የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ለሌሎች ሆስፒታሎች አርአያ ሊሆን ይችላል የተባለውን የሥነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒክ ታኅሳስ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በይፋ ሥራ አስጀመረ፡፡
‹‹ምቹ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ክሊኒክ፣ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የሚገኝ ሲሆን፣ የቤተሰብ ዕቅድ መረጃና ምክር፣ የእርግዝና መከላከል አገልግሎት፣ የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ሕጋዊ የፅንስ ማቋረጥና ተዛማጅ አገልግሎቶችን በማዕከል የሚሰጥ ነው፡፡
ሙሉ አገልግሎት በአንድ ላይ ከሚሰጠው ክሊኒክ በተጨማሪ፣ ኮሌጁ ሦስት የፌሎውሽፕ ፕሮግራሞችን ይፋ አድርጓል፡፡ ‹‹ምቹ›› በተመረቀበት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የማህፀንና ፅንሰ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ፌሩዝ ስሩር፣ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና መካንነት፣ ከማህፀንና ፅንስ ችግር ጋር በተያያዘ የሚመጡ ሕመሞችን እንዲሁም የማህፀን ካንሰር ሕክምና የፌሎውሽፑ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡