Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ድርቁ እየከፋ ነው!

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የፈጠረው ድርቅ እየከፋ ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አይታው የማታውቀው አስከፊ ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ዜጎችን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ ሲያደርጋቸው፣  በመጪዎቹ ወራት ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡ በእርግጥ አሁንም ተጨማሪ 7.8 ሚሊዮን ዜጎች የሴፍቲኔት፣ የንፁህ ውኃ፣ የጤናና የንፅህና፣ እንዲሁም የአልሚ ምግብ ዕርዳታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 18 ሚሊዮን ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የድርቅ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች በምግብና በውኃ እጥረት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ኤልኒኖ ከፍተኛ ጉዳት ካመጣባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡ በዚህም ከፍተኛ ሙቀትና ደረቅ ንፋስ ተባብረው ድርቁን የከፋ አድርገውታል፡፡ በተለይ በመካከለኛው፣ በምሥራቅና በሰሜናዊ የአገሪቱ አካባቢዎች የበልግና የመኸር አዝርዕት ከመውደማቸውም በላይ፣ ለበርካታ እንስሳት ዕልቂት ምክንያት ሆኗል፡፡ በድርቁ የተጎዱ አካባቢዎች ነዋሪዎችም ለፅኑ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ በአየር ንብረቱ ምክንያት ዝናብ በመጥፋቱ ውኃና  ግጦሽ ባለመኖራቸው በሕይወት ያሉ እንስሳትም እየተጎዱ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚፈጠር ሥጋት አለ፡፡

መንግሥትና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጀቶች በቅርቡ በጋራ ባወጡት ሰነድ የአሁኑ ድርቅ እጅግ የከፋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት ተጨባጭ ሁኔታው የሚያሳየው በሁለቱ የአዝመራ ወቅቶች ዝናብ በመጥፋቱ ሳቢያ የአገሪቱ 85 በመቶ ሕዝብ የሚሳተፍበት 80 በመቶ ያህል የግብርና ምርት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የ1.4 ቢሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ይህ የዕርዳታ ጥሪ ከቀረበ በኋላ የሚታየው ምላሽ በጣም ቀዝቃዛ ነው፡፡ በተከሰተው ድርቅ የተፈጠረው ችግር ትኩረት ያጣው፣ ዓለም በከፍተኛ ደረጃ ፊቱን ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ወደ ተፈጠረባቸው አገሮች በማዞሩ ነው፡፡ በኢራቅ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶሪያና በየመን የዓለም የምግብ ፕሮግራም በመወጠሩ ጫናው በከፍተኛ ደረጃ መንግሥት ላይ ሲወድቅ፣ አገር ውስጥ ያሉ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጀቶችም በርብርብ ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት በድርቁ ምክንያት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከመጠባበቂያ ክምችት በመበደርና ለአንድ ሚሊዮን ቶን ስንዴ ግዥ ጨረታ በማውጣት፣ ይኼንን የፈተና ጊዜ ለመወጣት በጥረት ላይ ይገኛል፡፡ እንደ አየር ንብረቱ  አያያዝ ከሆነ ደግሞ ከመጪው መጋቢት እስከ ግንቦት ድረስ የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ ላይኖር ስለሚችል፣ ወይም ደግሞ ከመደበኛው ሊያንስ ስለሚችል መጪው ጊዜ ፈታኝ ነው፡፡ የመኸሩም ጉዳይ ከወዲሁ ያሳስባል፡፡ በተለይ በረድኤት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጀቶች እንደሚሉት፣ የአገሪቱ የመጠባቂያ ምግብ ክምችት እየተሸረሸረ ከሄደ ሰብዓዊ ቀውሱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት የስንዴ ግዥው ከእጥፍ በላይ መጨመር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ  ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሹ ዝቅተኛ በመሆኑ የከፋ ጊዜ ላይ ነን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከምግብ ባልተናነሰ ውኃ በጣም ቢያስፈልግም፣ የውኃ ምንጮችና ጉድጓዶች ጭምር በመድረቃቸው ችግሩ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በዝናብ መጥፋት ምክንያት ወንዞችና ኩሬዎችም ደርቀዋል፡፡ ለእንስሳት የሚሆን ግጦሽ የለም፡፡ የእንስሳት መኖ ለማቅረብ ደግሞ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች የተወሰኑ እንስሳትን ሸጠው ሌሎቹን ለማትረፍ የሚያደርጉት ጥረት በዋጋ መውደቅ ምክንያት ችግር እየተፈጠረበት ነው፡፡ ቢያንስ በሚያገኙት ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው እህል ለመሸመት፣ ለእስሳት መኖ ለማቅረብና ለመሳሰሉት የሚያደርጉት ጥረት እየተደናቀፈ ነው፡፡ ይህ ችግር ከቀጠለ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ዕልቂት ሊያጋጥም ይችላል፡፡

የአገሪቱን ድርቅ በተመለከተ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የዘንድሮ ድርቅ የምርት መጠንን በጣም ከማሳነሱምና ተጎጂዎችን ለችግር ከመዳረጉ በተጨማሪ፣ በቀንድ ከብቶች ገበያና በእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተሰቦች የመግዛት አቅማቸው ተዳክሟል፡፡ በተለይ የአፋር፣ የደቡብ ክልል ስልጤ ዞን፣ የምሥራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ቆላማ ሥፍራዎች እስከ መጪው መጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ድረስ መሠረታዊ የምግብ ፍላጎታቸውን ላያሟሉ ይችላሉ፡፡ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የሶማሌና የትግራይ ክልሎች ሰፊ አካባቢዎች እስከ መጋቢት ድረስ የችግሩ ሰለባ ሆነው እንደሚቀጥሉ ተተንብይዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የችግሩን ፅኑ መሆን ነው፡፡ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚታወቁና ፅኑ የምግብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች ለወረርሽኝና ለተላላፊ በሽታዎች እንዳይጋለጡም ያስፈራል፡፡ ምንም እንኳ እንደ 1977 ዓ.ም. ረሃብ ጊዜ ባይሆንም አስፈሪ ምልክቶች ግን አሉ፡፡

ይኼ አስከፊ ድርቅ ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በሰው ሕይወት ላይ ጭምር አደጋ እንዲያዣብብ የሚያደርግ ሲሆን፣ በከተማ በሚኖሩ ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ግሽበትም ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ያለው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ የከተማ ነዋሪዎች የሚፈልጓቸውን በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት አዳጋች ይሆንባቸዋል፡፡ ለወትሮም በዋጋ ግሽበት የሚመቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይም ያሳስባል፡፡ በድርቁ ምክንያት የእንስሳት ተዋጽኦ አካል የሆነው ወተትና የአትክልትና የፍራፍሬ እጥረት በከተማ ሌላው አሳሳቢ ችግር ነው፡፡ የሸቀጦች እጥረት ሲፈጠር ደግሞ ከፍተኛ ለሆነ የዋጋ ግሽበት መዳረግ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ የድርቁ አስከፊነት ከዚህም በላይ በመሄድ በአገሪቱ በጤና፣ በትምህርት፣ ፍፁማዊ ድህነትን በመቀነስና በመሳሰሉት መስኮች እየታዩ የነበሩ ጅምር ለውጦች ላይ ረዘም ላሉ ጊዜያት የሚቆይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ የአሁኑ አስፈሪ ሁኔታ ካልተቀየረ ድርቁ እየከፋ መሄዱና ችግሮችን ማባባሱ አይቀሬ ነው፡፡

የድርቁ አስከፊነት በዚህ መጠን ሲገለጽ ምን መደረግ አለበት መባል ይኖርበታል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ቀዝቃዛ ከሆነ መንግሥት ከዚህ በፊት በፓርላማ በማፀደቅ ከያዘው 14 ቢሊዮን ብር በጀት በተጨማሪ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት በመጠባበቂያነት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት ራሱ መንግሥት ቃል እንደገባው በተቻለ መጠን አንገብጋቢ ያልሆኑ የልማት ፕሮግራሞችን በማጠፍ፣ የድርቅ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ሕይወት ማትረፊያ ማዋል አለበት፡፡ በዚህ ድርቅ ምክንያት አንድም ሰው መሞት ስለሌለበት መንግሥት ያሉትን መዋቅሮቹን በመጠቀምና መላውን የአገሪቱን ሕዝብ በማስተባበር ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ወገቡን ጠበቅ ማድረግ አለበት፡፡ ይህ የከፋ ድርቅ ሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት ርብርቡ በተጠና መንገድ በፈጣን ምላሽ ይታጀብ፡፡ ሌሎች ወገኖችም አገሪቱንም ሆነ በድርቁ ምክንያት አደጋ የደረሰባቸውን ወገኖች የማይጠቅሙ አጀንዳዎችን ማራገብ በመተው ይህንን አደገኛ ጊዜ በብቃት ለመቋቋም ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ይሰው፡፡ ወቅቱ አሳሳቢ በመሆኑ እንደ አገር አንድ ላይ በመቆም ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡ ድርቁ ከፍቷል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...