡  

  እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ ለሁለተኛ የዕቅድ ዘመን ያስፈልጋል በተባለው ገንዘብ ከ16 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታና ዕድሳት ይካሄዳል፡፡ በሁለተኛው የአምስት ዓመት በመንገድ ልማት ዘርፍ ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል 1,285 ርዝመት ያላቸው የዋና መንገዶችን ማጠናከር ሥራ አንዱ ነው፡፡ 577 የዋና መንገዶች ደረጃ ማሳደግ፣ የ3,397 ኪሎ ሜትር የአገናኝ መንገዶች ደረጃን ማሳደግም በዚሁ የዕቅድ ዘመን ይከናወናሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር 5,811 ኪሎ ሜትር የአገናኝ መንገዶች ግንባታ፣ 5,063 ኪሎ ሜትር ከባድ ጥገናና የ8,006 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገዶች ግንባታም ይካሄዳሉ፡፡

  በተጨማሪም 90,000 ኪሎ ሜትር የክልልና የወረዳ ገጠር መንገዶች ግንባታ ይካሄዳል ተብሎ ታቅዷል፡፡ እነዚህ በአምስት ዓመት ውስጥ ይከናወናሉ የተባሉ ግንባታዎች የአገሪቱን የመንገድ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዕቅድ በ2007 ዓ.ም. የተደረሰበትን የመንገድ ሽፋን መነሻ በማድረግ የተሰላ ሲሆን፣ በየዓመቱ የመንገድ ልማት ዘርፉ የሚደርስበትን ደረጃ ያመለክታል፡፡ በ2007 የአገሪቱ የመንገድ ሽፋን 110,414 ኪሎ ሜትር የደረሰ መሆኑን የሚያመለክተው መረጃ፣ ይህ ሽፋን በ2008 ዓ.ም. 120,000 ኪሎ ሜትር ይደርሳል፡፡ ይህም በዓመቱ እየጨመረ ሄዶ የዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ 200,000 ኪሎ ሜትር ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ባለሥልጣኑ በዋናነት አከናውናቸዋለሁ ብሎ ያቀዳቸው ክንውኖች መካከል ለመንገድ አስተዳደር ቅድሚያ ትኩረት መስጠት የሚለው ይገኝበታል፡፡

  የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋናነት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚጠናቀቅበት፣ የዲዛይን ጥናት የተካሄደላቸውና እየተካሄደላቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚጀመርበት ይሆናል ተብሏል፡፡ የበርካታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ጥናት እንዲሁም የማስፈጸም አቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚካሄዱም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ግርማይ ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ የአዲስ መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጨማሪ በክልሎች ከተጠየቁት ፕሮጀክቶች መካከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚጀመርበት እንደሚሆንም የዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ያስረዳል፡፡

  በሁለተኛው አምስት ዓመት በጠቅላላው በፌዴራል ደረጃ የ16,500 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት አቶ አርዓያ፣ በተጨማሪም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የገጠር መንገዶችና የወረዳ መንገዶች ግንባታ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ የመንገድ ኔትወርክ ከ200 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል፡፡

  የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንድ ብሎ በተጀመረበት የ2008 በጀት ዓመትም የመጀመሪያው ዓመት እንደመሆኑ በርካታ ሥራዎች የሚከናወኑበት እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም የተቀመጡትን የመንገድ ልማት ግቦች በስኬት ለማጠናቀቅ እንዲቻል ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመቀመርና የነበሩትን ጉድለቶች በማስተካከል ወደ ተግባር ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርቷል ተብሏል፡፡

  በ2008 በጀት ዓመት የዘርፉን አፈጻጸም ለማሻሻል በዘርፉ የሚገኘውን የሰው ኃይልና የዘርፉን የአሠራር ስልት ለማሻሻል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ በስፋትና በጥራት ለማካሄድ ማቀዱንም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

  በ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የግንባታ ሥራቸውን ለማስጀመር በዕቅድ ተይዘው የነበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግንባታ ያልተሸጋገሩ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ ተብሏል፡፡ ይህም ለበጀት ዓመቱ የሚፈቀደው በጀት የቻለውን ያህል ሥራ ለማስጀመር ጥረት የሚደረግበትና የአዳዲስ የጥናት ፕሮጀክቶች ሥራ የሚጀመርበት እንዲሁም ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች በመለየት ወቅታዊና መደበኛ ጥገናና የአቅም ግንባታ ሥራዎች የሚያከናውኑበት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት በ2008 በጀት ዓመት በጠቅላላው 1,832 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገዶች ማጠናከር፣ ማሻሻልና አዲስ ግንባታ እንዲሁም በተለያዩ የጥገና ኮንትራት አሰጣጥ ዘዴዎች 19,441 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና በተለያዩ ተቋራጮችና አማካሪ መሐንዲሶች ይከናወናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ2008 የቅድሚያ ክፍያ ተፈጽሞላቸው ወደ ግንባታ የሚሸጋገሩ ፕሮጀክቶች ብዛት በቁጥር 29 መሆኑም ታውቋል፡፡

  በበጀት ዓመቱ ለተያዘው የካፒታል ፕሮጀክቶች ዕቅድ ማስፈጸሚያ በጠቅላላው 33.2 ቢሊዮን ብር የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ስቴር የፈቀደ ሲሆን፣ በተጨማሪም የተለያዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻል ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት 936.9 ሚሊዮን ብር እንደተመደበለትም ተገልጿል፡፡     

  በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መንገዶች ከብልሽት መከላከልና ወቅቱን የጠበቀ ጥገና ማካሄድ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሁሉም የአገሪቱ መንገዶች ላይ መደበኛ ጥገና እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

  በአምስት ዓመቱ ውስጥም 5,063 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው መንገዶች ከባድ ጥገና በዕቅድ የተያዘና በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ ካለው የመንገድ ልማት ጋር ተያይዞ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን አቶ አርዓያ ገልጸዋል፡፡

  የመንገድ ጥገና ሥራ የሚፈለገው ገንዘብ ደግሞ ከመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ ለመንገድ ጥገና 7.2 ቢሊዮን ብር ይፈለጋል፡፡ ለጥገና ከሚፈለገው ገንዘብ አንፃር ይህ ገንዘብ በቂ ላይሆን እንደሚችልም እየተገለጸ ነው፡፡

  በተለይ በፌዴራል ደረጃ ላሉ መንገዶች ጥገና የሚፈለገው ገንዘብና ለጥገናዎቹ የሚያስፈልገውን በጀት የሚበጅተው የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በየዓመቱ እየለቀቀ ባለው ገንዘብ መጠን መካከል ሰፊ ልዩነት በመኖሩ፣ የመንገድ ጥገናዎችን በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን ፈታኝ ይሆናል የሚል ሥጋት ማሳደሩ ግን አልቀረም፡፡

  ባለሥልጣኑ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ከመንገድ መሠረተ ልማቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አዲስ አሠራሮች እንደሚከተልም አስታውቋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት አንድም መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቀ አይደለም እየተባለ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ዋና ዋና ችግሮች ተደርገው የሚወሰዱት የዲዛይን ችግርና ወሰን ለማስከበር የሚወስደው ረዥም ጊዜ ናቸው፡፡ የኮንትራክተሮች አቅም ችግርም ሌላው የችግሩ መንስዔ እንደሆነ መገለጹ ይታወቃል፡፡

           

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች