Friday, September 22, 2023

ፌዴራሊዝምን ያሽመደመደው ብልሹ አስተዳደር ነውን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ገሚሱ ሲያንቀላፋ፣ ገሚሱ ሲያዛጋ ቆይቶ በቡድን በቡድን በመሆን ውይይት የሚደረግበት ክፍለ ጊዜ ደረሰ፡፡ የአካባቢው ሙቀት ተጨምሮበት በአንድ ላይ ታጭቆ በቀረበው የፖለቲካ የሚመስል ትምህርት ከፍተኛ ድካም የተሰማው በአዳማ ራስ ሆቴል ላይ የተገኘው የጋዜጠኞችን ቡድን በቁጥር 30 ይደርስ ነበር፡፡

በፌዴራሊዝም ሥርዓትና በአክራሪነት (ፅንፈኝነት) ላይ በንባብ መልክ የቀረበው ጥናት አይሉት የርዕዮተ ዓለም ማጥመቂያ ሰነድም፤ እንደ አዲስ የተዋቀረው የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ያዘጋጀው ነበር፡፡ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመጡ ሦስት ኃላፊዎች እየተፈራረቁ ያቀረቡት፣ ‹‹ለሚዲያ አካላት ሥልጠና የተዘጋጀ ሰነድ›› የሚለው ጽሑፍ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው ‹‹ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና የኢትዮጵያ ህዳሴ›› ሲል፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹የሃይማኖት አክራሪነት/ፅንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› ይላል፡፡

በድኅረ ደርግ በኢትዮጵያ የተቋቋመውና ቋንቋን መሠረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት በሥርዓቱ ተቃዋሚዎች ‹‹የጎሳ ሥርዓት›› እየተባለ ይብጠለጠላል፡፡ አንዳንዶቹም አምርረው ሲወቅሱት፣ የኢትዮጵያ አንድነት ለማፍረስ ሆን ተብሎ እየተተገበረ ነው እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ በተቃራኒው በቅርቡ በኦሮሚያ አካባቢ የተከሰተውን ግጭት ላይ ግንባር ቀደም ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት አቶ ጃወር መሐመድ ዓይነት ፖለቲከኞች ደግሞ፣ ‹‹ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በቂ አይደለም፣ ለኦሮሞ ሕዝብ እውነተኛ ሥልጣንና ውክልና አልሰጡም፤›› የሚል አቋም አላቸው፡፡ ይህን በአንዳንድ ሚዲያዎች ከሰጡዋቸው ቃለ ምልልሶች መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ የሥልጠና ሰነድ ውስጥ ፌዴራሊዝም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ብዝኃነትን እንዲሁም ፅንፈኝነትና አክራሪነት የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችም ከሕገ መንግሥቱ ዋና ዋና አንኳር መርሆዎች አንፃር ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ የበርካታ ጋዜጠኞችን ቀልብ የሳበው ግን የ‹‹ሕብረ ብሔራዊነት›› ጽንሰ ሐሳብ ነበር፡፡ በአብዛኛው በብሔር መደራጀትን የሚቃወሙ፣ የአንድነት ኃይሎች (ተቃዋሚዎች) ይህን ጽንሰ ሐሳብ ሲጠቀሙት የሚስተዋል ሲሆን፣ ልዩነት ላይ ማተኮር የሚቀናቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ሰነዶች ደግሞ፣ ብዝኃነት፣ ልዩነት፣ እንዲሁም ብሔር፣ ብሔረሰብ የሚሉ ቃላቶች ያዘወትራሉ፡፡

‹‹ትምክህተኝነትና ጠባብነት››

የቡድን ውይይቱ ተካሂዶ ከተሰሙ አስተያየቶች መካከል፣ ‹‹አንድ ክስተት እስኪፈጠር እየጠበቅን ፌዴራሊዝምን ማስተማር አይቻልም፡፡ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ችግር ሲፈጠር ስብሰባ መጥራትና ለማስረፅ መሞከር እሳት የማጥፋት ሥራ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ ይህ አስተያየት ከደቡብ ክልል ከመጣ አንድ ጋዜጠኛ ነበር የቀረበው፡፡ ብዙዎቹ ጋዜጠኞችም ከተስማሙባቸው አስተያየቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን በግልጽ ከመናገሩ ውጪ ግን፣ ውይይቱ ለምን አሁን እንደተጠራ አልተገለጸም፤ የመድረክ አስተዋዋቂዎችም በግልጽ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡

ሰነዱን ካቀረቡት ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው በስሜት ሲያብራሩ የነበሩና በጉዳዩም ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት የነበራቸውና በሚኒስቴሩ የመንግሥት ግንኙነት ማጠናከር ዳይሬክቶሬት ጀነራል የሆኑት አቶ ፀጋብርሃነ ታደሰ፣ አሃዳዊውን ሥርዓት ለመመለስ ይፈልጋሉ ያሉዋቸውን ‹‹የትምክህት ኃይሎችና›› የመገንጠል አባዜ ያጠቃቸዋል ያሉዋቸውን ‹‹ጠባብ ኃይሎች›› የሥርዓቱ አደጋ አድርገው ያቀርቧቸዋል፡፡

ለእግረመንገዳቸውም በቅርቡ በኦሮሞ አካባቢ ለተነሳው ግጭት ምክንያት የሆነው የሕዝብ የመብት ጥያቄ መኖሩ ሳይክዱ፤ ‹‹ጠባብ›› ኃይሎች ተጠቅመውበታል በማለት አብራርተው ነበር፡፡ ‹‹ሥርዓቱ እንዲህ በቀላሉ የሚነቃነቅ አይደለም፤ ጠንካራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ፌዴራል ሥርዓት እንዲያቀራርበን እንጂ እንዲበታትነን የመጣ አይደለም ይላሉ፡፡ አቶ ፀጋብርሃነ በቅርቡ ኦሮሚያ አካባቢ የተከሰተውን ግጭት የፌዴራል ሥርዓቱ ልዩነቱ እየሰፋ መጥቶ የአገሪቱ አንድነት አደጋ ላይ ይጥለው ይሆን ወይ የሚል የብዙዎቹ ሥጋት የኃላፊውም ሥጋት የሆነባቸው ይመስላል፡፡ ሰነዱ ላይ የሕገ መንግሥቱ ዋና ምሰሶች፤ የፌዴራል ሥርዓቱ ባህርያት እንደ መሠረታዊ ጉዳዮች የቀረቡ ቢሆንም፣ ከአብዛኞቹ አቅራቢዎች ምላሽ አሰጣጥ መረዳት እንደሚቻለው ግን የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በግጭቱ ምክንያት ይመስላል፡፡

በመሆኑም የብዝኃነትን አያያዝና የሕብረ ብሔራዊነትን መጠናከር ላይ መንግሥት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ከአቅራቢዎቹ አንዱ ‹‹ብዝኃነት የተለያዩ ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች በአንድ አስተዳደራዊ ግዛት ወይም አገር ታቅፈው መገኘታቸውን የሚገልጽ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሕብረ ብሔራዊነትን ደግሞ የብዝኃነትን መስተጋብር አድርገው አቅርበውታል፡፡

‹‹ሕብረ ብሔራዊነት የብዝኃነትን ነባራዊ ሁኔታ የሚቀበል፣ ማኅበረ ባህላዊ ልዩነቶች የሚታመኑበትና የሚከበሩበት የሕዝቦች ትስስር ነው፤›› ያሉት አቶ ፀጋብርሃነ፣ ‹‹ሕብረ ብሔራዊነት ፕሮጀክት ነው፤›› በማለት የተለያዩ አገሮች የሚከተሉትን ፖሊሲ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ ማንነቶችን በማጥፋት ወይም በመዋጥ እንዲሁም፣ የተለያዩ ማንነቶችን በማቻቻል ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት እስከ መመሥረት የሚራራቅ ፖሊሲ እንደነበራቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ፖሊሲ አውጪዎቹ የሚለያዩበት ጉዳይ ኢትዮጵያንም እንደሚመለከት ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው፣ ‹‹ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ወይም የበላይና የበታች ሆነው የቆዩ ሕዝቦች እንዴት በእኩልነት አንድ ላይ ማቆየት ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ ምላሽ የሚሻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

የእውነተኛው ሕብረ ብሔራዊነትን ግንባታ አስተሳሰብ፣ ‹‹የማንነቶች አስተዋጽኦ በጥልቀት በማመን አስተዋጽኦዋቸውን ለመጠቀም በማያቋርጥ ሒደት የሚያበቃ የጋራ ራዕይና እሴቶች የሚገነባ አስተሳሰብና ተቋማዊ ሥርዓት ነው፤›› በሚል ተርጉመውታል፡፡

በአጭሩ ብዘኃነትን ለመያዝ ሁለት ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ያሉ መሆናቸው ከአቅራቢዎች የተብራራው ሲሆን፣ አንድ ብዝኃነትን እንደ ዕዳ በማየት ለማጥፋት የሚያስችል ፖሊሲ፤ ሁለተኛው ብዝኃነትን እንደ ዕድል በማየት በአገር ግንባታ መጠቀም የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦችን ተከትለው የሚወጡ ፖሊሲዎች አብሮ ለመኖርም ለመበታተንም ምክንያት እንደሚሆኑ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል፡፡

የብዝኃነት አያያዝ ስህተት ምንጮች፣ ከጥቂት ወይም ከአንድ ማኅበረሰብ ውጪ ያሉ የተለያዩ ማንነቶች ሥርዓትን በመገንባት ሒደት ዝቅ አድርጎ ማየትና የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ የፀጥታ ሥጋት አድርጎ መመልከት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ አባባል፣ የኢትዮጵያ የብዝኃነት አያያዝ ፖሊሲ፣ ማለትም ትግበራ ላይ የዋለው የፌዴራል ሥርዓት ለሁለቱም የአስተሳሰብ ስህተቶች ቦታ የለውም የሚል ነው፡፡

እንደ የተለያዩ አገሮች

በሦስት ቡድን ተከፍሎ ውይይት ያደረገው ጋዜጠኛው በአብዛኛው ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ያነሰ እምብዛም አልነበረም፡፡ አንድ ተሳታፊ በተለይ ‹‹ወርቅ የሆነ ሕገ መንግሥት አለን፣ አተገባበር ላይ ግን ችግር አለ፤›› ብለዋል፡፡ የብዙዎቹ ጥያቄ መሬት ላይ ባለው አተገባበሩና ፈጻሚዎቹ ላይ ይመስላል፡፡

አብዛኞቹ ድምዳሜዎችና አስተያየቶች ከላይ ወደታች የተሰገሰጉ የመንግሥት ሹመኞች ሥርዓቱን በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ አደጋ ላይ ጥለውታል የሚል ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ሲንቀሳቀስ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የሚሸጋገር ያህል ተለያይተናል በሚልም የቀረበ አስተያየት ነበር፡፡

አንዳንድ አካባቢዎችን በምሳሌነት የጠቀሰው አንድ ጋዜጠኛ፣ አንዳንድ ክልሎች የክልሉን ቋንቋ ካላወራህ የመኝታ አልጋ የማይገኝበት ሁኔታ አለ ብሏል፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ ከሰፈረው አንድ ዜጋ በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ጨርሶ የሚፃረር አካሄድ ወዴት ያመራናል ሲልም ይጠይቃል፡፡ በተያያዘም አሁንም የኦሮሚያን የቅርብ ክስተት ጠቅሶ፣ በአንድ ክልል ሕዝብ የሚቀርብ ቅሬታ የሌላው ክልል ነዋሪ አያገባኝም ዓይነት ስሜት ማንፀባረቁንም ተችቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ በአትሌቲክስ ውድድር ሳይቀር የአንድ ሰው የክልሉ ሰው ካላሸነፉ በስተቀር አገሩ እንዳሸነፈ መስሎ እንደማይሰማውም አቅርቦ ነበር፡፡ ‹‹እኛ ያለችን አንዲት አገር ነች፡፡ አሁን ግን ስንገናኝ እንኳን ከተለያዩ አገሮች የመጣን ያህል እየተሰማን ነው፤›› በሚል አስተያየቱን የቋጨው ጋዜጠኛ፣ ለአገር አንድነት አንድ ብሔራዊ መዝሙር መዘመር፣ አንድ የጋራ ባንዲራና የግዛት ካርታ መኖር በቂ አይደለም ብሏል፡፡

ሌላም ቡድን አቅራቢ በተለይ የደቡብ ክልልን ጠቅሶ፣ በዞን የተደራጁት የብሔረሰቦች አስተዳደሮች፣ በዘመድ አዝማድ እየተሳሳቡ አስተዳደሩን የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ መኖሩን አቅርቧል፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄ ያነሳ ሰውም ተባብረው ያጠፉታል የሚል ቅሬታ አንስቷል፡፡

በብዙዎቹ ጋዜጠኞች የተንፀባረቀው ጉዳይ በተለይ ታች መስተዳደሮች የተቀመጡ የመንግሥት ሹመኞች ሥርዓቱን የሚፃረር ሥራ እየሠሩ እንደሆነ፣ ይኸውም ለከፍተኛ ብልሹ አስተዳደር ምክንያት መሆኑን፣ ተዓማኒነት ያለው ጥቆማ ሲደርስም መንግሥት ዕርምጃ እንደማይወስድ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ እየተከሰተ እንደሆነ ሳይደብቁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥርዓቱን የተጠበቀውን ማምጣት ቀርቶ ያልተጠበቀውን ሥጋት እየፈጠረ ነው፤›› በሚልም የመበታተን አደጋ እንዳይመጣ ጥንቃቄ እንዲደረግ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ሚዲያውን ለቀቅ እንዲያደርገውና ለጋዜጠኛው ጥበቃ እንዲያደርግለት ሥርዓቱን እንዲፈትሽ በአማራጭነት አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዲወስድና በአቅመ ቢስ ሹማምንቶቹ ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ የሚልም በመፍትሔነት ቀርቧል፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞች የመንግሥት ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆን፣ የአለቆቻቸው ሎሌ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያ እንዲሆን ያደረገው መንግሥት ራሱ ነው፡፡ የችግሩ አደጋ ለእኛ እየታየን ነው፤›› በሚል አንድ አስተያየት ሰጪ አቅርበዋል፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞችና የመንግሥት ኃላፊዎች በአንዳንድ የአገር ጉዳዮች ላይ ሚዲያው የጋራ አቋም መያዝ አለበት በሚል አስተያየትም ቀርቧል፡፡ በተቃራኒው ሚዲያው የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚንሸራሸሩበትና የበለጠውን ነጥሮ የሚወጣበት እንጂ አቋም የሚያዝበት መድረክ እንዳይሆን በሚል የተነሳው ነጥብም መጠነኛ ክርክር አስነስቷል፡፡ በአብዛኞቹ ችግሮች ሚዲያውን ነፃ ማድረግ፣ የመንግሥትን የፕሮፖጋንዳ ማሽን ከመሆን እንዲላቀቅ፣ ነፃ ሚዲያውም አሉባልታን ከመዝገብ ወጥቶ ድርሻውን ሊጫወት ይገባል በሚል የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -