Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የጋዜጠኝነት ዋጋው ስንት ነው?

በሒሩት ደበበ

ሰሞኑን አልጄዚራ የተባለው ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ “Killing the Messenger” (የመልዕክተኛው ግድያ) የሚል ዶክመንተሪ ደጋግሞ አቅርቧል፡፡ ይህ በጋዜጠኞች እስራት፣ ግድያና እንግልት ላይ ያተኮረ ዘገባ ለሙያው ሥነ ምግባርና ሞራላዊ ተልዕኮ በየአገሩ የወደቁ እውነተኛ ሙያተኞችን ታሪክ ዘግቧል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ገደማ ብቻ በኢራቅ 174፣ በሶሪያ 91፣ በፊሊፒንስ 77፣ በሶማሊያ 58፣ በኮሎምቢያ 47፣ በሜክሲኮ 32… መሞታቸው ተወስቷል፡፡ አፍሪካን ጨምሮ በብዙዎቹ ለጋ ዴሞክራሲ ባለባቸው ወይም በለየላቸው አምባገነን መንግሥታት በሺዎች የሚቆጠሩ ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ ሌሎች በርካቶችም ስደትና መፈናቀል ተጋርጦባቸዋል፡፡

የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ሮበርት ጌልስ፣ “ጋዜጠኝነት የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለዓለም ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብሩህነት እውነት ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ሆኖ ሳለ መንግሥታት እየፈጸሙበት ያለው ጥቃት በሕዝቦች ላይ እንደተሰነዘረ ሊቆጠር ይገባል፡፡ ስለሆነም ይበልጡኑ በመንግሥት ፍርድ ቤቶች፣ የደኅንነት ኃይሎችና ታጣቂዎች በጋዜጠኝነት ላይ እየደረሰ ያለው በደል ሊቆምና ሊወገዝ ይገባል፤” ብሏል፡፡

ማጠንጠኛችን የአገራችን ጉዳይ ነውና ትኩረቴን ወደዚያው ላድርግ፡፡ በአገራችን የቅድመ ምርመራን ካባ ገፎ የሐሳብ ነፃነትን ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት ፀድቆ እውን መሆን ከጀመረ ሁለት አሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች መታተም ችለዋል፡፡ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ እንደሚፈለገው ባይሆንም እየተሞካከሩ መሆኑም ይታወቃል፡፡ በእነዚህ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ውስጥ ሲሠሩ የነበሩና እየሠሩ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እንደሆኑም ይታመናል፡፡

በአገራችን መገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ ጋዜጠኞች የሚባሉ የጋዜጣ ሪፖርተሮች፣ ጸሐፊዎች፣ ተርጓሚዎችና አራሚዎች ቢያንስ አንድ ክፍለ ዘመን አስቆጥረዋል፡፡ በዚህ ረጅም ጊዜ ምንም እንኳን የሙያ ሥልጠናውንና ዓለም አቀፉን ሥነ ምግባር አሟልተው ባይሆንም፣ አንቱ የተባሉ የመስኩ ሰዎች ተፈጥረዋል፡፡ መነሻቸው ከሃይማኖት ተቋማትም ይሁን ከቤተ መንግሥት የተለያዩ መረጃዎችን በተለይ ለአንባቢያን በማድረስ ቢያንስ በአገሪቱ የንባብና የጽሕፈት ባህል እንዲዳብር የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ሊካድ አይችልም፡፡ ከ1953 ዓ.ም. የለውጥ ጅማሮ በኋላም በተለያዩ መንገዶች የመንግሥትን ግድፈትና የባለሥልጣናትን ብልግና የሚተቹ፣ የሕዝቡን ቅሬታና ስሜት የሚኮረኩሩ ሙከራዎች ይታዩ ነበር፡፡ በኋላ የነአቤ ጉበኛና በዓሉ ግርማ ዓይነት ለእውነት ሲል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ መምጣት ጥንስሱ የለውጥ ስሜት ነበር፡፡

በአገራችን ጋዜጠኝነትና የድርሰት ሙያ በጥሩ ሁኔታ ተሰናስሎ መጓዙ በተለይ በመዝናኛና በሥነ ጽሑፋዊ መጣጥፎች ረገድ መሻሻሎች እንዲታዩ ረድቷል፡፡ ይሁንና አገሪቱን ደርግ ከተቆጣጠረ በኋላ እንደ ብዙዎቹ ተግባሮችና የዴሞክራሲ እሴቶች ጋዜጠኝነትም አንገቱ ላይ ገመድ የተንጠለጠለበት፣ እግሩ የተሰነከለ ሙያ ሆኖ ቀረ፡፡ የቅድመ ምርመራ መኖር ብቻ ሳይሆን የገዥዎችን እንከን መተቸትም ሆነ የፖሊሲ አፈጻጸምን መንቀፍ ወደ ገደል የሚያስወረውር ሆነ፡፡ በዚህም አድርባይነት፣ ውሸትና የተስፋ ዳቦ የሚያስገምጥ ፕሮፓጋንዳ አየሩን ሁሉ ሞልቶት አረፈ፡፡

ያ እኩይና አገሪቱን ወደኋላ የመለሰ ወታደራዊ ሥርዓት ተገርስሶ አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲቋቋም ጋዜጠኝነት የገጠመው ፈተና መልኩ ሌላ ሆነ፡፡ አንደኛው በተፈጠረው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ (Press Freedom) ስም በትጥቅ የተሸነፈው ኃይል ጥላቻ፣ ግጭት የሚጋብዝና ሕዝብን ተስፋ የሚያስቆርጥ አሉባልታና ልቦለድ ላይ ተጠመደ፡፡ በዚህም ሀቀኝነትና ሚዛናዊነት የተባሉት የሙያው ምሰሶዎች ወርውሮ መሞነጫጨሩን ተያያዘ፡፡ በእርግጥ ለዚህ ችግር መባባስ በአንድ በኩል የመንግሥት አካላት መረጃ ክልከላና የግሉን ፕሬስ የጎሪጥ መመልከትም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሁለተኛው ፈተና የሕዝብ የተባለው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለው ጋዜጠኛና ሚዲያ በ“ልማታዊ ጋዜጠኝነት” ስም ሙገሳ፣ የጎደለ ሞልቶ ማስተጋባት፣ አለፍ ሲልም ሀቅን መሸሸግ ላይ ተጠምዶ ቀረ፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት በኢቢሲ (የቀድሞው ኢቲቪ) እና የመንግሥት ጋዜጦች እንደታየው ትምህርት የሚወሰድባቸው የውድቀት ዘገባዎች፣ የጎሉ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ዘገባዎች፣ አልያም የፖሊሲ አፈጻጸም ድክመቶች ሲሠሩ አልተስተዋለም፡፡ አንዳንድ የምርመራ ዘገባ መልክ ያላቸው ሙከራዎች ብልጭ ቢሉም ተከታታይነት የሌላቸው ናቸው፡፡ በዚያ ላይ “ተነካሁ” የሚለው የመንግሥት ኃላፊ ወይም የሕዝብ ግንኙት የሚያንጋጋው ማስተባበያና ዛቻ ምን ያህል የገነገነ እንደሆነ በሙያው ውስጥ ያለ ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ሚዲያው አንቆለጳጳሽ፣ አዝማሪና አሞጋሽ ሆኖ እንደቀረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ውስጥ ዋናው ፈተና ግን ከዴሞክራሲው ለጋነት ጋር የሚመነጨው ችግር ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደሚታወሰው ጫፍና ጫፍ የነኩ የመቃወምና የመደገፍ አባዜ የተጠናወታቸው ብልሹ የጋዜጠኝነት ጅምሮች ተንጋደው ከመብቀላቸው ጎን ለጎን በአቀረቡት ዘገባ ብቻ የመታሰር፣ የመሸማቀቅና የመሰደድ ዕጣ ፈንታ የተደቀነባቸው ሙያተኞች አሉ፡፡ ሲፒጄ የተባለው የዘርፉ ዓለም አቀፍ ማኅበር ከሰሞኑ ባቀረበው የአፍሪካ ሪፖርቱ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የጋዜጠኞች እንቅስቃሴ ከግድያ በመለስ ባሉ ውክቢያዎችና የማሸማቀቂያ ሥልቶች ገልጾታል፡፡

መንግሥት በጋዜጠኞች ላይ ለሚያካሂደው ክልከላ ሕጋዊነት ያላቸው አዋጆችን አውጥቷል ያለው ሲፒጄ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ፣ አዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የሲቪክ ማኅበራት ሕጉና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 በማነቆነት ጠቅሷቸዋል፡፡ እነዚህ ሕጎች በምሥራቅ አውሮፓ አንዳንድ አገሮችና በሩሲያ፣ እንደ ቻይና በመሳሰሉ አገሮች ካሉ ሁኔታዎች ጋር በማመዛዘን የሐሳብ ነፃነትንም ሆነ የጋዜጠኛውን የመዘገብ መብት እንዳወከው ተችቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል ሕግና ሥርዓት መከበር አለበት ይላል፡፡ በዚህም ባልተገባ መንገድ ዘገባዎችን የሚሠሩ ጋዜጠኞች “ወደ መስመር ይግቡ” አልያም በሕግ ይጠየቃሉ ብሎ በመነሳቱ ከምኅዳሩ የወጡ ሙያተኞችና የመገናኛ ብዙኃን ቁጥራቸው ትንሽ አይደሉም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉና በሚዛናዊነታቸው የሚታወቁ የኅትመት ውጤቶች ቁጥራቸው ትንሽ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፉ ለመሆናቸውም ነጋሪ አያሻውም፡፡ በዋናነት ትክክለኛ መረጃ በፍጥነት የማግኘት ፈተና አለ፡፡ የኅትመት ዋጋ ንረት፣ የማተሚያ ቤት ችግር፣ ገጾችን ስፖንሰር የሚያደርግ ተቋም መጥፋትና ከሥርጭት አውታር ጋር ያለው ክፍተት ዘርፉ ለምሽ እንደያዘው ሕፃን እንዲውተረተር አድርጎታል፡፡

በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት (የግል የመንግሥት ሳይባል) ያለው ሌላው መሠረታዊ ፈተና ብስለትና ብቃት ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል የሚያኮራ ታሪክና መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ አርዓያ አለመኖሩ ነው፡፡ በተለይ አሁን ባለው የዘርፉ ትውልድ ውስጥ “አንቱ!” የተባለ ጋዜጠኛ ካለመኖሩም ባሻገር በቀደመው ትውልድ በሠሯቸው ሥራዎች በዓሉ ግርማን፣ ጳውሎስ ኞኞን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን፣ ወዘተ በመጥቀስ ብቻ ቀርተናል፡፡ በዚህ ረገድ አሁን አሁን በጋዜጠኝነታቸው ታስረዋል የሚባሉትን (እነ እስክንድር ነጋ፣ ብትፈታም ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት…) ለማሞገስ የሚደረገው ፖለቲካዊ ፍትጊያም በተጨባጭ በሙያው ውስጥ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ የጋዜጠኝነትን ዋጋ ከፍ የምናደርግበት ትልቁ ማዕረጋችንና ክብራችን ሊሆን የሚገባው ተፅዕኖ ፈጣሪነትና አርዓያነት እንደ ሰማይ ርቆን ቀርቷል፡፡ ጋዜጠኝነት በፖለቲካ ፅንፍ ውስጥ የሚታጨቅ ሙያ ሳይሆን የራሱ እሴትና ሙያዊ ሥነ ምግባር ያለው ነው፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ያለው ሙያተኛ (በተለይም በመንግሥት ሚዲያ ውስጥ) አቅምና ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ ነው፡፡ ልምድ እያካበተና “እጁን እየፈታ” ያለውም መስኩን እየተወ ቢበዛ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ቢያንስ ደግሞ በራሱ “የአየር ሰዓት ግብይት” ውስጥ ተወሽቋል፡፡ ይህን ሁኔታ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል በተደረገ አንደ ጥናት የችግሩ ሚስጥር ተለይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አብዛኛው ጋዜጠኛ ዝቅተኛ ተከፋይ ነው፡፡ በሙያው ከሚያገኘው ጥቅምና ክብር ይልቅ የሚከፍለው ዋጋና የሚደርስበት መገለል ይበዛል፡፡ እንደ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ባሉት የእርስ በርስ አለመግባባትና ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ የመንግሥት ጋዜጠኞች ከገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በላይ ተገለዋል፡፡ በሻይ ቤቶችና በታክሲ ፊርማታዎች ሳይቀር እስከ መሰደብ እንደደረሱ በወቅቱ በሙያው ውስጥ የነበርነው ሁሉ አንዘነጋውም፡፡ መንግሥት ለትንንሹ ካድሬ ሳይቀር ቤት፣ መኪናና የተሻለ ደመወዝ ሲሰጥ በጋዜጠኝነት ትልቅ ደረጃ ለደረሱት እንኳን ተገቢውን ክብር የሚጠብቁበት ሥርዓት ማበጀት አልቻለም፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜ አጥጋቢ የሚባል ደመወዝ ለጋዜጠኞች መክፈል የጀመሩ የግል ሚዲያዎች መኖራቸው ግን አንድ ተስፋ ነው፡፡

ገንዘብ ብቻ የአንድን ሙያ ክቡርነትና ተወዳጅነት ሊያሳይ አይችልም፡፡ በዋናነት የሥራ አካባቢ አመቺነት፣ የግብዓት መሟላትና ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነፃነት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ጋዜጠኛው (የግልም ሆነ የመንግሥት) በጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርና መርሆ እንዲሁም በአገሪቱ ሕግና በሕዝብ ጥቅም ሥር ተጠልሎ ሐሳቡን ማንሸራሸር ከቻለ ሥራውን ይበልጥ ይወደዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በል የተባለውን ብቻ ሳይሆን ከልቡ ማለት የፈለገውን በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመሥርቶ የማቅረብ ባህል ሊዳብርና ሊጠናከር ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ፈጠራና ተወዳጅነት የተላበሰ የጋዜጠኝነት ዲሲፕሊን እየተስፋፋ መሄዱ አይቀርም፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ የጋዜጠኝነት ሙያን ዋጋ ከፍ ሊያደርግ ሲገባው፣ ያልተጠቀምንበት ትልቅ ዕድል ጠንካራ ማኅበራትና የሚዲያ ምክር ቤት (ካውንስል) ያለመኖር ጉዳይም ነው፡፡ ዛሬ እነ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና ታንዛኒያና ሞሪሸስ ያሉ የአፍሪካ አገሮች እንኳን ጠንካራ የሙያ ኅብረቶችን ፈጥረዋል፡፡ በዚህም የሙያተኞቻቸውን ብቃት፣ ተወዳዳሪነትና በሥነ ምግባር የመሥራት ልምድ ከማሳደጋቸውም ባሻገር በመንግሥት የመረጃ ሥርዓትም ሆነ የፕሬስ ሕግ አፈጻጸም ላይ የሚታዩ እንከኖችን ማቅናትና መሄስ እየቻሉ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የጋዜጠኝነት ሙያና ሙያተኝነት ወደ ዳበረ ባህል እንዲሄድ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ እኛስ ለምን አቃተን? ማለት አለብን፡፡

በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ስም “ማኅበር” እየተባሉ በየቦታው እንደ ጨው ዘር የተበታተኑት ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡  ይሁንና የተጠናከረ አደረጃጀት፣ አመራርና የአባላት ተሳትፎ የሌላቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ “ለፖለቲካ ፍጆታ” በስም ብቻ ያሉ የስፖንጅ መዶሻና የቄጠማ ምርኩዞች ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ዋነኛ የሙያው አጀንዳ ሆኖ ብዙ የተደከመበት የሚዲያ ምክር ቤት ጉዳይም ጥረቶች እየተደረጉበት ነው ቢባልም ፍሬ አፍርቶ ሊታይ አልቻለም፡፡

በአገራችን የጋዜጠኝነት ፕሮፌሽን ውስጥ የአካዳሚካዊ ምርምርና ጥናት ተኮር ባህል እንዲገነባ፣ በሙያቸው አንቱ የተባሉ ሙያተኞችን ለማፍራት የሚችሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉት የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን የትምህርት መስክ ያሉትን ዘርፎች በማሠልጠን ላይ ያሉት፡፡ ይሁንና በዚህ ረገድም መፈተሽ ያለባቸው የተለያዩ መሰናክሎች አሉ፡፡

አንደኛው በአገሪቱ እውን እንዲሆን የሚፈለገው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮትና በየተቋማቱ የሚሰጡ የኒዮሊብራል ጋዜጠኝነት እሳቤዎች እየታረቁ መሄድ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው በትምህርት ተቋማቱ ከፖለቲካዊ መድልኦ፣ ከካድሬነት (በተለይ እየተለመደ ከመጣው አድርባይነትና አስመሳይነት) በመውጣት ለሙያው መርሆ የቆሙና ሞጋች ሙያተኞች፣ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ሊኖሩን ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ ጋዜጠኝነትን የመገንባት አቅማችን መዳከሙ አይቀርም፡፡

በአጠቃላይ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ሁኔታ ጋዜጠኝነት ከኮክቴልና ንግግር ግልበጣ ወጥቶ በምርምር፣ በጥናትና በምርመራ ባህል እንዲገነባ ሙያው የተተመነለት ዋጋና የቆመበት ድንጋይ ሊፈተሽ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከምንም ነገር በላይ በሙያ ሥነ ምግባር የሚመራ፣ ሀቀኛ፣ ሚዛናዊና ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዘወሩ ካድሬ ጋዜጠኞች ጉዳይ በኢትዮጵያ ተረት መሆን አለበት፡፡ ጋዜጠኝነት በገለልተኝነት መርህ የሚመራ ሙያ እንጂ የፖለቲከኞች ተቀፅላ አይደለም፡፡ አጋፋሪ ጋዜጠኞችን ጀግና እያሉ ማወደስ ይቅር፡፡ ለማንም አይጠቅምምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles