ሳላማንደር ይባላሉ፡፡ ረዥምና ሸንቃጣ አካል ሲኖራቸው አካላቸው ላይ ምንም ቅርፍ አይገኝም፡፡ እግርና ጅራትም አላቸው፡፡ እግራቸውም እንደ እንሽላሊት ዓይነትና በደንብ ያልዳበረ ነው፡፡ በአመጋገባቸው ሥጋ በል ናቸው፡፡ ርባታቸው እንደ ሴሲሊያን ውስጣዊ ፅንሰት በማካሄድ ነው፡፡ የዕጭ ዕድገት ደረጃቸው በውኃ ውስጥ ይካሄዳል፡፡ የጉልምስ ዕድገት ደረጃቸው ደግሞ የብስ ላይ ይታያል፡፡ የተለያዩ ዓይነት የመተንፈሻ ክፍለ አካል በተለያየ የዕድገት ደረጃቸው ላይ ያሳያሉ፡፡ በዕጭ የዕድገት ደረጃ በስንጥብ፣ በጉልምስ የዕድገት ደረጃ ደግሞ በሳንባ የሚተነፍሱ ይሆናሉ፡፡
ሳላማንደር የእንቁራሪት አስተኔ ዝርያዎች ውስጥ ከሚካተቱት አንዱ ሲሆኑ፣ ከእንቁራሪት ጋር ሲተያዩ በጭራቸው፣ ከሴሲሊያን ጋር ሲነፃፀሩ በእግራቸው የሚለያዩ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ቅርፀተ ለውጥ የሚያካሂዱ ሲሆን፣ በዕጭነት ጊዜያቸው በስንጥብ እየተነፈሱ በውኃ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በጉልምስ (ሙሉ አካል በሚይዙበት) ጊዜ ደግሞ በሳንባ እየተነፈሱ ረጠብ ያለ ፅንሰት ያካሂዳሉ፡፡ ይህም ማለት የወንዱ ነባዘርና የሴቷ እንቁላል የሚገናኙት ሴቷ አካል ውስጥ ነው ማለት ነወ፡፡ በአንፃሩ በእንቁራሪቶች ይህ የሚሆነው ውኃ ውስጥ ነው፡፡ ይህም ውጫዊ ፅንሰት ይባላል፡፡
ሳላማንደርን አንድ በጣም ለየት የሚያደርጋቸው ነገር አላቸው፡፡ ይኼውም አክዞሎትል (Axolotl) የሚባለው ዝርያቸው ነው፡፡ ይህ ዝርያ በእጭ የዕድገት ደረጃ እያለ (ጉልምስነት ላይ ሳይደርሱ) መራባት የሚችል ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው እንስሳት የሚታይ ባለመሆኑ አስደናቂ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004)