Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለበዓላት የሚዘረጉ እጆች

ለበዓላት የሚዘረጉ እጆች

ቀን:

ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ አራት ጓደኛሞች አረፍ ብለው ይጨዋወታሉ፡፡ ከመሀከላቸው አንዱ ጉዳይ ነበረውና ተሰናብቷቸው ከካፌው ወጣ፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ አንድ ወጣት አስቆመው፡፡ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የተሰናዳ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ምሳ የማብላት ዝግጅት አስተባባሪ እንደሆነ ነግሮት፣ ለዝግጅቱ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሸጠውን ኩፖን እንዲገዛው ይጠይቀዋል፡፡ ያለምንም ማንገራገር ኩፖኑን ከመግዛቱም ባሻገር፣ ወደነበረበት ካፌ ተመልሶ ጓደኞቹንም ኩፖን ያስገዛቸዋል፡፡

ግለሰቡ ዓውደ ዓመትን አስታከው የሚደረጉ በጐ አድራጐቶችን በቻለው አቅም ሁሉ ይደግፋል፡፡ በአንድ ወቅት ከኪሱ ብዙ ሺሕ ብሮች እያወጣ ነዳያንን በበዓላት ይመግብ ነበር፡፡ እንደእሱ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ለመመገብና ለማልበስ የተሰባሰቡ ሰዎችን ማኅበር በመቀላቀልም የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ኩፖኑን የገዛው አዲስ ሆሊደይ ላንች ዊዝ ዘ ሆምለስ በሚል ከሚንቀሳቀስ ማኅበር ነው፡፡ ኩፖኑ ከ25 ብር እስከ 200 ብር ዋጋ ያለው ሲሆን፣ ገንዘቡ ሲጨምር ገዥው ስፖንሰር የሚያደርጋቸው ነዳያን ቁጥር ከፍ ይላል፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተው ከ7 ዓመት በፊት ነበር፡፡ በአዲስ ዓመት፣ ልደትና ፋሲካ ደጋፊ የሌላቸውን አሰባስበው ይመግባሉ፤ አልባሳትም ያበረክታሉ፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለኢድ አልፈጥርና ኢድ አልአድሃ በዓላትም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

አንድ ዓውደ ዓመት ሲቃረብ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚያስተባብር ሰው ኮሚቴ ያዋቅርና ገቢ ማሰባሰቡ ይጀመራል፡፡ እንደ ዘንድሮው ኩፖን በመሸጥ እንዲሁም ሙሉ ወጪ ከሚሸፍኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ገንዘብ ያሰባስባሉ፡፡ ለሮተሪ ክለብ አባሎች ትኬቶችን በማደል እንዲሸጡ የሚደረግበት ጊዜም አለ፡፡ በመቀጠል በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የጐዳና ተዳዳሪዎች ካሳወቁ በኋላ፣ በበዓሉ ቀን የማኅበሩ አባላት ያስተናግዳሉ፡፡ ከበዓሉ በፊት ለማኅበሩ አልባሳት የሚሰጡ በዕለቱ ይዘው የሚሔዱም አሉ፡፡

የዘንድሮውን የልደት በዓል ዝግጅት ከሚያስተባብሩት አንዱ ዶ/ር አቤሴሎም ሳምሶን እንደሚናገረው፣ ወደ 20,000 ብር ገደማ አሰባስበው 2,500 የሚሆኑ ሰዎችን ለማብላት አቅደዋል፡፡ አልባሳትም እያሰባሰቡ ነው፡፡ እንደ ተራድኦ ድርጅቶች የተዋቀረ አሠራር ስለሌላቸው፣ አስፈላጊውን ግብአት ለማሰባሰብ ቢከብዳቸውም፣ ዓላማቸውን በመደገፍ ከጐናቸው የሚቆሙ ሰዎች መበራከታቸው ሥራቸውን እንደሚያቀልላቸው ይናገራል፡፡ ‹‹በበአል አብሮ መመገብ ወዳጅነት ይፈጥራል፤ በጐ አድራጐቱ የዜግነት ኃላፊነታችንን የምንወጣበትም ነው፤›› ይላል፡፡

ማኅበሩ ውስን አባላት የሉትም፡፡ ስለ ሥራቸው መረጃ ያላቸው ሰዎች በአጠቃላይ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ የማኅበሩ እንቅስቃሴ ከዓመት ወደ ዓመት እየታወቀ መምጣቱ ደጋፊዎቻቸውን እንዳበዛላቸው አስተባባሪው ያስረዳል፡፡ በአንድ በዓል ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ በጐ ፈቃደኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ተማሪዎችና ያላገቡ ወጣቶች ናቸው፡፡ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት መካከለኛ ገቢ ያላቸው እንደሆኑም አስተባባሪው ይናገራል፡፡

ኮርዴይት የተባለ ተቋም ሥራ አስኪያጅ የሆነው ዶ/ር አቤሴሎም፣ 34 ዓመቱ ሲሆን፣ በ2004 ዓ.ም. ነዋሪነቱን ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ ካደረገ ጊዜ ጀምሮ ከማኅበሩ ጋር ይሠራል፡፡ አውደ አመትን ምክንያት በማድረግ የሚካሔዱ በጐ አድራጐቶች ሰዎች ከተባበሩ በቀላሉ መረዳዳት እንደሚችሉ ያሳያሉ ይላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሳተፉ ግለሰቦች ቁጥር መጨመሩ መልካም ቢሆንም፣ ዕርዳታውን ቋሚ የማድረግ ጉዳይ መነሳት እንዳለበት ያምናል፡፡

በበዓላት የሚከናወኑ በጐ አድራጐቶች በልዩ ልዩ ሃይማኖቶችና በማኅበረሰቡ ዘንድም የሚበረታቱ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ለአንድ ቀንም ቢሆን የተቸገሩን ማብላት፣ ማልበስና ማዝናናት የተቀደሰ ምግባር መሆኑን ቢስማሙበትም፣ ቀጣይነቱ ካልተረጋገጠ ፋይዳው እምብዛም አይደለም ሲሉ የሚደመጡ አሉ፡፡ በዓልን ያስታከኩ በጐ አድራጐቶች ላልተገቡ ማጭበርበሮች የሚጋለጡበት አጋጣሚም አለ፡፡

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ወጣት ኩፖን ከሸጠላቸው አንዷ ፍሬገነት ብርሃኑ፣ ‹‹መልካም የሚደረግለት ሰው ለቅጽበት ያህልም እንዲደሰት በበዓላት በጐ ቢደረግ ጥሩ ነው፤›› ትላለች፡፡ ሆኖም ገቢ ለማሰባሰብ ኩፖን የሚሸጡ ሰዎች ሲገጥሟት የምትገዛበት የማትገዛበትም ጊዜ አለ፡፡ በእሷ እምነት፣ በሞትና ሕይወት መካከል ያሉ ሰዎችን በማስመሰል በሀሰት የሚነግዱ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ፣ በበጐ አድራጐት ስም የሚመጣውን ሁሉ ለማመን ያዳግታል፡፡

ብዙዎች ለበጐ አድራጐት በሚል ገንዘብ ሲጠየቁ ከመስጠት ወደኋላ የሚሉት ገንዘባቸው ለመልካም ነገር ስለመዋሉ እርግጠኛ መሆን ስለማይችሉ ነው፡፡ እንዳይጭበረበሩ በመስጋት ገንዘብ ከመስጠት የሚቆጠቡ እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ትክክለኛውን ከአታላዩ መለየት አይቻልም፤ የውሸት ነው ብዬ ገንዘብ ሳልሰጠው ያለፍኩት ግለሰብ፣ እውነተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ለጠየቀኝ በጐ አድራጊ ሁላ ገንዘብ እሰጣለሁ፤ ኩፖን እገዛለሁ፤ ልብስም እሰጣለሁ፡፡ ከሰጠሁ በኋላ በፈጣሪም ዘንድ የሚጠየቅበት ተቀባዩ ነው፤›› ያለን ደግሞ ከፍያለው ኃብተጊዮርጊስ ነው፡፡

ከፍያለው ይህን ቢልም የተዋቀረ አሠራር ከሌለ ለውጥ እንደማይመጣ ከፍሬ ገነት ጋር ይስማማበታል፡፡ ሀሳባቸውን የምትጋራው በአንድ የግል መሥሪያ ቤት የምትሠራው የ24 ዓመቷ ማስተዋል ዋለልኝ ናት፡፡ ማስተዋል ከሁለት ዓመት በፊት የሥራ ባልደረቦቿንና ጓደኞቿን አሰባስባ፣ ለበዓል አረጋውያንና ሕፃናትን አብልተዋል፣ አልብሰዋልም፡፡

በፌስቡክ፣ በራሪ ወረቀት በመበተንና በስሚ ስሚ ገንዘብ ካሰባሰቡ በኋላ እስጢፋኖስና ስቴዲየም አካባቢ ያሉ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ጠሩ፡፡ ነዳያኑ ፍል ውኃ ሔደው እንዲታጠቡ፣ ልብስ እንዲቀይሩና እንዲመገቡ ከተደረገ በኋላ በሙዚቃ ተዝናኑ፡፡

በዓሉ ካለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ ማስተዋል ከጐዳና ተዳዳሪዎቹ አንዱን መንገድ ላይ ታገኘዋለች፡፡ ልጁ የቆሸሸና የተቀዳደደ ልብስ ለብሷል፡፡ ፊቱም ገርጥቷል፡፡ ሰላምታ ስትሰጠው ስላላስታወሳት መልስ ሳይሰጣት አለፈ፡፡ ከዚያ አስቀድማ የአንድ ቀን በጐ አድራጐት ለውጥ እንደማያመጣ ብታምንም፣ ቅጽበቱ ሀሳቧን በእውን ያየችበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ችግረኞችን በዘላቂነት መደጐም የሚቻልበት ዕቅድ ነድፋ ከሥራ ባልደረቦቿና ጓደኞቿ ጋር መመካከር የጀመረችውም ጊዜ ሳታጠፋ ነበር፡፡

በሥራና ማኅበራዊ ጉዳዮች በመጠመዷ ዕቅዱ እስካሁን ባይተገበርም ባላት አቅም እየተጣጣረች እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ጊዜአቸውና ጉልበታቸውን ሰውተው ለተቸገሩ አለኝታ ለመሆን የሚጣጣሩ ወጣቶችና ባለሀብቶች እጅና ጓንት ሆነው መሥራት አለባቸው፡፡ ‹‹ሰዎች አሳቢ እንዳላቸው ማሳየት መልካም ቢሆንም፣ ከምግብና ልብስ በዘለለ ተፅዕኖ መፈጠር አለበት፤›› ትላለች፡፡

ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም እንዲሉ፣ በአቅማቸው ለአውደ አመት አረጋውያንን ከሚመግቡ ማኅበሮች አንዱ ባይሽ ኮልፌ ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ኮልፌ አካባቢ የሚኖሩ ጓደኛሞች ያቋቋሙት ማኅበሩ፣ 30 አባላት አሉት፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራንና በሌላም ሙያ ያሉ ግለሰቦች ይገኙበታል፡፡

ፎቶግራፍ አንሺና አርታኢ ውብሸት ተካ ከአባላቱ አንዱ ነው፡፡ ለዘንድሮው የልደት በዓል አረጋውያንን ለመመገብ ገቢ ያሰባሰቡት ኮልፌ አካባቢ ጫማ በመጥረግ፣ ሶፍትና ካርድ በመሸጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም ገንዘብ ለማሰባሰብ የእግር ኳስ ጨዋታ አዘጋጅተዋል፡፡ ከፊልም ሠሪዎች ጋር በመነጋገርም ፊልም በማሳየት ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡ ውብሸት አውደ አመትና በጐ አድራጐት እየተሳሰሩ መምጣታቸውን ይገልጻል፡፡ ብዙዎች ራሳቸውን ከማስተዳደር የዘለለ ገቢ ባይኖራቸውም፣ በወርሃዊ ገቢያቸውና ከሌሎች በመለመንም በጐ ማድረጋቸው ያስደስተዋል፡፡

ቢሆንም በጐ አድራጐት ከበዓል መዝለል እንዳለበት ያምናል፡፡ የባይሽ ኮልፌ አባላት አቅም የሌላቸው ሕፃናትን በማስተማር፣ የታመመ በማሳከም፣ የተጣላን በማስታረቅና አጋዥ የሌላቸው አረጋውያንን በተለያየ ሥራ በመርዳትም ይሳተፋሉ፡፡ ‹‹ሰው ሲትረፈረፈው ብቻ ሳይሆን ያለውን ማካፈል መልካም ነው፤›› ይላል፡፡ ሁልጊዜ በተዋቀረ መልኩ መርዳት ባይችልም፣ ሁሉም ያለውን እየሰጠ መረባረብ እንዳለበት ያክላል፡፡

በተለያዩ በጐ አድራጐቶች ላይ በመሰማራት የሚታወቁትን የሮትራክትና ሮተሪ ክለቦች እንቅስቃሴ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኢንተርአክት (ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች)፣ ሮትራክት (ከ18-30 ያሉ ወጣቶች)ና ሮተሪ (ከ30 ዓመት በላይ ያሉ ጐልማሶች) የሚገኙባቸው ክለቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡

ከሮትራክት ክለቦች አንዱ 11 ዓመታት ያስቆጠረው፣ ኬሮጂ ሲሆን፣ ወደ 90 የሚደርሱ አባላት አሉት፡፡ በተፈጥሮ ጥበቃ፣ ለካንሠር ሕሙማን ድጋፍ በማድረግና አረጋውያንን በመደጐም ላይ ያተኩራል፡፡ የኬሮጂ ፕሬዚዳንት አዳም አበራ እንደሚለው፣ በየዓመቱ በዓላትን ከአረጋውያን ጋር ያሳልፋሉ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ካሉ የሮትራክት ክለቦች ጋር በጥምረት የሚሠሩ ሲሆን፣ አረጋውያንን የሚመግቡበት ፕሮጀክት በዋነኛነት የአባላት መዋጮን የተመረኮዘ ነው፡፡ በተጨማሪ በፌስቡክና ቫይበር መልዕክት በማስተላለፍና ፖስተር በመበተንም ገቢ ያሰባስባሉ፡፡ ክለባቸው በዓላትን ተመርኩዘው የተቸገሩትን ለሚረዱ ማኅበሮችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ኩፖን በመሸጥ፣ አባላቶቻቸውን በማሠማራትና በሌላም መንገድ ይተባበራሉ፡፡

ለተቸገሩ ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ አቅሙና መዋቅሩ ባይኖራቸውም፣ ቢያንስ ለዓውደ ዓመት በጐ መዋል እንዳለባቸው በማመን የሚሰባሰቡ ጓደኛሞችና የሥራ ባልደረቦች መበራከታቸውን አስተያየታቸውን የሰጡን ይስማሙበታል፡፡ በሌላ በኩል በጐ አድራጐት ከበዓላት ውጪም መለመድ አለበት የሚል አቋም ያላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህ አንዷ የ31 ዓመቷ ዚነት መሐመድ ነች፡፡ የበጐ አድራጐት ተቋም ወይም ከወርሃዊ ደመወዟ የዘለለ ገቢ ባይኖራትም በበጐ አድራጐት ትሳተፋለች፡፡ ጓደኞቿንና የሥራ ባልደረቦቿንም ታስተባብራለች፡፡ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ግለሰቦችም ከዕርዳታ ሰጪዎች ታገናኛለች፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች በሚሰጣት ኮስት ሼሪንግ       (የወጪ መጋራት) አሁን ደግሞ በደመወዟ ትምህርት፣ ልብስ ሕክምና ወይም ሌላ ድጐማ የሚሹ ሰዎችን ትረዳለች፡፡ ‹‹ብር ባይኖረኝ እንኳን መርዳት የሚችሉ ሰዎችን ስለማውቅ አገናኛለሁ፡፡ መቸገር ምን እንደሚመስል ስለማውቅ ዕርዳታዬን ፈልጐ የሚመጣ ሰውን አልመልስም፤›› ትላለች፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...