Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዳኛ አልባው ጨዋታ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?

ሰላም! ሰላም! ባሻዬ ከቡላና ከበርበሬ ወጪያቸው ብሶ የባትሪ ድንጋይ ወጪ አናታቸው ላይ ወጥቷል። “ቻርጀር በሞላበት ዘመን ዘንድሮም ባትሪ ድንጋይ የሚጠቀም አለ?” ብላችሁ ብትሉ መልሱ ‘መብራት ሲመጣ ጠይቁ’ ነው የሚሆነው። ‘ግን መብራት የሚሄደው ወዴት ነው?’ አልኩ ከራሴ ጋር ተጣልቼ። ደንበኞቼን መጣሁ እያልኩ ስልኬ ባትሪ ጨርሶ መሀል መንገድ እየዋለልኩ። መዋለል በእኔ አልተጀመረም ታዲያ። ካስማችን ሁሉ በመዋለል ጌጥ እንደገና ዛፍ ደምቆ እንዴት እንረጋለን ስታስቡት? እውነቴን እኮ ነው። እናም አንዱ አላፊ አግዳሚ ሰምቶኝ ኖሮ ቆም አለና፣ “እኛ ቆመንበት እንጂ መብራትማ ምን እግር ኖሮት ይጓዛል?” አለኝ። ሲነካኩኝ አልወድም አይደል? “ማለት?” አልኩት። “ለምሳሌ . . .” ብሎ የባቡር መንገዱን እየጠቆመ (ይቅርታ ለካ ዛሬ ባቡር አለን። እኔ ደግሞ እንደ እምዬ ምንሊክ መንገዱ ሁሉ ባቡር መንገድ ማለት እወዳለሁ። ፀረ ልማት እንዳልመስላችሁ ብዬ ነው ማብራራቴ)

“ . . . ለምሳሌ ያ ባጃጅ ቆሟል። አጠገቡ . . . እየው . . . ያ የመደብ ልዩነታችን የቱን ያህል እንደሰፋ የሚያሳይህ ‘ካዲላክ’ እያለፈው ነው። አየኸው? እንግዲህ ለቆመው ባጃጅ ካዲላኩ ተጓዥ ነው። እኩል ቢጓዙ ግን የሚጓዝ የለም። ‘ሪላቲቪቲ’ ይባላል፤” እያለ ዛሬ የመመረቂያ ወረቀት ከገበያ እየተገዛ ባለዲግሪ በሚኮንበት ዘመን ባልማር፣ በስምንተኛ ክፍል አቅም ኮሌጅ በጠስን የሚሉትን በማሸማቀቅ በፊደል ዘመን መማሬን ረሳው። እንዲያው እኮ! ሳንተዋወቅ ብዙ የምናወራው ለምንድነው? ደግሞ አንዳንዱ ቃላት ስላንኳኳ ብቻ የተማረ ይመስለዋል ልበል? ‘ኢንፍሬሪቲ ኮምፕሌክስ ነው’ አትበሉኝና። ብቻ ተውትና እሱን ወደ . . . ወደ . . . ስለምን ነበር የምንጫወተው? እንዴ ጨዋታም በመብራት ሆነ እንዴ? ጠፋብኝ እኮ የማወራው። ጉድ ነው!

በቃ በጄኔሬተር ልቀጥልላችሁ። ጀምሬዋለሁና ጥቂት ስለባሻዬ የባትሪ ድንጋይ ወጪና ብሶት ላውጋችሁ። ደጋግሜ እንደማጫውታችሁ ባሻዬ ያለሬዲዮ አይሆንላቸውም። አንዳንዴ ሳስበው እግዜር ሰውን ከአፈርና ውኃ አበጅቶ ባሻዬ ላይ ሲደርስ በአንቴናና በዝርዝር ዜና ጥማት አሽሞንሙኖ እፍ ያለባቸው ይመስለኛል። አቤት! ‘እፍ’ እንኳንም የእሱ ሆነች። አስቡት እስኪ በኤሌክትሪክ ኃይል እንደ ሞባይል ሥሩ ብሎን ቢሆን? ጠዋት ‘ሰላም አውለኝ’ ብለን ከመነሳታችን ጠፍተን እኩለ ሌሊት ላይ ቦግ ስንል እዚያው አልጋ ላይ። እግዚኦ! እንኳንም ገንዘብና መሬት ብቻ የመንግሥት ሆኑ አያሰኝም ይኼ? ቱቱ! የጆሮ ጠቢ ጆሮ አይስማብህ በሉልኝማ። እና በሻዬ ከዚያች የዘመናት ሬዲዮናቸው አልላቀቅ ብለው ስንት የተራቀቀ ዲጂታላይዝድ ሬዲዮ በመጣበት በዚህ ጊዜ ውለው ያመሻሉ። ‘ቴሌቪዢን አልወድም’ ባይ ናቸው።

ልጃቸው ደግሞ፣ “ዓይኑ ስለደከመበት እንጂ አይጠላም። ለነገሩ እንኳን እሱ እኔም ጠልቻለሁ። የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሚሉት እኮ አንድኛውን የደምና የሽብር ወሬ ሥርጭት ቢሉት ይሻላል እኮ፤” ይለኛል። ታዲያላችሁ ከወር ቀለባቸው መሀል ሬዲዮናቸው የሚጎርሱዋቸው ስምንት ባትሪ ድንጋዮች ዋና የወጪ መደባቸው ናቸው። እንዴት ሆዳቸውን ነፍገው መረጃ እንሚሰበስቡ እዩ ብቻ። እንግዲህ የበዓል ሰሞን አይደል? እንደተለመደው ማልደው ተነስተው፣ ፀሎት አድርሰው ዓለም እንዴት አድሯል ብለው ሲከፍቱ፣ “እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ። ‘ምናምን’ ቢራ! በዓሉን በቢራችን አጣጥሙት…” የሚል ማስታወቂያ ሰሙ። ‘የለም ጆሮዬ ነው’ ብለው አለፉት። ደግሞ ሌላ ቢራ። የሰሙትን እስኪጠራጠሩ ሌላ ሦስተኛ ቢራ፡፡ “በዓሉ የሰላም፣ የብልፅግና፣ የልማት ይሁን” ብሎ ሲመኝ አደመጡና ጆሮአቸውን አመኑ። ውሎ አድሮ ልጃቸው እንደነገረኝ፣ “ወንጌል እመን ትድናለህ እንዳላለኝ ምነው አሁን ጆሮዬን ባምን ልቤን ስካር ስካር አለው?” አሉ ተባለ። ወይ ባሻዬ!

በጄኔሬተር ነን ብያችኋለሁ። እጄ ላይ ሦስት ተሳቢዎች አሉ። ገዢ አግኝቼላቸው ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው ስልኬ ዘግቶ እንጀራዬን ዘጋው። ስለዚህ ያለኝ ምርጫ ጭር ባለው መንደሬ ለወሬ ጥማቴን ቻርጅ ማድረግ ነው። እናም ባሻዬን ‘እንኳን አደረሰዎ’ ልላቸው አሰብኩ። አስቤም ባዶ እጄን ሄድኩ። የመልካም ምኞት መግለጫ ለይስሙላ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ተገድቦ እያዩ መቼም ባሻዬ እጅ እጄን አያዩም። “እንኳን አደረሰዎ?” ደርሼ ከማለቴ፣ “ስንተኛው ቢራ ነህ ደግሞ አንተ?” ብለው አስደነገጡኝ። ምን ያስደነግጠኛል? ያው እርጅና ነዋ። እንዲያ በምክራቸውና በአንደበተ ርቱዕነታቸው የማውቃቸው ባሻዬን ይጫወትባቸው ጀመር? ብዬ እኮ ነው። ለነገሩ ዘንድሮ በአዲሱ ትውልድ ቋንቋ እርጅና በርቶበታል እየተባለ ነው። ደግሞ ልጅነታችን ላይ የጠፋብን መብራት መስሏችሁ እርጅና ላይ የበሩ እንደ ሻማ የቀለጡ ዕድሜዎቻችሁን አስሉና እበዱ አሉዋችሁ።

ግድ የለም ነገም ሌላ ቀን ነው ወገኖቼ፡፡ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም። ብትችሉ መርሳት ጨምሩባት። ግራ ገብቶኝ ፍዝዝ ብዬ እያየኋቸው ቋሚያቸው እንጂ ብርሃናቸው እንደማይታይ የከተማችን የመንገድ መብራቶች ጨልሞብኝ ቆምኩ። ይኼው ልማልላችሁ! “የምን ቢራ አመጡ ባሻዬ? አንበርብር እኮ ነኝ፤” ስላቸው ነው ሳንጠይቅ በዝምታና በቸልታ ያስማማናቸውን ቅይጦች ያነሱ ይጥሉ የጀመሩልኝ። አንዱ ያው ሃይማኖታዊ በዓላትና የቢራ ጠማቂዎች አጋርነት ነው። “እኔምለው ግን የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አላለም እንዴ አዳኛችን? መልካም ልደት እያልነው ቄሳር ቄሳር ካልሸተትን ስንል ሃይ ባይ የለም? ነውር አይደለም? እንዴ ጠጪ ሊሆን አልተወለደ እሱ?” ሲሉ ቤት ውስጥ ሆኖ ይሰማቸው የነበረው ልጃቸው ጮክ ብሎ፣ ‹‹ዘመኑ የቢዝነስ ነው አባዬ። ቢዝነሱ ደግሞ እንዲሰምር ስም እየተቀባ መሆን አለበት። ለዚያ ነው በስም ብቻ ያለቅነው፤” አላቸው። ‘ስም ያለው ሞኝ ነው’ የተተረተው ገበያ መሀል ይሆን እንዴ?

ኧረ! ኧረ! ገበያ ስል ጉዴን አስታወስኩት። መቼም ከላይ እስከታች ያው ስንሳሳት ሰበብ መደርደር አይደል የምንወደው? እኔ አሁን ምሳሌ አልደረድርም። ምሳሌ ያማረው ተረትና ምሳሌን ገዝቶ ያንብብ። የተግባር እንጂ የጽንሰ ሐሳብ ምሳሌ እጥረት አለብን እንዴ ለመሆኑ? እኮ! ውዷ ማንጠግቦሽ የበዓሉ ዋዜማ ረቡዕ ስለሚውል ለማክሰኞ ዶሮ ገዝተህ እረድ ያለችኝ ልክ የዛሬ ሳምንት ነበር። በዕለተ ማክሰኞ ያው እንደተለመደው መብራት ወንዝ ይሁን እንጨት ለቀማ፣ ፀሐይ ታየሁ ስትል  ጀምሮ ጠፍቷል። በጠዋት የእነዚያን ተሳቢዎች ጉዳይ ልፈጣጥም ስልኬን ትንፋሽ ሳሳጣት ያለማስጠንቀቂያ እልም አለች።  ለነገሩ ሲጠፋብንና ሲበራብን እኩል ሆኗል አሁን። እኩል ያልሆነው የኑሮና የነዋሪው ጣጣ ብቻ ይመስለኛል።

እዚያም ስሄድ ‘አሁን ሄደ’ ሲሉኝ ፈቀቅ ስል ‘ትንሽ ጠብቀው’ ሲሉኝ እንዲሁ በውስለታ የተወለደ የአባት ወይ የእናቴን ልጅ እንደምፈልግ ሁሉ ስቃብዝ ቀኑ ነጎደ። ቀን ምን አለበት ብላችሁ ነው ደግሞ። እንኳን የኃይልና የኔትወርክ መቆራረጥ ተደራርቦበት የፍቅራችን መቆራረጥና መቀዝቀዝ ብቻ በቂው እኮ ነው ለመባከን። “በከንቱ የዋለች ያልደከመች ቀን” ያለው ገጣሚ ስሙ አፌ ላይ ነበር። ማንጠግቦሽ ታዲያ፣ “የት ደርሰሃል? በስንት አገኘህ?” ልትለኝ አርባ ጊዜ ደውላለች። ለምን እንደሆነ አላውቅም ደግሞ፣ “የደወሉላቸው ደንበኛ ቴሌፎን ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም…” ባዩዋ ሴትዮ ባለትዳሮችን ከግምት ያስገባች አትመስልም። ጨሰቻ ማንጠግቦሽ። እንዴት አያስጨስ በዶሮ ምትክ የሰው ልጅ ተታሎ በመጫኛ ሲጣል? አርዝመው አስረውን የፈቱን ሲመስለን ጭስ የወጣንም እኮ እኛ ሆነን ነው!

የጀመርኩትን ጨርሼ እንሰነባበታለን። ተስፋ ስትቆርጥ ከባሻዬ ልጅ ገንዘብ ተበድራ የምትፈልገውን ገዛዛች። እኔ ለራሴ ከእኩለ ቀን በኋላ መክሸፍ የዘወትር ልማዴ ሆኗል። ሰዓቱ ልክ ሰባት ሲል ዘመን ወደፊት ይቁጠር ወደኋላ ቢጠይቁኝ አላውቅም። ‘ምክንያቱ?’ ስትሉ ሰማሁ? እኔን ከምትጠይቁኝ ፀሐይዋን ብትጠይቁ አይቀልም? “አሁን እስኪ ከዚህ ሁሉ የሰው ዘር አንድ ጀግና ጠፍቶ የምድሩ አልበቃ ብሎ ሰማይ ሲያቃጥለን ዝም ብለን እንይ?” ስለው፣ “ምን ታደርገዋለህ ሲሞቃቸው የማቀዝቀዣ ችግር የለባቸው። አፋጣኝ ዕርምጃ እንደ መውሰድ በቀጠሮ እየተገናኙ ተቀጣጥረው ይለያያሉ። ለፖለቲከኞች እኮ እንዲህ በቀላሉ አየር ንብረት አለው ብሎ ማመን ቀላል አይደለም፤” የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። የማለት መብት አለው። ይብላኝ በሐሩር ወጨፎ የመሰቃየት ግዴታ ለተጣለብን። እናላችሁ ናውዤ ራሴን እያዞረኝ ሙቀቱን መቋቋም ሲያቅተኝ በደመ ነፍስ ተጉዤ ቤቴ ደረስኩ።

ማንጠግቦሽ ሌላዋ ፀሐይ ሆና ጠበቀችኝ። “ብለህ ብለህ ገናን በሽሮ ልታስውለኝ ነው? ጎረቤት ምን ይላል? አታፍርም ግን? ከሌለህ የለኝም አትልም? ወዘተ፣ ወዘተ…” ከሰማኋት ያልሰማኋት ይበልጥ ነበር። ትንሽ ሰዓት ጋደም ብዬ ራስ ምታቱ አልፎልኝ ስነቃ ጀንበር አዘቅዝቃለች። ማንጠግቦሽ ግን የጎደለባትን መቁጠር አላገባደደችም። ዓመት በዓልና ሆድ፣ ታሪክና አፈ ታሪክ፣ እውነትና ሐሰት አግባብ ያላግባብ ተቀያይጠውብን የምንኖረው ሕይወት ያቀረሸኝ ጀመር። ወጣ ብዬ ንፋስ ልቀበል ባስብ ደግሞ ንፋስ ተሰዶ በበርበሬ ቁሌትና በሚነጠር ቅቤ ቃና ተተክቷል። ወዲያ ማዶ ውሪው ተሰብስቦ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እያለ ሳንቲም ይለቅማል። ውጥን የለሽ ኑሯችን፣ እንደ ደራሽ ውኃ ሕይወት ገፍታ በጣለችን ፌርማታ ተመሳስሎ ማደር የሚሰለች ነገር ሆኖብኛል። ሃይማኖት ከፖለቲካ ራቀ ሲባል ከሆድና ከገበያ ጋር ተጣብቆ ይታየኛል። ባሻዬ፣ “ዓለምን ለማዳን ክርስቶስ በበረት ተወለደ” እያሉ ሲሰብኩኝ በዳንኪራና በስካር ‘ሃፒ በርዝ ደይ’ የምንለውን እኛን እያየሁ ግራ ይገባኛል። ሃይ ባይ የሌለው ቀዬ መምህር አልባ ተማሪ ሆነናል። ጨዋታችን ሁሉ አይቆጡም ጌታ ከሆነ አልሰነበተም ብላችሁ ነው? ዳኛ አልባው ጨዋታ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? መጥኔ! መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት