Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ለወሰን ማስከበር ችግር በዋናነት መፍትሔ መስጠት ያለበት መንግሥት ነው››

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ገምሹ በየነ፣ የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተደጋግሞ እንደሚነሳው የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቅ ጐልቶ የሚታይ ችግር ሆኗል፡፡ የመንገድ ግንባታ ባለቤቶች የሆኑት እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቅ እንደዋነኛ ምክንያት የሚነሳው የወሰን ማስከበር ችግር ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየት ከዚሁ የወሰን ማስከበር ችግር ጋር የተያዙ በመሆኑ ተፅዕኖውም የሰፋ ሆኗል፡፡  የመንገድ መዘግየት ዋነኛ መንስዔ የወሰን ማስከበር ችግር ይሁን እንጂ ተደጋጋሚ የዲዛይን ክለሳዎችም ለግንባታዎች መጓተት የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ የኮንትራክተሮችም አቅም ማነስም የማይታለፍ ነው፡፡ ለመንገድ ግንባታ መዘግየት እንዲህ ያሉ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም ረገድ አንዱ ኮንትራክተር ከሌላው መለየቱ አይቀርም፡፡

በወቅቱ ሥራቸውን ያለማስከበር ችግር ያለባቸው ኮንትራክተሮች እንዳሉ ሁሉ የተረከቡትን ፕሮጀክት ቀድመው አጠናቅቀው ያስረከቡ ኩባንያዎች መኖራቸውን መገንዘብ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከተቀላቀለ 10 ዓመታትን ያስቆጠረው ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የመንገድ ግንባታን ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት ማጠናቀቅ እንደሚችል ማመላከት መቻሉን የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ገምሹ በየነ ይናገራሉ፡፡ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን እስካሁን ገንብቶ ካስረከባቸውና እየገነባቸው ካሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዲማ-ፍየል ውኃ ፕሮጀክት፣ የመሃል ሜዳ-ዓለም ከተማ የአስፓልት ፕሮጀክት፣ የሐረር ባይፓስ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ይገኙባቸዋል፡፡ በተለይ ሁለቱን ፕሮጀክቶቹን ከማጠናቀቂያ ጊዜያቸው በፊት ማጠናቀቅ መቻሉን ኩባንያው ይገልጻል፡፡ በመንገድ ግንባታና በተለይም ግንባታዎችን ቀድሞ በማስረከብ አግኝተናል ባሉት ውጤት ዙሪያ ዳዊት ታዬ አቶ ገምሹ በየነን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮንስትራክሽን ኩባንያችሁ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ውስጥ ምን ያህል ተሳትፎ አድርጓል? የሥራ አፈጻጸማቸውስ ምን ይመስላል?

አቶ ገምሹ፡- እውነት ለመናገር የኮንስትራክሽን ኩባንያችን የትኛውንም ሥራ ከመረከባችን በፊት ምን መሥራት እንዳለበትና የሚሠራውን ሥራ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት በደንብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በተሰጠው ፕላን መሠረት ይሠራል፡፡ አንድ ፕሮጀክት ከተረከበ በኋላ ግንባታው ያልቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ በፊት ለማጠናቀቅ የሚሠራ ነው፡፡ የፕሮጀክቶቻችን የአፈጻጸም ሪፖርትም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኩባንያችሁ በመንገድ ግንባታዎች ላይ ብቻ ነው ወይስ በሕንፃና በሌሎች ግንባታ ሥራዎች ላይ ይሳተፋል?

አቶ ገምሹ፡- የሕንፃ ግንባታዎችን ከእህት ኩባንያችን ጋር ሠርተናል፡፡ ትላልቅ የሕንፃ ፕሮጀክቶችን ሠርተናል፡፡ አሁንም 22 ወለል ያለውን የኢሊሊ ሆቴል የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታ እየሠራን ነው፡፡ የኢሊሊ ሆቴልንም ግንባታ ያካሄድነው ራሳችን ነን፡፡ ነገር ግን ኩባንያችን በአንድ ሥራ ላይ ስፔሻላይዝድ አድርጐ መጓዝን ነው የመረጥነው፡፡ ይህንንም እየተገበርን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በየትኛው ዘርፍ ነው ስፔሻላይዝድ አድርገን እየተጓዝን ነው የምትሉት?

አቶ ገምሹ፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያለውን የመንገድ ግንባታ ማለቴ ነው፡፡ የመንገድ ግንባታውን መርጠን እሱን ስፔሻላይዝድ በማድረግ ነው እየሠራን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ውስጥ መቼ ነው የገባችሁት? እስካሁን ያላችሁ የሥራ ክንውን እንዴት ይመዘናል?

አቶ ገምሹ፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተለይ በመንገድ ግንባታ ሥራ አሥር ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡ መጀመሪያ የድሬዳዋ ደወሌና ድሬዳዋ ሐረር መንገድ ላይ በድንገተኛ ጥገና ዘርፍ ገብተን ሠርተናል፡፡ የድንገተኛ ጥገና በጣም አስቸጋሪ ሥራ ነው፡፡ እሳት የማጥፋት ዓይነት ሥራ ነው፡፡ አንዱ ላይ ሲበላሽ ሌላኛው ጋር ነው የምትሠራው፡፡ አስበህበት የምትሠራው አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ጥሩ አፈጻጸም ኖሮን ነው የወጣነው፡፡ ከዚያ ማይፀብሪ-ዲማ መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት በጥሩ ሁኔታ ለመገንባት ቀድመን አስበንበት የሠራነው ሥራ ስለነበር፣ የፕሮጀክቱ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ሳያልቅ ከሦስት ወር በፊት አስቀድመን ጨርሰናል፡፡ የማይፀብሪ-ዲማ የመንገድ ፕሮጀክትን ሥራ 90 በመቶ አካባቢ ባጠናቀቅንበት ወቅት ደግሞ የዲማ-ፍየል ውኃ ፕሮጀክትን በአጋጣሚ አሸነፍን ወደ ሥራ መግባት ችለን ነበር፡፡ ይህንንም ፕሮጀክት ከግንባታ ማጠናቀቂያው  ጊዜ በፊት ስድስት ወር ቀድመን ነው የጨረስነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ የአገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች አንድ የመንገድ ሥራ ተረክበው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አይጨርሱም ይጓተታል፡፡ እናንተ ደግሞ የተረከብነውን ሥራ ቀድመን እየጨረስን ነው ትላላችሁ፡፡ ይህ ምን ያህል ትክክል ነው፡፡ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት እያጠናቀቃችሁ ከሆነ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ገምሹ፡- በእኛ በኩል ሥራችንን ከማጠናቀቂያ ጊዜው በፊት ስለመጨረሳችን ማንም ሊመሰክር ይችላል፡፡ የመንገዱ ባለቤት የሆነው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም የሚታወቅ ነው፡፡ በመረጃም ያለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የግንባታዎች መዘግየት ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ በግንባታ መዘግየት የኮንትራክተሮች ችግር አይኖርም ማለት አይደለም፤ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ90 በመቶው በላይ የሚሆነው ከመንገዱ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር የተያዙ የወሰን ማስከበር ችግሮች ናቸው፡፡ በመንገድ ግንባታ ውስጥ ትልቅ ችግር ሆኖ የዘለቀውም ይህ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የእኛ ኩባንያ ከአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አንፃር ሲታይ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቂያ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት ግንባታዎችን የማጠናቀቅ ልምድ አለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አፈጻጸም አብዛኛዎቹ የውጭ ኩባንያዎች እንኳን ያላደረጉት ነው፡፡ እኛ ግን ቀድመን ለመጨረስ የቻልነው እያንዳንዱ ፕሮጀክቶቻችን በቅርበት የምንከታተልና ለሥራው ትኩረት መስጠታችን ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ከተረከብናቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ በአዘዞ ጐርጐራ መንገድ ፕሮጀክት ላይ የገጠመን የወሰን ማስከበር ችግር በምሳሌነት ይቀርባል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተፈጠረው የወሰን ማስከበር ችግር ኩባንያችን በሚታወቅበትና ሥራውን ቀድሞ ለማስረከብ የነበረው ጥረት ላይ እክል ይፈጥራል፡፡ በያዝነው ዕቅድ መሠረት እንዳንጓዝ አድርጐናል፡፡   

ሪፖርተር፡- በዚህ ፕሮጀክት ላይ ገጠመን ያላችሁት የወሰን ማስከበር ችግር ሥራውን ምን ያህል አጓትቷል? ችግሩስ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

አቶ ገምሹ፡- ይህ ፕሮጀክት ሁለት ዓመት ከሰባት ወር አካባቢ ወስዷል፡፡ ሥራው ግን መጠናቀቅ የነበረበት በሁለት ዓመት ከስድስት ወር ነበር፡፡ ሥራው ሳያልቅ የቆየውም ለመንገዱ ግንባታ ሊነሱ የሚገባቸው የተለያዩ ግንባታዎች ሊነሱ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የወሰን ማስከበር ችግር የሌለባቸው ቦታዎች ላይ ያለንን ኃይል አሰባስበን ግንባታውን አካሂደናል፡፡ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ላይም ሆነን ከፕሮጀክቱ ጠቅላላ ሥራ 67 በመቶውን ጨርሰናል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን የወሰን ማስከበር ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ በዚህ ምክንያት ሥራው ተጓትቷል፡፡ እስካሁን የሠራነውም ወሰን ማስከበር ችግር የሌለባቸውን ቦታዎች እየመረጥን በመሆኑ የተቆራረጠ ሥራ ነው የሠራነው፡፡ ችግሩ የእኛ ባይሆንም የኩባንያችን ስም እያስነሳ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደነገሩኝ ችግሩ ከእናንተ አቅም በላይ ከሆነ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂው ማነው?

አቶ ገምሹ፡- በወሰን ማስከበሩ ችግር የተፈጠረው መጓተት ያደረሰብንን ጉዳት አሳውቀን ማካካሻ እስከመጠየቅ እንሄዳለን፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የጠየቁትን ካሳ ለማግኘት ገፍተው የሄዱ የሉም፡፡

ሪፖርተር፡- በትክክል በኮንትራት ውላችሁ መሠረት ከእናንተ ውጪ ለተፈጠረ ችግር የሚገጥማችሁ ችግር ካለ፣ ካሳ እስከማግኘት መግፋት ያልቻላችሁት ለምንድነው?

አቶ ገምሹ፡- ይህ የራሱ ምክንያት አለው፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እዚሁ አገራችን ውስጥ ነው የምንሠራው፡፡ አቅማችንንም ያጐለበትነው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ባገኘነው ዕድል ነው፡፡ በጥቅሉ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተፈጠርን ነን፡፡ መንግሥት በሚሰጠው ድጋፍ እኛ ወደፊት እንድንጓዝና ሥራ እየሰጠን ነው፡፡ መንግሥት ኮንትራክተሮችን እያበቃ እኛ ወደ ካሳ ክፍያ ብንገባ ምን ይባላል? ብለን፤ ይህንን ሕመማችንን ይዘን ነው የምንጓዘው፡፡ አንድ ኮንትራክተር በተያዘለት ጊዜ ሥራውን ሲያጠናቅ ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥትም ይጠቀማል፡፡ ኮንትራክተሩም ተጠቃሚ ነው፡፡ ኮንትራክተር ፕሮጀክቱን በሦስት ወር ቢያሳጥር ቢያንስ ለሦስት ወር ከሚከፍለው ደመወዝ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሥራን ቀድሞ ማጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ፕሮጀክት በዘገየ ቁጥር ግን ብዙ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ኮንትራክተሩ ትልቅ ችግር ውስጥ ይገባል ሕዝቡም ይቸገራል፡፡ መንግሥትም እንዲሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሆን ብሎ ወይም ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር መዘግየት የለም እያሉኝ ነው?

አቶ ገምሹ፡- ኮንትራክተሩ በተሰጠው ውል መሠረት በትክክል ተለክቶ ተሰጥቶት ተግባራዊ ማድረግ ያልቻለ ኮንትራክተር ከጠያቂነት ይድናል ማለት አይደለም፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የእኛ ኩባንያ እንዲህ ያለው ነገር ውስጥ የለም፡፡ ሥራችንን በአግባቡ እየሠራን ነው፡፡ ኩባንያችን እንደ ኩባንያ የሰው ኃይልን ማሳደግና ጥራት ላይ እንሠራለን፡፡ ለጥራት የሚሰጠው ትኩረት አለ፡፡ በጥራት የISO ሠርቲፋይድም ነን፡፡ ሪፖርተር፡- በተለይ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተረከባችኋቸው ፕሮጀክቶች በማዘግየት የተጠየቃችሁበት ጊዜ የለም? ለዚህ ምን ማረጋገጫ አላችሁ?

አቶ ገምሹ፡- የማይፀብሪ-ዲማ መንገድ ግንባታው ተጠናቅቆ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት የተመረቀ ነው፡፡ በሥራውም የአካባቢው ነዋሪዎች ተደስተዋል፡፡ የምረቃ ሥርዓቱም በተለያዩ ሚዲያዎች ተሠራጭቷል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ከሦስት ወር በፊት በማስረከብም ትልቅ ታሪክ ሠርተናል፡፡ ከማጠናቀቂያ ጊዜው በፊት ሥራን ጨርሶ ማስረከብ ያልተለመደ ቢሆንም እኛ እያደረግነው ነው፡፡ የዲማ-ፍየል ውኃ ፕሮጀክትንም 24 ሰዓት በመሥራት ስድስት ወር አሳጥረን አስረክበናል፡፡ ስለዚህ ቀድመን በመጨረሳችን እንወደሳለን እንጂ በእኛ ችግር ዘግይታችኋል ተብለን የተጠየቅንበት ፕሮጀክት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ ግን ኩባንያችሁ ከተረከባችሁት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ያላጠናቀቃችሁት አለን እየተባለ ነው?

አቶ ገምሹ፡- ይህንን ለተመልካች መተው ነው፡፡ እኛ እንዲህ ነን ማለቱ ላይጠቅም ቢችልም፤ የሥራ አፈጻጸማችን ምን ያህል እንደሆነ በመረጃ የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ ሥራችንን ስለምናውቅ በእኛ ምክንያት የዘገየ የመንገድ ፕሮጀክት የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ግንባታዎችን ሊያዘገዩ የሚችሉ የዲዛይን ለውጥ እንኳን ቢኖር ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ዲዛይን አሠርቶ እስከመስጠት የደረሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ገምሹ፡- ለምሳሌ የመሃል ሜዳ ዓለም ከተማ ፕሮጀክትን በምንሠራበት ወቅት መሃል ላይ የዲዛይን ችግር እንደነበረበት ይታወቃል፡፡ በዚሁ ምክንያት የፕሮጀክቱ ሥራ ቆሞ ነበር፡፡ ምንም መፍትሔ ባለመሰጠቱ እኛ አማካሪ ቀጥረን ዲዛይን አሠርተንና አፀድቀን ወደ ሥራ እንዲገባ እስከማድረግ ሄደናል፡፡ ይህ ባይሆን ሥራው ተስተጓጉሎ የፕሮጀክቱ ሥራ ይጓተት እንደነበር ምንም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አልነበረም፡፡ እኛ በራሳችን ተነሳሽነት የሠራነው ሥራ ግንባታው በአግባቡ እንዲካሄድ አስችሏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን የሚያዘገይ ነገር ሲፈጠር፣ ለካሳ ጥያቄ ከመሯሯጥ መፍትሔ ማበጀቱ ይሻላል በሚል የወሰድነው ዕርምጃ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የዲዛይን ችግር ሲያጋጥም የውጭ ኮንትራክተሮች ቢሆኑ አጋጣሚው ሠርግና ምላሽ ይሆንላቸው እንደነበር አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የካሳ ኤክስፐርቶች አሉዋቸው፡፡ አገራቸው እዚህ አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አድርገነው የካሳውን ገንዘብ ይዘው ቢሄዱ ስማቸው የሚጠራበት ምክንያት የለም፡፡ እኛ ደግሞ ያለን ደንበኛ አንድ ነው፡፡ ተመልሰን ብንመጣ ነገስ እንዴት እንሠራለን የሚለውንም እናስባለን፡፡ ለመሃል ሜዳ ዓለም ከተማ ፕሮጀክት ለተፈጠረው ችግር 140 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቀን ዝም ብለናል፡፡ ግን ይህንን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በተፈጠረ ችግር ሥራው ለአንድ ዓመት ተስተጓጉሎብን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በየፕሮጀክቶቹ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የካሳ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ በኮንትራት ስምምነታችሁ መሠረት ችግሩ አለ፡፡ ካሳውን ልታገኙ ይገባ ነበር፡፡ ሥራውን የሚያስተጓጉሉና ከእናንተ ውጪ ለሆኑ ችግሮች ለተፈጠሩ ጉዳቶች ካሳ ማግኘት ሲገባችሁ፣ ይህንን በመተዋችሁ እናጣለን የምትሉት ገንዘብ ከፍተኛ ከሆነ እንዴት ነው ኩባንያችሁን የምታስቀጥሉት?

አቶ ገምሹ፡- እንዴት ለሚለው መልሱን አንተም ልትመልሰው ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በተወሰነ ደረጃ ወደ ላይ ይወጡ ይወጡና መጨረሻ ላይ ቁልቁል ይሄዳሉ፡፡ ይህ በብዙ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ አንደኛ የፋይናንስ ማኔጅመንታችን እንዴት ነው? የሚለውን ወደ ራሳችን እናያለን፡፡ ሁለተኛ የዲዛይን ችግር ቢኖር እንኳን እንደ ኮንትራክተር እኛን ባይመለከተንም፣ ምን ያህል ሠርተን እናቀርባለን? ለሚለውም ጥያቄ መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛው ግን የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው መሥሪያ ቤትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የዲዛይን ችግር ሲያጋጥም እያንዳንዳቸው በቅርበት ተከታትለው መፍታት ካልቻሉ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች አያድጉም፡፡ ቢያድጉም ዕድገታቸውም አዝጋሚ ይሆናል፡፡ ወደ ውጭ ሄደው የውጭ ምንዛሪ ሊያመጡ ይችላሉ የሚለው ነገርም እንዳይሳካ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን አውቆ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በወሰን ማስከበር ችግር በተፈጠረ ቁጥር ፕሮጀክቱ ላይ መሣሪያዎች ያለሥራ ይቆማሉ፡፡ ሠራተኞችም እንዲሁ ሥራ ፈተው ይቀመጣሉ፡፡ ይህንን ወደ ገንዘብ ብትለውጠው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ሥራ እንደሌላው ቢዝነስ ሳይሆን አንድ ችግር ሲያጋጥመው በቀን በሚሊየኖች ብር ነው የሚከስረው፡፡ ስለዚህ ኩባንያው ዕድሜ አጭር ይሆናል፡፡ ሞቱ ይፈጥናል፡፡ ተመልሶ ለመነሳት እንኳን ከባድ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኮንትራክተሮች እንዲህም ያለ ችግር አለብን ካላችሁ በተለይ ወሰን ማስከበር ችግር ትልቅ ማነቆ እየሆነ ከመጣ መፍትሔው ምንድነው?

አቶ ገምሹ፡- በእኔ ግምት ሥራውን በአግባቡ የሚሠሩትን አጉልቶ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ እንዲጠናከሩ አቅጣጫ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ድክመት ያለባቸውም ካሉ መንግሥትም ደካማ ጐናቸውን ገምግሞ ወደ ሲስተም እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልተደረገ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እየወደቁ የሚሄዱ ከሆነ የያዙትን ሰፊ የሰው ኃይል መበተን ይመጣል፡፡ ሊከፍሉ የሚችሉትንም ግብር ሊያሳጣ ይችላል፡፡ በእኛ በኩል ግን የኩባንያችን ማኔጅመንት አባላት በሙሉ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለን አይደለም የምንሠራው፡፡ በየጊዜው ፕሮጀክቶቹ ባሉበት አካባቢ በመንቀሳቀስ፣ የፕሮጀክቶቹን ማኔጀሮች በየወሩ ስለምንገመግም ከተሳሳቱም ማረሚያ ስለምናደርግ በጥሩ ደረጃ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በእጃችሁ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ? እነዚህ መንገዶች ምን ደረጃ ላይ ናቸው?

አቶ ገምሹ፡- በእጃችን ካሉት ውስጥ አንዱ ሐረር ባይ ባስ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ችግር ያለበት ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክታችን ላይ ያሉ መሣሪያዎችን ያለ ሥራ ቆመዋል፡፡ ምክንያቱም አሁንም ድረስ የኤሌክትሪክና የቴሌ ምሰሶዎች አልተነሱም፡፡ ፕሮጀክቱ 21 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሪት ነው፡፡ ከዚህ የአስፓልት ኮንክሪት ውስጥ ብዙ ነገሮችን አሳልፈን ፕሮጀክቱ አሁን 98 በመቶ ላይ ነው፡፡ የቴሌ ታወሮች ከተነሱ ግን ቀሪው ሥራ በሁለት ወር የሚያልቅ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከተቀመጠልን የጊዜ ገደብ በፊት እናስረክባለን፡፡ አዘዞ-ጐርጐራንም ብንወስድ ከፍተኛ የወሰን ማስከበር ችግር ያለበት ነው፡፡ ችግሩን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያውቃሉ፡፡ መንግሥትም ያውቃል፡፡ ከአምስት ቀን በፊት እኔው ራሴ እዚያ ፕሮጀክት ላይ ነበርኩ፡፡ የወሰን ማስከበሩ ችግር እንዲፈታ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ የተሰጠበት፣ ስንት አቤቱታ የቀረበበት ቢሆንም የወሰን ማስከበር ሥራው እስካሁን አንዱም አልተሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከሆነ ስንት ዓመት ሆነው?

አቶ ገምሹ፡- ሦስት ዓመት ሊሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወሰን ማስከበር ችግር ካለበት ውጪ ያለውን የፕሮጀክቱ ክፍል ምን ያህል ሠርታችኋል?

አቶ ገምሹ፡- ከተሞች አካባቢ ከተቆራረጡት በስተቀር ሰኔ ሳይደርስ ያልቃል፡፡ የወሰን ማስከበር ችግር ያለባቸው ከተሞች አሉን፡፡ እነዚህን ትተን የወሰን ማስከበር ችግር የሌለባቸውና ሜዳ ሜዳውን ነው የምንሠራው፡፡ መሣሪያ እያጓጓዝን የሰው ኃይሉንም እያንቀሳቀስን ነው የምንሠራው፡፡ ይህ የኩባንያችን ወጪ ነው፡፡ ችግሩ ባይኖር ግን በተሻለ እንሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የወሰን ማስከበሩ ይፈታልናል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ገምሹ፡- ምንም ተስፋ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ ቀረ ማለት ነው? የታሰበው መንገድ ተስተጓጐለ ማለት ነው?

አቶ ገምሹ፡- እኛ ኮንትራት አለን፡፡ እንደ ኩባንያ አቋም ወስደህ፤ ኮንትራታችን ምን ይላል ብለህ ማየት አለብህ፡፡ የወሰን ማስከበር ችግር የሌለባቸውን ቆርጠን እየሠራን ነው፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህንን ቅድመ ሁኔታ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አሳውቀናል፡፡ ችግሩንም በሚገባ ያውቃል፡፡ እኔ እስከማውቀውም ባለሥልጣኑ ለየክልሎቹ ጽፏል፡፡ ለኢትዮ ቴሌኮምና ለመብራት ኃይል ለግንባታ እንቅፋት የሆኑትን ምሰሶዎች እንዲያነሱ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ እስካሁን የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ይህ ካልሆነ ያለውን ሥራ ጨርሰን መውጣት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው ችግር ከመንገድ ግንባታው መዘግየት ባለፈ ሌሎች ችግሮች አያስከትልም?

አቶ ገምሹ፡- ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ የተደጋገመ በመሆኑ እንደ ኮንትራክተር መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

አቶ ገምሹ፡- ለወሰን ማስከበር ችግር በዋናነት መፍትሔ መስጠት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ መንገዶች በክልሎች ውስጥ የሚሠሩ ናቸው፡፡ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ተጣምረው መሥራት አለባቸው፡፡ ሚዲያውም በቦታው ላይ ተኝቶ እያንዳንዱን ችግር ግልጽ እያደረገ ሕዝብም እንዲማርበት ማድረግ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ መንገድ ዘገየ ሲባል በኮንትራክተሩ ችግር ብቻ ይመስላል፡፡ ይህ እንዳልሆነና ታች ያለውንም ችግር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤ ማስጨበጥም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ አንዱ ሌላውን ጥፋተኛ ከማድረግ ውጭ ምንም ለአገር ይጠቅማል የሚባል ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ በተለይ ሚዲያው ትክክለኛ ነገር ይዞ መሥራት አለበት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች