የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለመገንባት አውጥቶት የነበረው የውስን ጨረታ ሒደት መሰረዝን ተከትሎ የደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር፣ የኮርፖሬሽኑን ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታውን አሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡበት ጠይቋል፡፡
ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችን በጅምላ በመፈረጅ ጨረታውን መሰረዙ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሷል፡፡ ከድሬዳዋ፣ ከሐዋሳና ከሌሎቹም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር የግንባታ ሒደትን መሠረት በማድረግ መንግሥት እየተከተለ ያለው አሠራር እንደሚያሳስበው፣ ማኅበሩ አቤቱታውን ባቀረበበት ደብዳቤው ገልጿል፡፡
ምንም እንኳ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው አቤቱታ በተናጠል መነሻውን ለድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የወጣውን ጨረታ መሰረዝ ያድርግ እንጂ፣ የማኅበሩ ሥጋት ግን ከዚያም ያለፈ እንደሆነ በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡ በኢንዱስትሪ ግንባታ ረገድ መንግሥት በአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ላይ የተዛባ አመለካከት መያዙን ማኅበሩ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡ የጨረታው መሰረዝም የዚህ የተዛባ ግንዛቤ ቀጥተኛ ውጤት ነው ሲል አክሏል፡፡
የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ ከውጭ ሸሪኩ ጋር እንዲሁም ሌላ የውጭ ኩባንያ ለፋይናንስ ምዘና ደረጃ በመድረሳቸው መመረጣቸውን በመግለጽ፣ ከዚህ ቀደም የወጣው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጨረታ በቅርቡ መሰረዙ ይታወሳል፡፡ ከተወዳደሩት መካከል የነበረው ሌላኛው አገር በቀል ተቋራጭ የቴክኒክ ደረጃዎችን ማለፍ ባለመቻሉ መውደቁ ተነግሯል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ራማ ኮንስትራክሽን የተባለው አገር በቀል ተቋራጭ የቴክኒክ ደረጃውን ማለፍ ያልቻለ ኩባንያ ነው፡፡
ይህም ሆኖ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሲሲኢሲሲ) የተባሉት ኩባንያዎች የሚኤሶ-ጂቡቲ አገር አቋራጭ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታን በቅርቡ ያጠናቀቁ ሲሆኑ፣ ለፋይናንስ አቅም ምዘና ደረጃ ያለፉት ናቸው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ በድንገት ጨረታው መሰረዙን አስታውቋል፡፡ ለጨረታው መሰረዝ ምክንያቱ ደግሞ አሻሚ ይዘቶች በቀደመው የጨረታ ሰነድ ውስጥ መኖራቸው ስለተረጋገጠ ነው ተብሏል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሌላ ጨረታ በድጋሚ እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡
የጨረታው መሰረዝ ግን በአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ዘንድ ቅሬታ ሲፈጥር፣ ተቋራጮቹ ስረዛው አገር በቀል ኩባንያዎችን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለማስወጣት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው በማለት ተቃውመውታል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ግን፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግንባታ ጨረታ የተሰረዘው ግልጽነት በተመላበት መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዶ/ር አርከበ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለመገንባት ወጥቶ የነበረው ዋና ሰነድ ላይ ከፍተኛ አጠራጣሪና ለትርጉም የተጋለጡ ሐረጎች ስለነበሩበት ጨረታው እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡
‹‹የፓርክ ልማቱ አገሪቱ ከውጭ የቦንድ ሽያጭ ባገኘችው የፋይናንስ ምንጭ የሚካሄድ በመሆኑና አገሪቱም ዕዳዋን በተቀመጠው የመክፈያ ጊዜ ውስጥ አክብራ መክፈል ስለሚገባት፣ ለስህተት ምንም ዓይነት ቦታ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፓርኮቹን በወቅቱ ገንብተን ለኩባንያዎች ካላደረስንላቸው ዕዳችንን ለመክፈል የሚያስችለን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አንችልም፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑም ሆነ መንግሥት የፓርክ ልማቱን በጥንቃቄ እንደሚያካሂዱ የገለጹት ዶ/ር አርከበ፣ በዚህ የጥንቃቄ ሒደት ወቅት በጨረታ ሰነዱ ላይ የነበረው አወዛጋቢ ይዘት ሊታወቅ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር አርከበ በምሳሌነት ከጠቀሱት ውስጥ በዋናው የጨረታ ሰነድ ውስጥ የእሽሙር (ጆይንት ቬንቸር) ኩባንያዎች ተሳትፎን መፍቀዱ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ይሁንና በጋራ የሚያለማው የውጭ ኩባንያ አገር ውስጥ ያለ ወይም በውጭ የሚገኝ ስለመሆኑ ግልጽ አላደረገም፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአስቸኳይ ተገንብተው የውጭ ምንዛሪና የሥራ ዕድል ማስገኘት አለባቸው ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ የፓርኮቹ ግንባታ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡ በእሽሙር ለመገንባት የሚሳተፉ ኩባንያዎች ከሆኑና የውጭው ኩባንያ ከአገር ውጭ የሚሠራ ከሆነም፣ የግንባታ መሣሪያዎቹን እስኪያስገባ ከሦስት እስከ አራት ወራት የሚፈጅበት በመሆኑ፣ ይህንን ለማስተናገድ እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በጨረታ ሰነዱ ለፕሮጀክቱ የሚጠየቀው ዓመታዊ ሽያጭ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑም ሌላው አሻሚ ነጥብ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በዋናው የጨረታ ሰነድ ለግንባታ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ዓመታዊ ሽያጭ የፕሮጀክቱን 55 በመቶ መሸፈን አለባቸው፡፡ ይህ ለእሽሙር ኩባንያዎችም በግልጽ መቀመጥ አለበት ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ‹‹የጨረታ ሰነዱ የማያሻማና ፍጹም ግልጽ እንዲሆን እየሞከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን የተቀመጡት መሥፈርቶች የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለማሟላት የሚቸገሩባቸው መሆናቸውን ቢያምኑም፣ መሥፈርቶቹ በግድ መሟላት ያለባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ረገድ የተረጋገጠ ብቃት ያላቸውና ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ያላቸውን ኩባንያዎችንና ወሳኝ ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት፣ የራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ያላቸውን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ክፍያ ተከፍሏቸው ሥራ የሚጀምሩትን አንጠብቅም፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ቢባልም የደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበሩ በበኩሉ መሥፈርቶቹ ሆን ተብለው ለውጭ ኩባንያዎች የተዘጋጁ በመሆናቸውና የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን የሚያገሉ በመሆናቸው የመሥፈርቱን አግባብነት በእጅጉ ኮንኗል፡፡ ዶ/ር አርከበ ግን እንዲህ ያለውን አቤቱታ ውድቅ የሚያደርጉት፣ ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከነበሩበትና ከዚያም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ የአገር ውስጥ አቅም እንዲገነባ ሲደግፉና ሲያግዙ መቆየታቸውን በመግለጽ ነው፡፡ ‹‹የደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች መንግሥት በዘረጋቸው ፕሮግራሞች አማካይነት እንደመጡ መዘንጋት የለበትም፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ሲካሄዱ የነበሩት በጥራትና በጊዜ የማስረከብ ችግሮች ተሸፍነው እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹አሁን ይህንን ማድረግ አንችልም፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ይህ አይቻልም፡፡ በተለይ በአንደኛው የግንባታ ምዕራፍ ወቅት ይህ የሚቻል አይደለም፤›› በማለት አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር አርከበ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለመገንባት ስድስት ዓመታት ፈጅቶም አሁንም ድረስ እንዳልተጠናቀቀ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ፓርክ 23 ኩባንያዎችን ብቻ በማቀፍ ከአምስት ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር ያልቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ መንገድ የአገሪቱን አምራች ኢንዱስትሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ማድረግ እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡