Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ኩባንያ የ285 ሚሊዮን ዶላር ሥራ ተነጠቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ፕሮጀክቱ ለሌሎች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተሰጠ

በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች በየጊዜው የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችለውን ፕሮጀክት የተረከበው ኃይድሮ ቻይና፣ ባስመዘገበው ደካማ ሥራ አፈጻጸም ፕሮጀክቱን ተነጠቀ፡፡

የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሥራ አመራር ቦርድ፣ የኃይድሮ ቻይናን ሥራ አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ ፕሮጀክቱ እንዲነጠቅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዙሪያዋ በሚገኘው ኦሮሚያ ልዩ ዞን 12 ከተሞች በየጊዜው የሚከሰተውን ኤሌክትሪክ መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት ዕቅድ ነድፏል፡፡

ይህ ዕቅድ ተግባራዊ የሚደረገው በሦስት ዙር ሲሆን፣ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ በሚል ዝርዝር የአፈጻጸም ዕቅድ ወጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2017 ድረስ ተግባራዊ ለሚደረገው የአጭር ጊዜ ዕቅድ 285 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ሁሉንም ዕቅዶች ለማስፈጸም 1.067 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ሰኔ 2007 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል፡፡

በዚህ ዕቅድ መሠረት የቻይናው ኩባንያ ኃይድሮ ቻይና የአጭር ጊዜ ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስፈልገውን በጀት ይዞ እንደሚመጣ መተማመኛ በማቅረብ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የግንባታ ውል በመፈረም ሥራ ውስጥ ገብቷል፡፡

ነገር ግን ይህ የቻይና ኩባንያ አመጣለሁ ያለውን ብድር ማምጣት ካለመቻሉም ባሻገር፣ በአጠቃላይ ያካሄደው የሥራ አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ከዚህ ፕሮጀክት ውጪ እንዲሆን የሥራ አመራር ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ፣ ኃይድሮ ቻይና ሥራውን መነጠቁን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ሥራ አመራር ቦርዱ፣ ከዚህ ውሳኔ በተጨማሪ ታኅሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሚ ተሰብስቦ ይህ ፕሮጀክት በአስቸኳይ መካሄድ ያለበት በመሆኑ፣ ለሌላ የቻይና ኩባንያ ዳንግ ፉንግ እና ለደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ኮምኮ እንዲሰጥ ውሳኔ ማሳለፉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ባሳለፈው ውሳኔ ዳንግ ፉንግ እና ኮምኮ በጋራ በሚፈጥሩት ጥምረት ሥራውን ያከናውናሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ኩባንያዎች የግንባታ ውል የሚፈራረሙት ከራሳቸው የገንዘብ ምንጭ ብድር ማምጣት ከቻሉ ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች በዋናነት የሚያካሂዱት ሥራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ማሳደግ፣ ያረጁ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን፣ ከፍተኛ ቮልቴጅ በሚያስተላልፉ መስመሮች መተካት እንደሆነ ታውቋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ለእነዚህ ኩባንያዎች ሊሰጥ የቻለው በድርድር አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት በመሆኑ ይህ ሥራ እንዲከናወን የሚፈለገው ከውጭ በብድር በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ በመሆኑ ነው፡፡

አገሪቱ ይህንን በጀት የምትመድብ ቢሆን፣ ዓለም አቀፍ ጨረታ ይወጣ እንደነበር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

የቻይና ኩባንያ ዳንግ ፉንግ የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኤሌክትሮክና ኃይድሮ ሜካኒካል ግንባታዎችን ያካሄደ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኮምኮ ለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ግንባታዎች አዲስ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች