Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዋጋ ቅናሽ?

የዋጋ ቅናሽ?

ቀን:

ከገና በዓል ዕለት ቀደም ባሉት ቀናት በተለይም ሁለት ሦስት ቀናት በፊት በዓል በዓል የሚሉና በዓል መሆኑን የሚያስታውሱ የተለያዩ ነገሮች መንገድ ላይ፣ በገበያ፣ በሕንፃዎች እንዲሁም በመዝናኛ ሥፍራዎች ተስተውለዋል፡፡ ከንግድ ቤቶች ደጃፍ የተዘጋጁ የገና ዛፎች፣ መንገድ ላይ የሚሸጡ ፖስት ካርዶች፣ የገና ዛፍ ማስዋቢያ ቁሳቁሶች በዚህ ረገድ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው በሕንፃዎች መግቢያ ላይ ትልልቅ እስፒከሮችን አድርጎ የዓውደ ዓመትና ሌሎችንም ሙዚቃዎች ከፍ ባለ ድምፅ መልቀቅ ደግሞ ጐልቶ የወጣ የበዓል ትዕይንት እየሆነ ነው፡፡

በአንዳንድ ሕንፃዎች ደግሞ በዓሉን በዓል የማሰኘቱ ነገር ከሙዚቃው አልፎ በባህላዊ ውዝዋዜና በሰርከስም እየታጀበ ነው፡፡ ይህንን በሕንፃዎች የሚታይ ነገር ብዙዎች ድምፁ አካባቢን ይረብሻል በማለት ሲያማርሩ አንዳንዶች ደግሞ ደስ የሚያሰኝ የበዓል ድባብ ይፈጥራል ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በሌላ በኩል የበዓል ገበያ ሲታይ በዕቃዎች ላይ የሚደረግ ታላቅ ቅናሽ ትኩረት የሚደረግበት ነገር ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢ በሚገኙ መደብሮች እንዲሁም በገበያ ማዕከሎች የዋጋ ቅናሽ መኖሩን የሚጠቁሙ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጽሑፎች የመደብሮቹ በርና መስኮቶች ላይ ተለጣጥፈው ይታያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ቅናሽ አድርገናል ከማለት በዘለለ 50 በመቶ ወይም 40 በመቶ ቅናሽ መደረጉም በተመሳሳይ መልኩ ይለጠፋል፡፡ ይህ በተለይም በልብስና ጫማ ቤቶች ላይ የሚጐላ ቢሆንም ሌሎች ዕቃዎች በሚሸጥባቸው ሱቆችም ያለ ነገር ነው፡፡ የእነዚህ ታላቅ ቅናሾች መረጃ በተለያየ መንገድ (በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ በማስነገር በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ጭምር) ከገዥው ዘንድ እንዲደርሱም ይደረጋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ አዲስ አበባ ባለ ከተማ ውስጥ ሽያጭና የሽያጭ ማስታወቂያ ዓመት ሙሉ ያለ ነገር ቢሆንም በበዓል ነጋዴዎች የገዥን ቀልብ ስበው የገበያ ድርሻቸውን ለመውሰድ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡ ታላቅ ቅናሽ ማድረጋቸውን ማሳወቅ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው፡፡ እዚህ ላይ በብዙዎች የሚነሳው ጥያቄ ይኼን ያህል ያንን እየተባለ የሚባለው ቅናሽ ምን ያህል እውነተኛ ቅናሽ ነው? የሚለው ነው፡፡ በበዓል ጊዜ የሚደረገው ላይ ብቻም ሳይሆን በየጊዜው የሚደረጉ ቅናሾች ላይም ይህ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ቢሆንም ግን ገዥውን የሚጋብዝ ቅናሽ ማድረግ የብዙዎቹ ሱቆች የዓውደ ዓመት የሽያጭ ስትራቴጂ ነው፡፡

የዓመት በዓል ሽያጭ ድርሻን ማስፋት፣ አዳዲስ ዕቃዎች ማስገባት ሲታሰብ የማጣሪያ ሽያጭ ሲያስፈልግና ሌሎችም ለታላቅ ቅናሽ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ያነጋገርናቸው የተለያዩ ሰዎች የዋጋ ቅናሾች እውነተኛ ቅናሽ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸውልናል፡፡ ብዙዎቹ እንዲሁ ነገሩን ከሁኔታው ትክክለኛ ነው ብለው እንደማያምኑ ሲገልጹ በተደጋጋሚ ገበያውን በማስተዋል አንዳንድ ዕቃዎች ምንም ዓይነት ቅናሽ ሳይደረግባቸው በታላቅ ቅናሽ ስም እንደሚቸበቸቡ የሚናገሩም አሉ፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት ደንበኝነቷን ቦሌ አካባቢ ከሚገኝ የሴቶች ልብስ መሸጫ መደብር እንዳደረገች የምትናገረው ሒሩት ተፈራ ብዙ ቦታ ዓመት በዓልን ምክንያት አድርገውም ይሁን ሌላ ጊዜ የሚደረጉ ቅናሾች እውነተኛ ናቸው ብላ አታምንም፡፡ ይህንን የምትለው በየጊዜው ወደ ልብስ መሸጫ መደብሮች ጎራ የምትል በመሆኑ ቅናሽ ተደረገባቸው የሚባሉ ዕቃዎችን ዋጋ ከቀደመ ዋጋቸው፣ እንዲሁም ከመደብር መደብር የዋጋ ልዩነቶችን የምታጤን መሆኗን ነው፡፡

ሒሩት እንደምትለው ታላቅ ቅናሾች በአብዛኛው የነጋዴውን ፍላጐት መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ቅናሽ ተደርጓል ሲባል ገዥውም በተወሰነ መልኩ ትክክለኛ ምክንያታዊ ዋጋ ይሰጣል እንዲሁም ብዙ ዕቃ ቀርቦ አማራጭ ይሰፋል ብሎ ስለሚያምን የመግዛት ፍላጎቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የሚደረገው ቅናሽ ግን እውነተኛ ስለማይሆን ጥቅሙ የሻጮች ይሆናል፡፡

‹‹እኔ ከሁለት ዓመት ወዲህ ደንበኝነቴን ያደረግኩት አንድ ሱቅ ነው፡፡ ጓደኛዬ ሱቁ የሚገኝበት አካባቢ ስለምትሠራ የዋጋ ቅናሽ ሲደረግ ትደውልልኛለች፤›› የምትለው ሒሩት በየወሩ አንድም ይሁን ሁለት ነገር ለመግዛት ወደ መደብሩ ጐራ ስለምትል በዚያ ሱቅ የሚደረገው ቅናሽ እውነተኛ መሆኑን በእርግጠኝነት ትናገራለች፡፡

በሱቁ ለገና በዓል በተደረገው የዋጋ ቅናሽ ከበዓሉ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ አምስት ነገሮችን መግዛቷን፣ በዚህም በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ ሃምሳ በመቶ ድረስ ቅናሽ መደረጉን ማስተዋሏንም ትናገራለች፡፡ ‹‹ዕቃዎቹ ሲገቡ የነበራቸውን ዋጋ ስለማውቀው የእውነት ቅናሽ መደረጉን መናገር እችላለሁ፡፡ ሌሎች ቦታዎች ላይ የማየው ወይ የመጀመሪያ የሚባለው ዋጋ የተጋነነ ነው አልያም እንዲሁ ይኼን ያህል ቅናሽ አድርገናል ብለው ይለጥፉና የዕቃዎቹ ዋጋ የነበረው ራሱ ይሆናል፤›› ትላለች፡፡

ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ገዥ ለመሳብ የሚሞክሩ ሱቆች በርካታ ቢሆኑም የዚህ ዓይነት የሽያጭ ዘዴ የማይከተሉም አሉ፡፡ ፒያሳ አካባቢ ጎራ ባልንበት አንድ መደብር በባለቤቶቹ ወንድማማቾች እንደተገለጸልን ብዙ ሱቆች የሚያደርጉት የዋጋ ቅናሽ እውነተኛ ነው ብለው ስለሚያምኑ የዚያኑ ያህል ውጤታማ ነው ብለውም አያስቡም፡፡ ስለዚህም ጊዜ እየጠበቁ የዋጋ ቅናሽ ከማድረግ ይልቅ እንደ ዕቃው፣ እንደ ገዥው ሁኔታ እያዩ ደንበኛ ማፍራትን ይመርጣሉ፡፡

በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ መደብሮች የተደረጉ የዋጋ ቅናሾች እውነተኛነትን በሚመለከት ጥያቄ ያቀረብንላት ወ/ሪት ሕይወት ዓለሙ በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ፕሮጀክት አስተባባሪ ነች፡፡ ብዙ ጊዜ የሚደረጉ የዋጋ ቅናሾች እውነተኛ ናቸው ብላ አታስብም፡፡ እውነተኛ አይደሉም ስትል መጀመሪያ የምታስቀምጠው የቀደመ ዋጋቸው ተብሎ የሚለጠፈው ዋጋ የተጋነነና የማይመስል መሆኑን ነው፡፡ ሱቆች ቅናሽ ማድረጋቸውን የሚያሳዩ ጽሑፎችን መለጣጠፍ እንዲሁ የለመደባቸው እንደሚመስላት ሁሉ ትናገራለች፡፡ ‹‹ቢሆንም ግን ብዙ ሰው ይኼን ያህል ቅናሽ አድርገናል ያን ያህል የሚል የተለጠፈባቸው ቤቶች መግባት ስለሚቀናው ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑ ይመስለኛል፤›› ትላለች፡፡

ቅናሾቹ የመደብሮች ገዥ የመሳብ ስትራቴጂዎች እንጂ ትክክልኛ እንዳልሆኑ እንደ እሷ ያሉ ብዙዎች የሚያምኑ ቢሆኑም እውነተኛ ነው አይደለም የሚለውን ሳያስተውል ዝም ብሎ እየገባ የሚገዛው ቁጥር እንደሚበልጥም ይሰማታል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ እየታየ ባለው የሰዎች እንደየአቅማቸው የተለያዩ ዕቃዎችን የመሸመት አዝማሚያ የዚህ ዓይነቱ የንግድ ዘዴ ሻጩን ተጠቃሚ እያደረገ ገዥውን እንደሚጫን ትገልጻለች፡፡  

የዋጋ ቅናሾቹ ትክክለኛ ካለመሆን አልፎ እንደ ዓመት በዓል ያሉ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ቅናሽ አድርገናል በማለት እንዲያውም ዋጋ ጨምሮ የመሸጥ አዝማሚያ መኖሩን የሚያምኑም አጋጥመውናል፡፡ በሌላ በኩል በዋጋ ቅናሽ አድርገናል ስም ረጅም ጊዜ የቆዩና ጥሩ የማይባሉ ዕቃዎችን የማቅረብ ነገር መኖሩንም የገለጹልን አሉ፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ታላቅ ቅናሽ አድርገናል ተብሎ ይለጠፍና ወደ ውስጥ ሲዘልቁ የዋጋ ቅናሽ የተደረገው በጣት የሚቆጠሩ ዕቃዎች ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ዕቃዎቹም ጥሩ አይሆኑም፡፡

አቶ ዳግማዊ ድጋፌ ቦሌ መድኃኒዓለም አቅራቢያ በሚገኝ ሕንፃ የልብስ መሸጫ መደብር አለው፡፡ በእሱ መደብርም ለበዓል የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ እሱ እንዳለው 6,000 ይሸጡ የነበሩ ሱፎች በ4,700 ብር ሲሸጡ 1,100 የነበሩ ቲሸርቶችም በ700 ብር እየተሸጡ ነው፡፡ መጀመሪያ የዋጋ ቅናሹ ለአሥራ አምስት ቀናት ያህል እንዲቆይ አስበው የነበረ ቢሆንም ከአሥራ አምስት ቀን ዘሏል፡፡ ለጥምቀት በዓልም ተመሳሳይ የዋጋ ቅናሽ የማድረግ ሐሳብም አላቸው፡፡

በእሱ መደብር የተደረገው የዋጋ ቅናሽ እውነተኛ እንደሆነ ለማስረዳት የሚሞክረው አቶ ዳግማዊ በጥቅሉ ከተማ ውስጥ ያለውን የዋጋ ቅናሽ 25 በመቶ ብቻ እውነተኛ ይሆናል ብሎ ሲያስብ ቀሪው እንዲሁ አድርገናል በሚል ገበያ የመሳብ መላ እንደሆነ ግምቱን ይናገራል፡፡ የዋጋ ቅናሾች እውነተኛ ያለመሆን ነገር በሌሎችም አገሮች እንዳለ የሚጠቁመው አቶ ዳግማዊ የዚህ ዓይነቱ ነገር አንዳንድ ጊዜ ከባለቤቶች እውቅና ውጪ በሻጮችም እንደሚደረጉ ይናገራል፡፡

‹‹ዕቃ ያመጣው ያስገባው ባለቤት ያስቀመጠው ዋጋ እያለ ሱቅ ላይ የሚቆሙ ሠራተኞች አንድን ዕቃ አምስት መቶ እንደዚህ ጨምረው ይሸጣሉ፡፡ ባለቤት የዋጋ ቅናሽ ይደረግ ብሎ ሲደረግ ዋጋው ራሱ ሆኖ ሲገኝ ገዥን ግራ ያጋባል፤›› ይላል፡፡

ዕቃዎችን ለማየት እንዲሁም የተወዳዳሪዎችን ዋጋ ለማወቅ የተለያዩ መደብሮችን ተዘዋውሮ የተመለከተው አቶ ዳግማዊ በአመዛኙ ቅናሽ እየተባለ ያለው ሐሰት መሆኑን ይደመድማል፡፡ የተወሰኑ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቅናሽ አድርጎ ሌሎች ላይ አለማድረግ ግን በራሱ ችግር አይደለም ይላል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...