በመንግሥት ውሳኔ ከፈረሰ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ኤጀንሲ፣ እንደ አዲስ ለተመሳሳይ ዓላማ በድጋሚ ሊቋቋም መሆኑ ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች አመለከቱ፡፡
ከንግድ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ በአሁኑ ወቅት በንግድ ሚኒስቴር ሥር በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተዋቅሮ የሚገኘውን የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ወደ ቀድሞ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ለመመለስ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥም የሕግ ማዕቀፉ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክና በምክር ቤቱ በሚወጣ ደንብ ተቋሙ በኤጀንሲ ደረጃ ተመሥርቶ፣ አገልግሎቱንም በፍጥነት እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሚቋቋመው ኤጀንሲ ለአገሪቱ የወጪ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለግ፣ እንዲሁም አሁን ባሉ የገበያ መዳረሻዎች ተጨማሪ የገበያ ዕድሎችን የመፍጠርና የማስፋፋት ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ስትራቴጂ በመቅረፅ ወደ ትግበራ እንደሚገባና በዋናነትም ለአገሪቱ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ምርቶች የገበያ መዳረሻ ማስፋፋት ተልዕኮው እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተመሳሳይ ኃላፊነት የነበረው ኤጀንሲ በ1991 ዓ.ም. በአዋጅ ተቋቁሞ ለአሥር ዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም፣ አጥጋቢ ባልሆነው እንቅስቃሴው ምክንያት መንግሥት በ2001 ዓ.ም. እንዲታጠፍ አድርጎት ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የገበያ ማስፋፋት ሥራው በራሱ መንገድ አልያም በላኪዎች ጥረት ብቻ ሲመራ ቆይቶ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ንግድ ሚኒስቴር የገበያ መዳረሻ የማፈላለግና የማስፋፋት ኃላፊነትን የያዘ ዲፓርትመንት በሥሩ ፈጥሮ ነበር፡፡
የቀድሞው ኤጀንሲ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረ ሲሆን፣ ከገበያ ማስፋፋት ተልዕኮው በተጨማሪ በአምራቾች፣ በላኪዎችና በአገልግሎት ሰጪዎች መካከል ቀልጣፋ ግንኙነት እንዲፈጠር የማበረታታት፣ ላኪዎች የሚገጥሟቸው ችግሮች እንዲወገዱ የማድረግ ኃላፊነቶች ነበሩት፡፡
በቅርቡ እንደሚቋቋም የሚጠበቀው የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዚህ ተቋም መመሥረት የንግድ ሚኒስቴርን በበርካታ ኃላፊነቶች ላይ የተበተነ አደረጃጀት እንዲወሰንና በንግድ ሥርዓትና ቁጥጥር ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያግዝ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ቀደም ሲል ይከታተለው የነበረው የቡና ኤክስፖርት በአሁኑ ወቅት በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር ወደተደራጀው የቡናና ሻይ ልማት ኤጀንሲ ተላልፏል፡፡
በተመሳሳይም የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች የወጪ ንግድም ለዚሁ ሚኒስቴር ሥር የተላለፈ ሲሆን፣ የቁም ከብት ወጪ ንግድ ዳይሬክቶሬት ደግሞ ወደ አሳና የቁም እንስሳት ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡ በመሆኑም የገበያ ማስፋፋት ኃላፊነት ወደሚቋቋመው ኤጀንሲ ሲተላለፍ፣ የንግድ ሚኒስቴር ትኩረት የንግድ ሥርዓቱን የማደራጀትና የመቆጣጠር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡