Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዘንድሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ

ዘንድሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ

ቀን:

በኢትዮጵያ አገር አቀፍ ፈተና መስጠት ከጀመረበት 1938 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ ጊዜው ሁኔታ የሚለዋወጡ የፈተና አስተዳደር ሥራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ከሚሄደው የተማሪ ቁጥር አንፃር በየወቅቱ የሚሰጡ ፈተናዎች በሙሉ ተመሳሳይ የፈተና አስተዳደር ሒደትን አይከተሉም፡፡ የኅትመት ሒደቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ያሉ የፈተና ዝግጅት ሒደቶችን ጨምሮ ያሉ ሒደቶች ፈተናው ተጠናቆ የመስጠት ያህል ቀላል እንዳልሆነም መገመት ይቻላል፡፡ የፈተናው ዝግጅትና ኅትመት ተጠናቆ፣ በየፈተና ጣቢያዎች ለተፈታኞች እስኪሠራጭ ድረስ እጅግ በጣም ሰፊና አድካሚ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ካሉት ተጨባጭ ነጥቦች አንፃር በአገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት፣ ኅትመትም ሆነ አሰጣጥ ላይ ተዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ጉዳዮች ተፈጥረዋል፡፡ የተማሪ ቁጥር መጨመር፣ የበጀት ዕጥረት፣ ለፈተና አስተዳደር ሒደቱ ምቹ የሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በበቂ ሁኔታ በየክልሉ አለመመቻቸትና የመሳሰሉት ሊነሱ የሚገባቸው የፈተና አስተዳደር ችግሮች ናቸው፡፡

ከምንም በላይ ግን የፈተና ሥራውን በባለቤትነት ስሜት በመፈጸምና በማስፈጸም ጉዳይ ላይ ያለ የአመለካከት ችግር መኖሩ በዋናነት መታረም ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ይወሳል፡፡ የፈተና ዝግጅት ሒደቱ የሚጀመረው ትምህርት ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት በሚገኙት የክረምት ጊዜያት ነው፡፡ ባለሙያዎች ጥምረት በቂ ጊዜ ተወስዶ በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት የተዘጋጀው ፈተና የመጨረሻ ቅርፁን እንዲይዝ ይደረጋል፡፡

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን የአሥረኛ ክፍል (የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ) ፈተና ወንድ 648,837፣ ሴት 573,920 በአጠቃላይ 1,222,757 ተማሪዎች፣ እንዲሁም የአሥራ ሁለተኛ ክፍል (የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን) ሴት 128,628፣ ወንድ 155,930 በአጠቃላይ 284,558 ተማሪዎች እንደሚፈተኑ አገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡

ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያና ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ተፈታኞች የሚውሉ ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ የፈተና ወረቀቶች ተዘጋጅተው ለሥርጭት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ፈተናው ታትሞ፣ ተደልድሎ፣ ሌሎችም የቅድመ ዝግጅቶች ሥራዎች ተጠናቀዋል፡፡ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ደኅንነቱ ተጠብቆ በመላ አገሪቱ ከፈተናው ቀን በፊት ይደርሳል የሚል እምነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡

‹‹የሚሠማራውም የሰው ኃይል ለዚህ ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ ነው፡፡ የተፈታኞችም ምዝገባ ከወዲሁ ተከናውኗል፡፡ አዲስ አበባ ተፈታኞችን በኦንላይን ነው መዝግበን የጨረሰነው፡፡ ይህም አንድ ዕድገት ነው፡፡ ካለፉት ዓመት ዘንድሮ የተሻለ ነገር ተሠራ የተባለውም ተማሪዎቹን በኦንላይን መመዝገብ በመቻሉ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን አካሄድ በሚቀጥሉ ዓመታት በስፋት ሥራ ላይ ሊውል ይችላል፡፡ አድሚሽን ካርድም እየተሠራጨ ሲሆን፣ በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ሁሉም ተፈታኞች እጅ ይገባል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

የክልሎችን ተፈታኞች በኦንላይን (ድረ ገጽ) ለመመዝገብ የተደረገው ሙከራ በሁለት ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አንደኛው የመሠረተ ልማት ችግር ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት በዚህ አሠራር ሥልጠና የወሰዱት ባለሙያዎች ደፍረው መግባት ላይ ወይም ትምህርት ቤቶቹን አስተባብረው መግባት ላይ ችግር በመፈጠሩ ነው፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በዚህ ዓመት ከግንቦት 22 ቀን እስከ ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ፣ ከግንቦት 26 ቀን እስከ ግንቦት 29 ቀን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ፣ ከሰኔ 11 እስከ ሰኔ 13 ቀን ድረስ የስምንተኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተናዎችን ይሰጣሉ፡፡

በእነዚህም ቀናት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ወደ 4,050 የፈተና ጣቢያዎች እንደተዘጋጁ፣ ከእነዚህም ውስጥ 2,850 የፈተና ጣቢያዎች ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የሚውሉ ሲሆን፣ የቀሩት 1,200 የፈተና ጣቢያዎች ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የሚውሉ ይሆናሉ፡፡ ሌላ 50,000 መምህራንም በፈተና ጣቢያዎች ኃላፊነት፣ በሱፐርቫይዘርነትና በፈታኝነት በመላ አገሪቱ ውስጥ ይሠማራሉ፡፡

ከዚህም ሌላ የፈተናውን ሒደት፣ አስተዳደሩንና ደኅንነቱ የሚገመግምና ለሚቀርቡ የግብዓት ጥያቄዎች ወዲውያኑ አፋጣኝ መልስ የሚሰጥ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ግብረ ኃይሉ የሚመራው በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሲሆን፣ በግብረ ኃይሉም ከታቀፉ አካላት መካከል ኤጀንሲው፣ መምህራን ማኅበር፣ ፖሊስ፣ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በፈተናው ለሚሠማራው የሰው ኃይል አበል ክፍያና ለሌሎች ጥቃቅን ሥራዎች ማከናወኛ የሚውል 150 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

በዘንድሮ ፈተና ላይ ዓምና የታዩት ልዩ ልዩ ዓይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የፈተና ወረቀቶች በሸራ ከተከተቱ በኋላ ሸራው በጓጉንቸር ይቆለፋል፡፡ ጓጉንቸሩ ተከፍቶ ወረቆቶቹ የሚቆጠሩት ከፈተናው በፊት ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በ2008 ዓ.ም. ዋጋ ያስከፈለ ሲሆን፣ የታሸገው ከረጢት ተፈትቶ ወረቀቶቹ የሚቆጠሩት በፈተናው ዕለትና በተፈታኙ ፊት እንዲሆን ተደርጓል፡፡  

የዘንድሮ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ተፈታኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተፈታኞች ጋር ሲነፃፀር በ39,515፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ደግሞ ካለፈው ዓመት ተፈታኞች ጋር ሲነፃፀር በ105,939 ከፍ ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...