Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየገናን በዓል ስናስብ የምናስታውሳቸው የሕግ ነጥቦች

የገናን በዓል ስናስብ የምናስታውሳቸው የሕግ ነጥቦች

ቀን:

በአገራችን ከሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ውስጥ ገና አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል በክርስትና አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መታሰቢያ ነው፡፡ ከፈረንጆቹ ገና በአንድ ሳምንት ዘግይቶ የሚከበረው ይህ ሃይማኖታዊ በዓል በሁሉም ክርስቲያን ቤተ እምነቶች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡ የቱሪስት መስህብ በሆነው በደብረ ሮሃ ላስታ ላሊበላ ያለው አከባበር ደግሞ ከሁሉም የተለየና የሚማርክ ነው፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ካህናት ከላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው በቤተ ማርያምና በዙሪያው ባለው የማሜ ጋራ ዝማሬው በጥንግ ድርብና በጧፍ ታጅቦ ይከበራል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንደሚገልጹት በጋራው ላይ የሚያሸበሽቡት ካህናት የመላዕክት፣ በጋራው ሥር የሚያሸበሽቡት ካህናት ደግሞ የሰው ልጆች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ካህናትና ሰዎች በአንድነት ኢየሱስ ክርስቶስን ያመሰገኑበት ምሳሌ መሆኑ በበዓሉ በስፋት ይነገራል፡፡ የገና ባህላዊ በዓልነቱ በአብዛኛው በገጠራማው የአገራችን ክፍል የሚስተዋል ቢሆንም፣ የተወሰኑ የባህሉ ቅሪቶች በአንዳንድ ከተሞችም አይጠፉም፡፡ በዓሉን በባህላዊ ጭፈራ፣ በገና ጨዋታ፣ ባህላዊ ልብስ ለብሶ ማክበር የተለመደ ነው፡፡ ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የሚለው ብሂል እንደሚያስረዳው ሁሉም ወጣት ከቤቱ ወጥቶ በሜዳ ላይ በጨዋታ፣ በደስታና በሐሴት ያከብረዋል፡፡ እንደሌሎች በዓላት ሁሉ በገና በዓል ድፎ መጋገር፣ ሰንጋ መጣል፣ ጠጅና ጠላ መጎንጨት የተለመደ ነው፡፡ እንደ ፈረንጆቹ የበዛ ባይሆንም በዚህ ጊዜ ስጦታ መስጠት የበዓሉ ዓቢይ መገለጫ ነው፡፡

ሕግ የኅብረተሰብን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ስብጥር የሚገዛ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ የበዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ኩነቶች በአንድም በሌላ የሕግ ጥበቃ የሚሰጣቸው፣ የሕግ ጭብጦችም የሚነሱባቸው ናቸው፡፡ ለበዓሉ የሚደረጉ ግብይቶች፣ ስጦታዎች፣ የአከባበር ሥርዓቶች ወዘተ. ሕግ ነክ ጉዳዮችን የሚያስነሱ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሕጉ የገና በዓል ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ኩነቶች ላይ ምን ይዘት እንዳለው ለግንዛቤ በሚረዳ መልኩ በአጭሩ በዚህ ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡

የገና ስጦታ

የገና በዓል ሲከበር የቅርብ ሰዎች (ጓደኛሞች፣ ፍቅረኛሞች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ቤተ ዘመድ ወዘተ.) መካከል ስጦታ መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ስጦታው ከተራ ተንቀሳቃሽ ዕቃ ጀምሮ የማይንቀሳቀስ ንብረትንም መስጠት የሚያካትት ሊሆን ይችላል፡፡ በፈረንጆቹ ከገና በዓል ለጥቆ የሚመጣውን አዲስ ዓመታቸውን በማሰብ የቤት ዕቃዎች፣ መኪናዎች፣ ቤቶች ወዘተ. መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ጸሐፊው የገና ስጦታ መነሻን በተመለከቱ ጽሑፎች ባይመለከትም፣ የገና ስጦታ መነሻ ሃይማኖተዊ እንደሆነ ማሰብ አሳማኝ እንደሆነ ያምናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናነበው በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ክፍል በቤተልሔም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ወርቅና፣ ከርቤ፣ እጅ መንሻም ሰጥተውታል፡፡ የገና ስጦታ መነሻም ይሄው ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንደሚናገሩት ሰዎች ወርቅ፣ እንስሳት ደግሞ ትንፋሻቸውን በበረት ለተወለደው ለኢየሱስ ክርስቶስ በስጦታ መልክ አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ዘመን በገና የሚፈጸመው ስጦታ ግን ለሰዎች የሚፈጸም ሲሆን፣ ስጦታው ሕጉ በአስቀመጠው መስፈርት ወይም ፎርም ካልተሰጠ በሕግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በገና ወቅት በተለይ ከፍ ያለ ስጦታ (መኪናና ቤትን የመሰለ) የሚሰጥ ሰው ሕጉ ስለ ስጦታ ምን እንደሚል ማወቁ ለግንዛቤ ይረዳዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2427 ‹‹ስጦታ›› ማለት ‹‹አንድ ወገን ተዋዋይ ማለት ሰጪው ተቀባይ ተብሎ ለሚጠራው ለሌላ ሰው ችሮታ በማድረግ ሐሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት ወይም ግዴታ የሚገባበት ውል ነው፤›› በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጋችን ከቁጥር 2427 እስከ 2470 ድረስ ስጦታ ስለሚባሉና ስለማይባሉ ድርጊቶች፣ የስጦታ ውል ሊያሟላቸው ስለሚገባቸው መስፈርቶች፣ ስጦታ ስለሚሻርበት ሁኔታ ወዘተ. በዝርዝር ይደነግጋሉ፡፡ ስጦታ የሰጪ የራሱ (Personal) ተግባር ሲሆን ሰጪው በትክክለኛ አዕምሮ፣ ስጦታውን በሚሰጥበት ወቅት የራሱ የሆነን ንብረት የተመለከተና ከስህተትና ከተንኮል ነፃ በሆነ መልኩ ሊፈጸም ይገባል፡፡ ስጦታ የፀና የሚሆነው ሰጪው ስለሰጠ ብቻ ሳይሆን ተቀባዩም ለእርሱ የተደረገውን ልግስና እቀበላለሁ ብሎ ሐሳቡን ሲገልጽ እንደሆነ ሕጉ በአንቀጽ 2437 ደንግጓል፡፡

ሕጉ የስጦታ ሥርዓት ፎርም ያስቀመጠ ሲሆን፣ ሕጉ ባስቀመጠው ሥርዓት ስጦታው ካልተፈጸመ በሕግ ፊት ዋጋ የለውም፡፡ በማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብትን የሚሰጥ ስጦታ በግልጽ በሚደረግ ኑዛዜ አሠራር ዓይነት ካልተደረገ ፈራሽ ነው፡፡ በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ የሚባለው ተናዛዡ እየተናገረ ማናቸውም ሌላ ሰው ወይም ተናዛዡ ራሱ የሚጽፈው ነው፡፡ ኑዛዜው በተናዛዡና በአራት ምስክሮች ፊት ካልተነበበና ይህም ሥርዓት (ፎርማሊቲ መፈጸሙንና የተጻፈበትንም ቀን የሚያመላክት) ካልሆነ በቀር ፈራሽ ነው፡፡ ተናዛዡና ምስክሮቹ በኑዛዜው ላይ ወዲያውኑ ፊርማቸውን ካላደረጉበት ፈራሽ ነው፡፡ (የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 881) ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የተመለከተ ስጦታ ሰጪው እየተናገረ፣ በእርሱ ወይም በሌላ ካልተጻፈና በአራት ምስክሮች ካልተረጋገጠ፣ ይህ ሥርዓት ስለመፈጸሙም የሚገልጽ የጽሑፍ ሰነድ ከሌለ በቀር በሕግ ተቀባይነትን አያገኝም፡፡ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረግ ስጦታ በመዝጋቢ አካል ፊት መደረግና መመዝገብ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው በሕግ ባለሙያዎች መካከል አከራካሪ ነው፡፡ አንዳንዶች የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1723 መሠረት ስጦታው ከላይ በተገለጸው ሥርዓተ ከመፈጸም ባለፈ በአዋዋይ ፊት መፈጸምና መመዝገብ አለበት የሚል አቋም ይወስዳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሕጉ ስለ ስጦታ በደነገገበት ክፍል የማይንቀሳቀስ ንብረት ስጦታ መመዝገብ እንዳለበት ስለማይገልጽ መመዝገብ እንደማያስፈልገው ይከራከራሉ፡፡ በአዋጅ ገዥ ፍርድ የመስጠት ሥልጣን ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሁለተኛውን አቋም በመደገፍ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

ከማይንቀሳቀስ ንብረት ውጭ ባሉ ንብረቶች ላይ የሚፈጸሙ ስጦታዎች ግን የተለየ ሥርዓት አያስፈልጋቸውም፡፡ ግዙፍ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችና ለአምጪው የሚከፈሉ ሰነዶች እጅ በእጅ በሚደረግ ማስተላለፍ ብቻ ሊሰጡ ይቻላል፡፡ ሰጪው ከፈለገም ለማይንቀሳቀስ ንብረት ስጦታ አስፈላጊ የሆነውን ሥርዓት ሞልቶ ሊሰጥ እንደሚችል ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ በገና በዓል የሚሰጡ ስጦታዎች በሕግ ፊት ዋጋ እንዲኖራቸው ሕጉ ያስቀመጠውን ሥርዓት ሊከተሉ እንደሚገባ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ በግልጽ ኑዛዜ አፈጻጸም ሥርዓት፣ ሌሎች ተንቀሳቃሾች ከሆኑ (መኪና፣ ኮምፒዩተር፣ ቲቪ፣ የቤት ዕቃ፣ ሽቶ፣ ልብስ ወዘተ.) ደግሞ እጅ በእጅ በማስተላለፍ ብቻ ስጦታን መፈጸም ይቻላል፡፡

የገና ዛፍ

በገና በዓል ከሚስተዋሉ ኩነቶች አንዱ ቤትን በገና ዛፍ ማስጌጥ ነው፡፡ የገና ዛፍ በአብዛኛው ከሰፈር ወይም ከዱር የሚገኝ የጥድ ዛፍን በመቁረጥ የሚሠራ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በዋና ከተማዎች ካልሆነ በቀር በገጠራማ አካባቢዎች አሁንም ለደን ጭፍጨፋ ምክንያት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በከተማ አካባቢ የገና ዛፍ በገና የፕላስቲክ ዛፍ በመተካቱ የዛፍ ጭፍጨፋውን እንደቀነሰው ይገመታል፡፡ ልማዱ ባልቀረባቸው የአገራችን ክፍሎች ግን የገና ዛፍ መቁረጥ በንጹህ አካባቢ የመኖር መብትን  ችግር ላይ የሚጥል፣ ለደን ጭፍጨፋ ዓቢይ ምክንያት መሆኑ አይቀርም፡፡

የገና ዛፍ ኢትዮጵያዊ ባህል አለመሆኑን ብዙ መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ልማዱ ከክርስቶስ ልደት በፊት የሚፈጸም በግሪክ የነበረ የባዕድ አምልኮ መገለጫ መሆኑን በመተንተን ከገና በዓል ጋር ያለውን ቀጥተኛ ተቃርኖ ይገልጻሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የገናን ዛፍና ሕግን የሚያገናኙ የሕግ ድንጋጌዎች አይጠፉም፡፡ ግንኙነታቸው አሉታዊ በመሆኑ የወንጀል ሕጉ ያለፈቃድ ዛፍን መቁረጥ፣ ደንን መጨፍጨፍ በአጠቃላይ ዕፅዋትን አለመጠበቅ የወንጀል ተግባር መሆኑን አስቀምጧል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 850 ማንም ሰው ብሔራዊ ዕፅዋትንና ደንን፣ እንስሳትንና የዱር አራዊትን ስለመጠበቅ የወጣውን ሕግ፣ ደንብ ወይም መመርያ የጣሰ እንደሆነ በመቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ ደኖች ከተጨፈጨፉ፣ ዛፍ ያለአግባብ ከተቆረጠ በረሃማነት ስለሚስፋፋ በንጹህ አካባቢ የመኖር የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ይሆናል፡፡ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 542/99 ከግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ወይም የግብርና ቢሮ ፈቃድ ሳይሰጥ ዛፍ መቁረጥን ይከለክላል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት  ያለአግባብ ዛፍ የቆረጠ ከአንድ ዓመት በማያንሰና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራትና በብር 10000 እንደሚቀጣ በአንቀጽ 20 ላይ ተደንግጓል፡፡ ዛፍ የቆረጠው ሰው እጅ ከፍንጅ ከተያዘ ጉዳዩ የሚታየው በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት እንደሆነም አዋጁ ደንግጓል፡፡ ስለዚህ የገና ዛፍ በመቁረጥ በዓሉን በማረፊያ ቤት ላለማሳለፍ ባህላችን ያልሆነውን የገና ዛፍ ማዘጋጀት ካስፈለገ እንኳን በፕላስቲክ መተካት አማራጭ የለውም፡፡

የገና በዓል ገበያ

የገና በዓል በአገራችን ሲከበር ሰንጋ ተጥሎ፣ የወይን ጠጅ (ጠላ) ተጠምቆ፣ ከመብል ጋር  በተያያዘ የሚከበር በመሆኑ በገበያው ከሚበላው ከሚጠጣው ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ወንጀል ይስተዋላል፡፡ ለጤንነት ጎጂ የሆኑ ምግቦች ማምረት፣ ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል ወይም አደገኛ ወይም የተበላሹ ምግቦችን ማቅረብ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፉ ምግቦችን በአደባባይ መሸጥ፣ ቅቤን በሙዝ፣ በርበሬን በሸክላ መቀላቀል፣ የተወጋ ውስኪ መሸጥ በበዓላት ሰሞን በብዛት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በዓል የሚያከብረው ሰው የምግብ ሸቀጦችን ሲገዛም ማጭበርበር ይፈጸምበታል፡፡ ሸቀጦች በተጋነነ ዋጋ ይሸጣሉ፣ በሚዛን ይጭበረበራል፣ ያልገዙትንም ነገር ተጠቅልሎ ሊሰጥ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ በበዓል ሰሞን በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ እንሰማለን፡፡ በዓል አክባሪው ሕዝብ እነዚህ ወንጀሎች መፈጸማቸውን እንዳያውቅ የገበያ ግርግሩ ይከለክለዋል፣ ቢያውቅም ማስረጃ አይኖረውም፣ ማስረጃ ቢኖረውም ለመክሰስ የበዓል ሰሞን የአዕምሮው ሁኔታ አይፈቅድለትም፡፡

ሕጉ ግን ለእንደዚህ ዓይነት ያልተገቡ ድርጊቶች የሚያስቀምጠው መፍትሔ አለ፡፡ ለአብነት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 527ን ብንመለከት የሚጎዱ ወይም የተበላሹ ዕቃዎችንና ምግቦችን መሥራት መሸጥ እንዲሁም ጥራታቸውን ማርከስ ወንጀል ስለመሆኑ ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ‹‹ማንም ሰው አስቦ ምግቦችን፣ ቀለቦችን፣ በምግብነት የሚያገለግሉ ነገሮችን ጎጅ ወይም የተበላሸ ይዘት እንዲኖራቸው በማድረግ የሠራ እንደሆነ ወይም የዕቃዎቹን ጥራት ያረከሰ እንደሆነ ወይም ጎጅ የሆኑ የዚህ ዓይነት የምርት ውጤቶችን ያከማቸ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ወደ ውጭ የላከ ወይም ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ የተቀበለ፣ ወይም ያከፋፈለ እንደሆነ ከስድስት ወር በማያንስ ጽኑ እስራትና መቀጮ ይቀጣል፡፡›› ከዚህ በተጨማሪ የሚጎዱ ወይም የተበላሹ ዕቃዎችን ያመረተው፣ የሚሸጠው ወይም ያከፋፈለው ሰው ወንጀሉን የፈጸመው ከፍተኛ ብዛት ባላቸው ዕቃዎች ላይ ሲሆንና የደረሰውም ጉዳት ከባድ ሲሆን፣ ቅጣቱ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና ከ200 ሺሕ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡ እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች የተፈጸሙት በሕግ ሰውነት ባለው ድርጅት ከሆነ ደግሞ መቀጮው እስከ አምስት እጥፍ ሊደርስ ይችላል፡፡

ስለዚህ በዓሉን የሚያከብረው ሕዝብ ከእንደዚህ ዓይነት የወንጀል ድርጊቶች ራሱን መጠበቅ የሚገባው ሲሆን፣ ወንጀሉንም የሚፈጽሙ ሰዎች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ በዓሉን በማረፊያ ቤት ለማክበር እንደሚገደዱ ሕጉ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

የገና በዓልና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች

የገና በዓል ከባህላዊ መገለጫው በላይ ሃይማኖታዊ ይዘቱና የአከባበር ሥርዓቱ ሰፊ ነው፡፡ በዓሉ በሁሉም የክርስቲያን ቤተ እምነቶች በተለያዩ አምልኮና የአምልኮ መግለጫ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡ ቤተ እምነቶቹ ከሚከተሉት ዶክትሪን፣ ትውፊትና ከመጡበት ታሪክ አንፃር በዓሉን የሚያከብሩበት ሥርዓት፣ ሥርዓቱ የሚከወንበት የእምነት መገልገያ ዕቃና ዝማሬው የተለያየ ነው፡፡ ይህም ለአገራችን የእምነት ብዙኃነትና ተቻችሎ የመኖር ተላቅ አሻራ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቤተ እምነቶቹ በሚከውኑት ሥርዓት አንዱ የሌላውን እምነት የሚያንቋሽሽ፣  አንዱ ለዘመናት ይከውንበት የነበረውን የእምነት መገልገያ ዕቃ ዝማሬና አከዋወን ሌላው በአደባባይ ሲጠቀምበት መመልከት ጀምረናል፡፡ መንግሥትን የሃይማኖት አክራሪነት እጅጉን የሚያሳስብበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ቸል የማይባሉ እንደሆነ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡

አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን ቤተ እምነት የእምነት መገልገያ ዕቃና ሥርዓት የመጠቀምና ያለመጠቀም መብት ወይም የሌላውን የማክበር ግዴታ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27(1) ማንኛውም ሰው የሃይማኖት ነፃነት መብት እንዳለው ሲደነግግ አንቀጽ 27(5) ደግሞ ሃይማኖትን ወይም እምነትን የመግለጽ መብት ለሕዝብ ደኅንነት፣ ሰላም፣ ጤንነት፣ ትምህርት፣ የሕዝብ ሞራልና የሌሎችን መሠረታዊ መብቶች ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት የሚገደበው የሃይማኖት መብት ወይም የመረጡትን እምነት መያዝ ሳይሆን አገላለጽ ነው፡፡ የእምነት (የአመለካከት) መብት ፍጹማዊ በመሆኑ፣ አይገደብም፣ መገደብም አይቻልም፡፡ አገላለጹን በተመለከተ ግን በሕግ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሊገደብ ይችላል፡፡ ሃይማኖትን የመግለጽ መብት ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ገደብ ሊጣልበት ይችላል፡፡ የአንድ እምነት የአምልኮ ሥርዓቶች ኅብረተሰቡን የሚረብሹ፣ የሕዝቡን ሥርዓትና ደኅንነት የሚያናጉ፣ በኅብረተሰቡ ሕይወት፣ ሕልውናና ንብረት ላይ ከባድ አደጋ የሚያደርሱ ሆነው ከተገኙ መንግሥት ሕግ በማውጣትና ገደቡን በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ ገደብ ሊጥል ይችላል፡፡

በቤተ እምነት መካከል የሚታየው የአንዱን የአምልኮ መፈጸሚያ መሣሪያ ሌላው ያለ ፈቃዱ የመጠቀሙ ነገር ከዚህ እምነትን ከመግለጽ አንፃር የሚታይ ነው፡፡ አንዱ ቤተ እምነት ለዘመናት ሲዘምርበት፣ ሲያመሰግንበት የቆየበትን ሥርዓትና የአገልግሎት መጠቀሚያ ሌላው ሲጠቀም በአማኞቹ መካከል አለመግባባት መከሰቱ አይቀርም፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ችግሩን ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› መፍትሔ ለመስጠት የሚችሉት ቤተ እምነቶችና መንግሥት ናቸው፡፡ ቤተ እምነቶቹ አንድ በሚያደርጓቸው ማኅበራዊና አገራዊ ነገሮች ላይ አብረው የሚሠሩትን ያህል እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችም ለመቻቻል ፈተና እንዳይሆኑ ተነጋግሮ መፍታት ይገባል፡፡ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ታሪክን፣ የቤተ እምነቶቹን ሥርዓት፣ ትውፊታቸውንና የዳበረ ልማድን መሠረት አድርጎ ላለመቻቻል መሠረት የሚሆኑትን ድርጊቶች ለመገደብ የሚያስችል መመርያ ወይም ደንብ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ የገና በዓል ስናከብር መንፈሳዊና ባህላዊ ኩነቶችን ብቻ ሳይሆን ሕግ ነክ ጉዳዮች እንዳሉትም ማስተዋል ጠቃሚ ነው፡፡ በበዓሉ ያከናወናቸው ድርጊቶች ሕጉን የተከተሉ እንደነበሩ ጸሐፊው እምነቱ  ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...