ኒውሞንት የተሰኘ ግዙፍ የአሜሪካ የማዕድን ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ክልል በወርቅ ፍለጋና ምርት ሊሰማራ ነው፡፡
የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም በወርቅ ምርት አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውሞንት በትግራይ ክልል ሁለት ቦታዎች በፅንስ ወርቅ ፍለጋና ልማት ለመሰማራት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡
ኒውሞንት በከፍተኛ የወርቅ ምርት ላይ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቱን የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ ኩባንያው ሥራውን በሽርክና እንደሚያካሂድ ገልጸዋል፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ግዙፍ የማዕድን ኩባንያዎችን ለመሳብ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ በአሁኑ ወቅት አራት ኩባንያዎች የፅንስ ወርቅ ፍለጋ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በወርቅ ፍለጋ ሥራቸው ጥሩ ውጤት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ የአዋጭነት ጥናት አካሂደው የምርት ፈቃድ ለመውሰድ በድርድር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ የወርቅ ምርት የተሰማራው ኩባንያ ሚድሮክ ጎልድ ብቻ ነው፡፡
ሚድሮክ ጎልድ በለገደምቢ በሚገኘው ወርቅ ማውጫ በዓመት አራት ቶን ወርቅ ያመርታል፡፡ ባህላዊ የወርቅ አምራቾች በዓመት ስምንት ቶን ያህል ወርቅ ያመርታሉ፡፡ አገሪቱ በዓመት ከማዕድን ኤክስፖርት 600 ሚሊዮን ዶላር ያህል የምታገኝ ሲሆን፣ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ወርቅ ነው፡፡ ባህላዊ አምራቾች ከአጠቃላይ የማዕድን ምርት ሁለት-ሦስተኛውን ያቀርባሉ፡፡
የኒውሞንትን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች እንደ ትልቅ ድል ቆጥረውታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1921 አሜሪካ ኔቫዳ ውስጥ የተቋቋመው ኒውሞንት በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች፣ በኢንዶኔዥያ፣ በአውስትራሊያ፣ በኒውዚላንድ፣ በፔሩና በጋና የወርቅ ማውጫዎች ሲኖሩት፣ ዓመታዊ ገቢው ከ9.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡
ኒውሞንት ከኤፈርት እህት ኩባንያዎች አንዱ ከሆነው ኢዛና ማይኒንግ ኩባንያ ጋር በሽርክና እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሰሜን ትግራይ በተለያዩ ቦታዎች የወርቅ ክምችት የሚገኝ ሲሆን፣ ሽሬ አካባቢ በባህላዊ መንገድ በስፋት ይመረታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢዛና ማይኒንግ ወደ ከፍተኛ የወርቅ ምርት ለመግባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ኢዛና ዕውቅና ያለው የጂኦሎጂካል ላቦራቶሪ ባለቤት ነው፡፡ ኩባንያው የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በሽርክና ለመሥራት መምረጡን አንድ የኩባንያው ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡