Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ ቦርድ የአይሻ ንፋስ ማመንጫ ፕሮጀክትን ለሁለት ኩባንያዎች እንዲሰጥ ወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሥራ አመራር ቦርድ የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያና ለቻይና ኩባንያዎች እንዲሰጥ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን፣ አገር በቀል ኩባንያ የሆነው መስፍን ኢንዱስትሪያልና የቻይናው ዳንግ ፋንግ ኩባንያ በጋራ 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት እንዲገነቡ ተወስኖላቸዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ሥራ አመራር ቦርድ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ተሰብስቦ ለዓመታት ሲንከባለል በቆየው በዚህ ፕሮጀክት ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ የተላለፈው ውሳኔ፣ የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ዳንግ ፋንግ ከራሱ የገንዘብ ምንጮች ፋይናንስ ይዞ እንዲመጣና ከአገር በቀሉ መስፍን ኢንዱስትሪያል ጋር በጋራ ግንባታውን እንዲያካሂድ ነው፡፡

ዳንግ ፋንግ ፋይናንስ ይዞ መምጣቱ ሲረጋገጥ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የግንባታ ውል እንዲፈራረም ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ ዳንግ ፋንግ የተለያዩ ድርድሮችን ካካሄደ በኋላ ከመስፍን ኢንዱስትሪያል ጋር ውል ይፈራረማል ተብሏል፡፡

አይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ በሶማሌ ክልል የሚገኝ ሲሆን፣ አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አመቺ የሆነ ንፋስ በሰፊው እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

በዚህ አካባቢ በተካሄደው ጥናት ከአንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በላይ ማመንጨት የሚችል አቅም ያለ ቢሆንም፣ ለግንባታ የቀረበው ግን ከዚህ ውስጥ 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህንን 300 ሜጋ ዋት የቻይናው ዳንግ ፋንግ፣ የጀርመኑ ላፕቶና አገር በቀሉ  ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጥያቄ አቅርበው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ለዓመታት ሲደራደሩ ቆይተዋል፡፡

ይህ ድርድር ረጅም ጊዜ የፈጀ ሲሆን በመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠው ለዳንግ ፋንግ ሆኗል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በትልልቅ ግንባታዎች ውስጥ አገር በቀል ኩባንያዎችን ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ውስጥ ተሳታፊ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ኢትዮጵያ ከንፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አላት፡፡

ዳንግ ፋንግ የሥራ አመራር ቦርዱ ያስቀመጠውን ፋይናንስን የመሳሰሉ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟላ ከሆነ፣ የግንባታ ውል በቅርቡ እንደሚፈራረም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች