በአዲስ አበባ ከተማ 60 ሺሕ ተመልካች የሚይዘው ስታዲየም ግንባታ በ45 ቀናት ውስጥ ግንባታው እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ አጠገብ በ2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባውንና ‹‹አደይ አበባ›› የሚል መጠርያ ያለውን ብሔራዊ ስታዲየም ከሚገነባው የቻይናው ስቴት ኮንስትራከሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ታኅሳስ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡ በዕለቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የስታዲየሙ ግንባታ በሁለት እርከን የሚከናወን ሲሆን፣ መንግሥት በመደበው 2.4 ቢሊዮን ብር ግንባታው ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴንና የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር ሶንግ ሱዶንግ ናቸው፡፡ የአዲሱ ስታዲየም ግንባታው በ48.8 ሔክታር መሬት ላይ የሚከናወንና የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የሚያስቀምጡትን ደረጃ የሚያሟላ መሆኑ ታውቋል፡፡