Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከግብፅ ጋር የተጀመረው የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ብልኃት ይታከልበት!

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከግብፅ በኩል የተለያዩ ወቅቶችን ተንተርሶ የሚያገረሸው በሽታ ሰሞኑን ጀማምሮታል፡፡ ‹‹ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ›› የሚባለው ብሒል በግብፆች በኩል የተለመደ ሥልት ሆኗል፡፡ በግብፅ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ትንፋሽ እየወሰዱ የሚያካሂዱዋቸው በተንኮል የተሸረቡ ሴራዎች፣ መልካቸውን እየቀያየሩ መከሰታቸው የተለመደ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በኩል ወዳጅነትን ላለማበላሸት ሲባል በተቻለ መጠን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተደረገው በሙሉ የሚያስመሰግን ሲሆን፣ ነገሮች ገጽታቸውን እየቀያየሩ ሲከሰቱ ግን ብልጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብልጠት ደግሞ በተራ ጮሌነት ሳይሆን በብልኃት መታጀብ ይኖርበታል፡፡

በቅርቡ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ ሚኒስትሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች በግድቡ ግንባታ ላይ ጥናት እንዲያደርጉ ተወስኗል፡፡ ግብፅ በሦስቱ አገሮች ውይይት ላይ የፖለቲካ ውይይት መደረግ አለበት በማለት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጥነት ሥጋት እንደሆነባት አሁንም በአፅንኦት አስታውቃለች፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል የፖለቲካ እርግጠኝነት እንዲኖርም ትፈልጋለች፡፡ ለዚህ ማጠንጠኛ የሚሆናት ደግሞ የጥናቱ ውጤት ይፋ ሳይሆን ከወዲሁ የግድቡን የውኃ ሙሌት ማስቆም ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የግብፅ መገናኛ ብዙኃን በአንድ ላይ በመሆን ዘመቻውን አጣጡፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት ላለመጀመር መስማማቷን አውጀዋል፡፡ ይህ ዓይነቱን የሚዲያ ዘመቻ ከበስተጀርባ የሚመራው የፖለቲካ ኃይል እንዳለ አያጠራጥርም፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ መሰሪ ደባ ነው ብልኃት የሚያስፈልገው፡፡

ገና ከጅምሩ ከዓመታት በፊት በዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድር ላይ፣ ግብፅ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልን በተመለከተ በፍፁም እንደማትቀበል በማስታወቅ ከድርድሩ መውጣቷ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ መሪነት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ (CFA) በአብዛኞቹ አገሮች ከፀደቀ በኋላ፣ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ጀምራለች፡፡ በግብፅ አብዮት ምክንያት ወደ ሥልጣን የመጡት የቀድሞው ጄኔራል አብዱልፈታህ አልሲሲ ሰላማዊ መንገድ በመከተል ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር በመርህ መገለጫ ስምምነት (Declaration of Principles)፣ አገራቸው ግብፅ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍሉን በይፋ እንደምትቀበል መስማማታቸው ለኢትዮጵያ ትልቁ ስኬት ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ያስገኙት ውጤት ነው፡፡ ግብፅ የዓባይ ውኃ የሁሉም ተፋሰስ አገሮች የጋራ ሀብት መሆኑን እንድታምን ተገዳለች፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥረት ወደፊትም መጎልበት አለበት፡፡

ማንም የተፋሰሱ አገር ከዚህ በፊት በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት ለመጀመር ከፈለገ ከግብፅ ፈቃድ ለማግኘት ይገደድ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ዓይነቱ የግብፅ ፈላጭ ቆራጭነት አብቅቶ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር እንደሆነች፣ በሉዓላዊነቷም የተፈጥሮ ሀብቶቿን የመጠቀም መብቷ በመርህ መገለጫው ስምምነት ሳይቀር መረጋገጡ ትልቅ ስኬቷ ነው፡፡ ማንኛውም የዓባይ ተፋሰስ አገር ጉልህ ጉዳት ሳያደርስ ውኃውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብት ያገኘውና ግብፅ ጭምር የተስማማችበት የመርህ መገለጫ ስምምነት የተረጋገጠው በኢትዮጵያ ጥረት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በከባድ ፈተና የታጀቡ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ተደርገዋል፡፡ ብልኃት በተሞላበት ጥበብም ውጤት ተገኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ መሪዎች በተስማሙበት የመርህ መገለጫ ስምምነት አንቀጽ 5 ላይ የተቀመጡት ነጥቦች የኢትዮጵያን ጥቅም የማስከበር አቅም ቢኖራቸውም፣ ከግብፅ ጋር በብርቱ የሚያታግሉ ናቸው፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ የጥናቱን ውጤት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የግድቡን ግንባታ እያከናወኑ በጥናቱ ውጤት መሠረት የመጀመሪያውን ሙሌት ማከናወን የሚሉ ነጥቦች ተካተዋል፡፡ እነዚህ ነጥቦች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ ቢሆኑም፣ እንደ ሌሎቹ ነጥቦች በቀላሉ የማያስማሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ የግድቡ ግንባታና ጥናቱ ጎን ለጎን መከናወናቸው በስምምነቱ ላይ የሠፈረ ሲሆን፣ የውኃ ሙሌቱም የግንባታው አካል ሆኖ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውን ስትሰጥ፣ መውሰድ የምትፈልገው ሊኖር እንደሚችል ብልኃት በተሞላበት መንገድ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ግብፅ ከኢትዮጵያ መውሰድ የምትፈልገው ዋነኛ ጉዳይ በግድቡ የውኃ ሙሌት ላይ እያጠነጠነ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው የፖለቲካ መሳሳብ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ ብልኃት ያስፈልገዋል፡፡

በቅርቡ በሦስቱ አገሮች በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሁለቱ ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎች በመጪው ጥር መጨረሻ ላይ ጥናታቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መሀል የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮችና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት የታላቁን ግድብ ግንባታ እንቅስቃሴ እንዲጎበኙ ኢትዮጵያ ጥሪ አድርጋለች፡፡ ይህ የሚደረገውም ኢትዮጵያ ከማንም ደብቃ የምትሠራው እንደሌለ ለማሳየትና እምነት ለመፍጠር እንደሆነ በመንግሥት ተነግሯል፡፡ ይሁንና በግብፅ ፖለቲከኞችና በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የተጀመረው አዲሱ ዘመቻ ክፍተቶችና ደካማ ጎኖች ላይ የሚያነጣጥር በመሆኑ፣ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ያሻዋል፡፡ አርቆ አስተዋይነትና ብልኃት የተሞላበት ጥበብ ያስፈልጋል፡፡

የግብፅ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙኃን እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች በፈረሙት የመርህ መገለጫ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ የጥናት ውጤቱን እንደምትቀበል፣ የመጀመሪያው የውኃ ሙሌትም በስምምነቱ መሠረት እንደሚከናወን ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በግልጽ የተነገረው ደግሞ የግድቡ ግንባታ ቀጥሎ ጥናቱ ጎን ለጎን እንደሚከናወን ነው፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙኃን ይህንን ዕውነታ ሆን ብለው እያድበሰበሱ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መክፈታቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባትም የግድቡን ግንባታ ማቀላጠፍ ይመረጣል ብሏል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ግብፆች የተለመደው የአሻጥር ሥራ ውስጥ ገብተው አላስፈላጊ ተግባራትን እንዳይፈጽሙ፣ የተፈጠረውን የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ይህም በብልኃት ይታጀብ፡፡

በአጠቃላይ ታሪክ እንደሚነግረን በዓባይ ጉዳይ ሁሌም ጠንቅ በመሆን የምትታወቀው ግብፅ፣ በጦር ኃይል ከማስፈራራት ጀምሮ በተለያዩ ሴራዎች ኢትዮጵያን ተፈታትናለች፡፡ ሰሞኑን የግድቡ ውኃ ሙሌት ከጥናቱ ውጤት በፊት አይጀመርም በማለት ያሰራጨችው ዘርፈ ብዙ ፕሮፓጋንዳ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ መደናገጥና ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር፡፡ እንደ ሞራል ክስረትም ተቆጥሯል፡፡ ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ሀብት ከመሆንም በላይ የአገሪቱ ቅርስ ስለሆነ፣ ሁሌም በከፍተኛ ንቃትና በተጠንቀቅ ጉዳዮችን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ግብፆች የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻቸውን ጭምር ማብረጃ የሚያደርጉበት በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ከመቼውም በላቀ ሁኔታ ንቁ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው ከግብፅ ጋር የተጀመረው አዲሱ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ብልኃት የሚያስፈልገው፡፡   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...