Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊልሂቅ ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ  (1927- 2010)

ልሂቅ ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ  (1927- 2010)

ቀን:

በ1920ዎቹ ዓመታት በማርክስ ጋርቬይ መሪነት ተራማጅ አስተሳሰብ ያራምድ በነበረው የሐርለም ፓን አፍሪካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከነበሩት አንዱ ራባይ አርኖልድ ጆሹዋ ፎርድ ይጠቀሳሉ፡፡ በማርከስ ጋርቬይ የተመሠረተው ዩኒቨርሳል ኔግሮ ማኅበርም የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆነው ከማገልገላቸው ባሻገር ‹‹ወደ አፍሪካ እንመለስ›› በተሰኘው ንቅናቄ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ በዓል ሲከበር የሙዚቃ ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡

በዓመቱ በ1924 ዓ.ም. ሚኞን ፎርድ የራባይ ፎርድን ዳና ተከትለው ኢትዮጵያ በመምጣት የራባይ ፎርድ ፕሮጀክቶች ጸሐፊ ሆነው በሚያገለግሉበት አጋጣሚ ነበር ትዳር መሥርተው ጎጆ ቀልሰው የኋለኛው ባለታሪክ ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ የተወለዱት፡፡ ይሁን እንጂ በ1928 ዓ.ም. በጣልያን ወረራ መባቻ ላይ ራባይ ፎርድ በፅኑ በመታመማቸው ሕይወታቸው ከማለፉ አስቀድሞ ራባይ ፎርድ የአዲሲቱን አገራቸውን ዕጣ ፈንታ በጋራ ለመቋቋም ባለቤታቸው ሚኛን ፎርድ ኢትዮጵያን ጥለው እንዳይሄዱ አደራ ብለው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ሚስስ ፎርድ ወረራውን በመቃወም ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ከድል በኋላም ከካረቢያን ጓደኞቻቸው ጋር በመተባበርም ልጃቸው ትምህርት ሀሁን የጀመረበት ‹‹ቤተ ኡራኤል›› ቆይቶ ልዕልት ዘነበ ወርቅ የተሰኘውን ትምህርት ቤት ኢትዮጵያ ድል በኋላ ለማቋቋም ሚስስ ፎርድ የትውልድ ሰንሰለት በትምህርት፣ በሥነ ምግባር፣ በሥራ ወዳድነት እንዲታነፅ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉና ትውልድ የገነቡ እናት ነበሩ፡፡ ሁለቱም ወንድ ልጆቻቸው ዮሴፍና ዓቢይም ይህንኑ የሕይወት ቅርስ በማንገብ ሕይወታቸውን በሙሉ ለማስቀጠል ችለዋል፡፡

የፎርድ ቤተሰብ መሠረታዊ እምነት የአፍሪካን ባህሎችና ማንነቶችን ከሁሉም አንፃር አጉልቶ ማንፀባረቅ ማክበር ነው፡፡ ቤተሰቡ በዘመናት ውስጥ ዓይነተኛ አስተዋጽዖን በትውልዶች መካከል አበርክተዋል፡፡ ሚኞን፣ አርኖልድ፣ ዮሴፍና ዓቢይ በማኅበረሰብ ውስጥ ያበረከቱት ተግባር ሕያው ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ፕሮፌሰር ዓቢይ እንደ ሊቅነታቸውና ምሁርነታቸው በትሁት ሰብእና በአስተዋይ ህሊና ልምዳቸውን አካዴሚያዊ ተቋማት እንዲመሠረቱ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ በማድረግ ለአፍሪካውያን በአገራቸውም ሆነ በድዮስጶራ ባሉበት ዐቢይ ተግባርን አከናውነዋል፡፡ ለተማሪዎች አርአያ በመሆን ኪነ ጥበባዊ ተግባራትን ለፊልም ሠሪዎች፣ ለሙዚቀኞች፣ ገጣሚዎችና ሠዓሊያን አጋርተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዓቢይ የፓን አፍሪካኒዝም ውርስን (ሌጋሲ)  ለማስቀጠል ለዚህም የሚኞን ፎርድ ፋውንዴሽን በመመሥረት የእናታቸውን የሚስስ ፎርድ ሕይወትና በኢትዮጵያ ያከናወኑት ሥራዎች እንዲታወስ በማድረግ ዓቢይ ተግባር አከናውነዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዓቢይ በክርስትና ስማቸው ‹‹ወልደ አብርሃም›› መንፈሳዊ፣ ምሁራዊና የፈጠራ ሕይወታቸው የብዙ ዓለማት ሰው እንደነበሩ ይመሰክራሉ፡፡ ከባርቤዶስ የዘር ግንድ ከተመዘዙትና የፓን አፍሪካዊ ታጋይ ከነበሩት ወላጃቸው በአዲስ አበባ ከተማ ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 1927 ዓ.ም. የተወለዱት ዓቢይ ፎርድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት

በሊሴ ገብረማርያም ሲሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በአሜሪካ አጠናቀዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል በአውሮፕላን አብራሪነት ሠልጥነው አገልግሎት መስጠታቸውንም ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በይቀጥላልም ኒውዮርክ ከሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ሲመረቁ፣ ወደ ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በማምራትም የራዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የፊልም ትምህርት ዘርፍን በማቋቋምና መሥራች የፋካልቲ አባል በመሆን በአካዴሚያዊ ልቀታቸውና በአስተማሪነት ብቃታቸውምፕሮፌሰርነትን አግኝተዋል፡፡ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችን ከመሥራት ባሻገር በተጨማሪም ዕውቅና በተቸራቸው የጥናትና ምርምር ኅትመቶች ላይም አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በ1998 ዓ.ም. ከጡረታ እስተገለሉበት ድረስ ዓቢይ ሁለት ጊዜ የፉልብራይት ስኮላር በመሆን  በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶና ምርምር ሠርተዋል፡፡ አርባ ዓመታት የዘለቀው የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ቢያበቃም ልሂቅ ፕሮፌሰር (ፕሮፌሰር ኤሚራይተስ) ዓቢይ ፎርድ ግን ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር አዲሱን የሕይወታቸውን ምዕራፍ ያጠናከሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲቋቋም ትልቅ ሚና በመጫወት ነው፡፡ የፋኩሊቲው ዲን በመሆንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሠልጠኛ ተቋም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲቀላቀል በትጋት ሠርተዋል፡፡

 የፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ ሌላው ላቅ ያለው ተግባራቸው ገጸ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ለማዋቀር እንዲያግዝ ወደ ተለያዩ ተቋማት የተደረጉትን የጉብኝት ጉዞዎች የልዑካን መሪ በመሆን መሥራታቸው፣ በ2000 ዓ.ም. ደግሞ በጓደኛቸውና የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባቸው በነበረው በስኩንዱር ቦጎሰያን ስም የተሰየመውን የኪነ ጥበባት ኮሌጅ እንዲቋቋም የመማክርት ጉባዔውንም ሆነ የማኔጅመንት ቡድኑን ሲመሩ መቆየታቸው ነው፡፡ በመቀጠልም ኵቤክ ከሚገኘው የካናዳ ፊልም ተቋም ጋር ያላሰለሰ ጥረትና ግንኙነት በመፍጠር ዘለቄታማ የሆነና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፊልም ፕሮግራም መከፈት ተቋማዊ ሽርክና ለመክፈት እንዲቻል አድርገዋል፡፡

በ2004 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበባትና ዲዛይን የትምህርት ዘርፍ ሥር የመጀመሪያው የፊልም ፕሮዳክሽን ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲቋቋም ፋና ወጊ ብቻ ሳይሆኑ ተጋባዥ ፕሮፌሰር በመሆንም የተለያዩ ኮርሶችን በመስጠት ለበርካታ ፊልም ሠሪዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን መቻላቸውም ይወሳል፡፡

ሊቀ ጠበብቱ ዓቢይ ከሙያዊ ሕይወታቸውና ካበረከታቸው ሥራዎች ባሻገር የተዋጣላቸው የሙዚቃ ሰውም ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ ውስጥ ሙዚቃ በሚደገስበት ቦታ ሁሉ ዓቢይን ማግኘት የሠርክ ተግባር ነበር ይባላል፡፡ ዕውቅናን ካተረፉት ሙዚቀኞች ከነአበጋዙ ክብረ ወርቅ ሺዮታና ሔኖክ ተመስገን ጋር ሙዚቃ መጫወት ለልሂቁ ዓቢይ የሚዘወተር ነበር፡፡ በአሜሪካ ቆይታቸውም ትላልቅ ከበሮዎችን ጭነው ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኘው ማልኮም ኤክስ መናፈሻ  በኩባውያን ካሪቢያውያን እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች የታጀበ የሙዚቃ ድግስ ላይ መሳተፍም ለሙዚቃ ሰው ዓቢይ የዘወትር ልማድ እንደነበር ይነገራል፡፡

ዕውቀትን ልምድን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል ዋሽንግተን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውም ሆነ በአዲስ አበባ ባለው ስቱዲዮአቸው ሙዚቀኞችን፣ ገጣሚዎችንና አርቲስቶችን ለበርካታ ዓመታት በመጋበዝና መድረክ በማዘጋጀትም ይታወቃሉ፡፡ ‹‹ፒያኖ በመጫወት የሚያገኘው እርካታው እንዲሁም ኩንጋ እና ጀምቤ በመምታት የሚያወጣው ዜማ ፍጹም የሆነ ደስታን ያጎናፅፉት ነበር፤›› የሚሉት አድናቂዎቻቸው፡-

‹‹ረቂቋ ድምፅ ውቢቷ ሙዚቃ

 ዓቢይ ነው ጌጧ›› ብለው ገጥመውላቸዋል፡፡

የፕሮፌሰር ዓቢይ ልጅ ሚኒ ዓቢይና ልጇ ፋሲል እንዲሁም ኤልሳቤጥ ፎርድና ሌሎቹም የቤተሰቡን ውርስ በማስቀጠል ሕይወታቸውን ሙሉ ያከናወኑት ሠናይ ተግባር ሕያው ሆኖ እንዲዘልቅ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ይታመናል፡፡

በግል ሕይወታቸውም ሆነ በሙያቸው የኢትዮጵያንና የካሪቢያን ሕዝቦችን ባህላዊ ማንነት ክብርና አንድነትን ያለማቋረጥ ሲያራምዱ የቆዩት ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ፣ በ83 ዓመታቸው በሀገረ አሜሪካ ያረፉት ረቡዕ ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በካቶሊክ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ከተደረገላቸው በኋላ በቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር፣ ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን በክብር ሲፈጸም የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይን ጨምሮ ታላላቅ ምሁራን፣ የጥበብ ሰዎችና አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል፡፡

በተለያዩ ሥርዓተ ቀብሮች ላይ ሲገኙ የሚታዩት የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በዘጠና ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ባለውለታ ከሆኑት የፎርድ ቤተሰቦች አንዱ በሆኑት ነፍስ ኄር ዓቢ ፎርድ ሥርዓተ ቀብር ለምን ሳይገኙ ቀሩ በማለት አስተያየት ከመሰንዘር ያልተመለሱም አሉ፡፡

‹‹እንግዲህ መቃብር ተግተህ ተማር

አፍሪቃና ሙዚቃን ጋዜጠኝነትና ፊልምን

ይዞልህ መጥቷልና ዓቢይ መምህር፤›› አሰኝቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...