Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርስለ ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ጥቂት ልናገር

  ስለ ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ጥቂት ልናገር

  ቀን:

  በማንኛውም ሚድያ የቃልም ሆነ የጽሑፍ መልዕክት አስተላልፌ አላውቅም፡፡ ዛሬ ግን ምቾት ያጣሁበትን የቴሌቪዥን ማስታወቂያ በተመለከተ ቁጣዬን የማበርድበት ባጣ ወረቀትና ብዕሬን አንስቼ ተሰተካከሉ ወይም አስተካክሉ  ማለትን ወደድኩ፡፡ ይህንን በማድረጌ የሚያነሳ  ቅሬታ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ማስታወቂያ ማለት እኮ አንድን ነገር፣ አዲስ ምርት ሊሆን ይችላል፣ ዕቃ፣ ኩባንያ፣ ሪል ስቴት፣ መሥሪያ ቤት፣ ሆቴል፣ የገበያ አዳራሽ፣ መዝናኛ ሥፍራዎች ወዘተ፣ በተለያየ መልኩ ሰው እንዲያውቀውና አትራፊ እንዲሆን መረጃ መስጠት ማለት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በተለያዩ ሚድያዎች መልዕክት ይተላለፋል፡፡ ማስታወቂያ ባለንበት ዘመን የመሠልጠን ምልክት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊና ጠቃሚ የንግድ ሥልት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሆኖም የማስታወቂያ ሥራ ራሱን የቻለ ሙያ እንደመሆኑ መጠን በዕውቀት ሊታገዝ ይገባዋል፡፡ በድሮ ዘመን ማስታወቂያ መንገር አዲስ ክስተት ስለነበር፣ ቀልደኞች በመኮመክ ቢያቀርቡት፣ ወቅቱ የሚፈቅደው ነው፡፡ ሰው እየሳቀ የተፈለገውን በዚያ ውስጥ መልዕክቱን ያገኘው ነበር፡፡  ቴክኖሎጂው በተራቀቀበት፣ አሻንጉሊት መጫወቻ መሆኑ ቀርቶ በድሮን (ሰው አልባ በራሪ ቁስ ሆኖ) መልክ በርካታ ቁምነገሮች  የሚከናወንበት ሆኗል፡፡ በዚህ  ዘመን ላይ እየኖርን ግን ተፈጥሮ ባልሆነ ቀልድ ማስታወቂያን ሲያቀርቡት ማየት ምናልባት ቢያናድድ እንጂ ለመልዕክቱ  ትኩረት የሚሰጥ  ይኖራል ማለት ያስቸግራል፡፡

  ማስታወቂያ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ትኩረት ሊስብ በሚችልና በቀላሉ ኅብረተስቡ ሊረዳው በሚችል መልኩ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከሕፃናት ጀምሮ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ የሚገኝ የኅብረተሰብ ክፍል ይከተለዋል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተማረ፣ ያልተማረ፣ የተለያየ አመለካከትና ባህል፣ እምነትና ልምድ ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉንም ሊደርስ ይችላል ተብሎ ታስቦበት፣ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ፣ ከፍተኛ ጥናት ተደርጎበት፤ ከመተላለፉ በፊትም የማስተካከያና ዕርምት፣ በሌሎች ልምድ ባካበቱ ሙያተኞች ጭምር ግምገማ ተደርጎበት ሊቀርብ ይገባል እላለሁ፡፡  

  አንዳንዴ በቴሌቪዥን የምናያቸው ማስታወቂያዎች፣ ማስታወቂያ ይሁን አጭር ድራማ መልዕክቱ እንኳ ሳይገባን ግራ አጋብቶን ያልፋል፡፡ ለምሳሌ የሳሙና ማስታወቂያ (በበኩሌ ብዙም ባልደግፈውም) ሁለት የተለያዩ ሳሙናዎችን አንድ ግለስብ አድንቆ ለሁለቱም ተመሳሳይ ማስታወቂያ ሲሠራላቸው እንድንገዛው  ሳይሆን  ይቅርባችሁ  የሚለን ይመስላል፡፡  አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ማስታወቂያዎቹ በአጭር ደቂቃዎች ልዩነት ተደጋግመው ይቀርባሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ እንኳ ማስታወቂያውን ቴሌቪዥኑንም እንድንዘጋ  ይጋብዛል፡፡

  በዛሬው ዕይታዬ መናገር የፈለኩት ከሰሞኑ ያየሁትን የቢራ ማስታወቂያ ነው፡፡ አሉን የምንላቸው የመድረክ ሰዎች ይታዩበታል፡፡  አንዲት ወጣት ወንዶች በተሰበሰቡበት መጠጥ ቤት ውስጥ በትልቅ ብርጭቆ በአንድ ትንፋሽ ስትጨልጥ ትታያለች፡፡ አብረዋት ያሉት ወንዶች በአግራሞትም በድንጋጤም  ይመለከቷታል፡፡ ብራቮ  የሚሉም ይመስላሉ፡፡ ስትጨልጥ ያልኩት በመጠጣትና በመጨለጥ መሀል ያለውን  ሰፊ ልዩነት ለማሳየት ነው፡፡ የቢራው አልኮል መጠን ከነበረበት መጠን 0.5 በመቶ በመቀነሱ፣ አያሰክርም ለማለት የተፈለገም ይመስላል፡፡ ወንዶቹ  አይከብድሽም? ብለው በድንጋጤ ይጠይቋታል፡፡ የአጠጣጧን አስደንጋጭነት ማስታወቂያ ሠሪዎቹም አልሸሸጉም፡፡      

  ከ18 ዓመት በታች ያሉት እንዳይጠጡ የተከለከለ፣ በኃላፊነት ይጠጡ እየተባለ በሌሎች ማስታወቂያ በየጊዜው እየተነገረ እያለ፣ ወጣት ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወጣት ወንዶችንም የሚቀሰቅስ ማስታወቂያ መሥራታቸውን አላስተዋሉትም፡፡ መልዕክቱ ተቃርኖ ነው፡፡ ከ18 ዓመት በታች ያሉ እንዳያዩት በዚሁ ማስታወቂያ ቢነገር መልካም ነበር፡፡

  ከዚህ ባሻገር ቴሌቬዥንም የድምፅ ጥራት ቁጥጥር ይኑረው፡፡ ማስታወቂያ ሲነገር ይጮሃል፡፡ ሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ግን ይቀንሳል፡፡ በአንድ ሰዓት ውስጥ የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች አይደጋገሙ። እርግጥ ነው የቢራው ብዛትና ማስታወቂያው ተበራክቷል፡፡ የተለያየ የቢራ ማስታወቂያ በየደቂቃው በመተላለፉ መለየት እስኪያቅተን ድረስ ግራ አጋብቶናልና በጥንቃቄ ይሠራ፡፡

  (ሁሉባንቺ  ዓለሙ፣ ከአዲስ አበባ) 

  *********

  አሁን ነው መሮጥ

  ጊዜው ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈ አንድ ማስታወቂያ ነበር፡፡ አንድ የጫማ ቀለም ለማሻሻጥ ተብሎ የተሠራ ነው፡፡ ‹‹ማምለጥ ነው የሚሻለው ለጫማው በኋላ ይታሰብበታል፤›› የሚለውን ማስታወቂያ የሠራም ያዘጋጀውም ታዋቂው የማስታወቂያና የትወና ጥበበኛ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ይመስለኛል፡፡ ፈጣኑ አቦሸማኔ ከሯጩ ኋላ ሆኖ እየጋለበ ሲመጣ ትዕይንቱ አድራጊው ተጨንቆና ተጠቦ በጭቃ በተዋጠው ረግረግ፣ እየሰጠመ ነብሱን ለማዳን ሲጥር ይታያል፡፡ ትዕይንቱ ድንቅና አይረሴ ተውኔት ነበር፡፡

  ይህን የገለጽኩላቸው ለጽሑፌ መነሻ ይሁነኝ ብዬ ነው፡፡ በዚሁ አጭር መነሻ ያሳሰበኝ ጉዳይ ግን የሚከተለው ነው፡፡

  አገራችን አሁን የደረሰችበት ‹‹የልማት›› ደረጃ ትልቅ ነው፡፡ ለውጥ መኖሩን ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የአፍሪካ መዲና ከተማችንን ተዘዋውሮ መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡ እስከ ህዳሴ ግድብ ከሄድን ደግሞ ጅምራችን ‹‹ዓለም አቀፋዊነቱን›› ያረጋግጣል፡፡ አላጠናቀቅንም፡፡ ገና ነን፡፡

  እንግዲህ ይህ ሁሉ ሆኖም ከፍተኛ የአስተዳደር ችግሮች እየታዩ መሆኑን አውቀናል፡፡ ከችግሮቹ ሁሉ ግን የብር መዳከም አሳሳቢ ነው፡፡ በአንዳንድ አስተዳደር ክልሎች ‹‹ኤልኒኖ››ም ያምጣው ‹‹ሰው ሠራሽ›› ብቻ ድርቅ መከሰቱ ታውቆ መንግሥት ችግሩን ለማስወገድ እየተረባረበ መሆኑ በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ 

  ይሁንና ‹‹የገንዘብ የመግዛት አቅሙ›› መውደቁ ግን ለምን ቸል እንደተባለ ብናውቅ ጥሩ ነበር፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቀጣሪዎች ከወር ደመወዛቸው እስከ 35 በመቶ ታክስ እየተቆረጠባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ለሕክምና ‹‹ለጤና መድኅን›› ተብሎ ሦስት በመቶ ተጨማሪ ቅነሳ ይኖራል መባሉ አሳሳቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ተቀንሶ ገበያ ውስጥ ሲገባ፣ ግዥ ሲፈጸም አሁን በየአገልግሎቱና በዕቃ ግዥ ላይ 15 በመቶ ቫት ሲቆረጥበት እንግዲህ ምን ሊቀረው ነው? የልጆች፣ የትምህርት ቤትና ሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች ታክለውበት ኑሮ ምኑን ይችላል? አጨብጭቦ ባዶ እጁን መቅረት አይደለም ወይ?

  ‹‹ንፋስ በተነሳ ጊዜ እሳት አይጫርም፤›› የሚል አባባል አለ፡፡ ስለዚህም ሁኔታውን በርጋታ መንፈስ ተመልክተን ችግሩን በምን መልኩ እንቀንሰው? የሚል የመፍትሔ ሒደት ሊመቻችለት ይገባል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው የመንግሥት አስተዳደር አካላት ሳይውል ሳያድር ‹‹ትኩረት›› ይሰጡበታል የሚል ግምት አለኝ፡፡

  ‹‹አሁን ነው መሮጥ›› ያልኩትም የኑሮ ውድነቱን ሊቀንሱ የሚያስችሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰድ ስላለባቸው ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ ‹‹ብልህ ሲሳሳት ከገልቱ ይብሳል፤›› የሚለው አባባል እንዳይሆን ከአሁኑ ዘዴ ለመቀየስ እንሩጥ፡፡ አሁን ነው መሮጥ!

  (ታዛቢ፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img