Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሙዚቃና ጋምቤላ

ሙዚቃና ጋምቤላ

ቀን:

በያዝነው የጥር ወር ከጥቂት አገሮች ውጪ መላው ዓለም አዲስ ዓመትን ተቀብሏል፡፡ በጥር ወር አዲስ ዓመትን መጀመር እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ጥቂት አገሮች ውጪ በየትኛውም ዓለም የተለመደ መሆኑ ቢታወቅም በኢትዮጵያ ውስጥ በጥር ወር አዲስ ዓመት የሚጀመር (የሚከበር) መሆኑ ግን እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ ጊዜ አመጣሹ ግሎባላይዜሽን (ሉልነት) በሕዝቦች ባህልና አኗኗር ላይ ግልፅ የሆነ ተፅዕኖ እያሳደረ ባለበት በዚህ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ግለሰቦች የፈረንጆች አዲስ ዓመትን ማክበር መጀመራቸው ሰንበትበት ያለ እውነታ ነው፡፡

በተቃራኒው በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ባለው የባህል ልዩነት ምክንያት አብዛኞቹ ብሔረሰቦች ከብሔራዊው የአዲስ ዓመት መለወጫ ቀን (የቀን መቁጠሪያ) በተጓዳኝ የራሳቸው የዘመን መለወጫ ያላቸው ቢሆንም ከፈረንጆቹ የዘመን መለወጫ ወር ጥር ጋር ግን የተያያዘ አለመሆኑ ይታወቅ ነበር፡፡ በጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል በሚገኙ አምስቱም ነባር ብሔረሰቦች በየራሳቸው የሚያከብሯቸው ክብረ በዓላት እንዳሏቸው ሊታወቅ፣ በኑዌር ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ታኅሣሥ ወይም ጥር ወር ላይ በቆሎ ሲደርስ በዓመታዊ ክብረ በዓልነት መከናወኑ አዲስ ነገር ይመስላል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት በባሮ ወንዝ ዳር በመሰባሰብ በሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል የብሔረሰቡ አባላት ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ቢኖራቸውም እንደ ሙዚቃ በዓሉን የሚያደምቅ ነገር የለም፡፡ በልዩ ምት የሚታጀበው ጭፈራ የጋምቤላ የሁሉም ብሔረሰቦች መገለጫ ቢሆንም በኑዌሮች ዘንድ በዘመን መለወጫ በዓል ቀን የሚጨፈረው ግን ለየት ያለ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በተመለከተ የጅማት፣ የትንፋሽና የምት እንዲሁም በንዝረት ድምጽ የሚሰጡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲገኙ በጅማት የሚሠራው ቡሉ፣ በንዝረት የሚሠራው ቶምና በእግር ላይ የሚታሠረው ጋሪ የክልሉ ልዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች መገለጫ ናቸው፡፡

እንደ ‹‹ጋምቤላ›› ድርሳን አገላለጽ፣ በኑዌር ብሔረሰብ ዘፈኖች ልዩ ቦታ አላቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለምሳሌ ኑዌሮች ከብቶቻቸውን በሚያሰማሩበት ወቅት ‹‹ቱዋሬ›› የሚባል ዜማ ለከብቶቻቸው ያዜማሉ፤ በሚያዜሙበት ጊዜ ልዩ የሆኑ አካላዊ እንቅስቃሴዎችና ጭፈራዎች አሏቸው፡፡ በደስታ ጊዜ፣ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሥርዓቶችና በሥራ ጊዜ ሲያዜሙ ‹‹ጅችዋንግ›› (ጥሩንባ)፣ ‹‹ዲት›› (ፊሽካ)፣ (ክራር)፣ ‹‹ቱም››፣ ‹‹ቡል›› (ከበሮ) እና ‹‹ቡድ›› (ዋሽንት) ይጠቀማሉ፡፡ መሣሪያዎቹ ከቆዳ፣ ከቀርከሃና ከጥላ ሽቦ፣ ከገመድ ይሠራሉ፡፡ ‹‹ቡል›› ከበሮ ከከብት ቆዳና ከቆርቆሮ ሁት ዓይነት ድምጽ እንዲያወጣ ረጅምና አጭር ሆኖ የሚሠራ ሲሆን እንጨት ላይ ተሰቅሎ በአጭር እንጨት ሁለት ሰዎች ይመቱታል፡፡

የአኙዋሃ ብሔረሰብ በግብርና ሥራ ወቅት እየተቀባበሉ የሚያዜሙት ‹‹ዱት›› የሚባል ልዩ ዜማ አላቸው፡፡ ዜማው የሚደረሰው በቃል ሲሆን ልዩ መነቃቃትና የሥራ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሠርግና በደስታ ጊዜ እንዲሁም በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች ላይ የሚዜሙ ዜማዎች አሏቸው፡፡ የአኙዋሃ ብሔረሰብ የራሱ የሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎች ዝነኛው ቶም፣ ከበሮ (ቡል) ዋሽንት ‹‹ገብሎ››ና ቃጭል ‹‹ባሬ›› ሲኖሯቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የሙዚቃ መሣሪያዎች በወንዶች የሚመቱ ሲሆን ንጉሥ ወይም መሪ ሲሞት ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡

በማጃንግ ብሔረሰብ ‹‹ገረኔ›› ወንዶች ለሐዘን ሄደው ሲመለሱ የሚዘፈን፣ ‹‹ጎፌ›› በቆሎ ሲደርስ የሚዘፈን፣ ‹‹ማበሬ›› ቁጭ ተብሎ የሚዘፈን ትውፊቶች ሲኖሩ ማጃንጎች በሙዚቃ ባህላቸውና በሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው የታወቁ ናቸው፡፡ በተይም ጆኬ የሚባል ቅባት ተቀብተው የሚጫወቱትን ጭፈራና በንብ ሥራ ጊዜ፣ በሠርግና በአዝመራ ወቅት የሚያዜሟቸው ማራኪና ጥልቅ ባህላዊ ትርጉም ያላቸው ዜማዎች አሏቸው፡፡ በማጃንግ ብሔረሰብ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲኖሩ ከእነዚህም ‹‹ቶም›› የሚባለው የሙዚቃ መሣሪያ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ቸርግን››፣ ‹‹ፑዋክ›› (የትንፋሽ መሣሪያ)፣ ‹‹ሸትየ ታርቢይ››፣ ቃጭል ‹‹ሸኩሬይ›› እንዲሁም በጭፈራ ወቅት በሴቶችና በወንዶች እግር ላይ በመታሰር ሲንቀሳቀሱ ድምፅ የሚሰጡ መሣሪያዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የኦፖ ብሔረሰብ አባላት ሰፊ የሙዚቃ ትውፊት ባለቤቶች ናቸው፡፡ የኦፖ ወጣቶች ‹‹ካጋ›› የሚባሉ የፍቅር መግለጫ ዘፈኖች አሏቸው፡፡ ወጣቱ የውስጡን የፍቅር ስሜት በ‹‹ቱቱሉ›› (በክራር) አንድ ቦታ በመቀመጥ ስላፈቀራት ልጅ ይዘፍናል፡፡ ሴቷም እንዲሁ ስለወደደችው ልጅ ሥራ በምትሠራበት ጊዜ ‹‹አቢንዲሊ›› በሚባል መሰንቆ ትዘፍናለች፡፡ የፍቅር ዜማ ‹‹ቡሊፖ››፣ ትላልቅ ሰዎችን የሚያሳትፍ ‹‹ቆይቶር››፣ ጀግንነትን ለመግለጽ የሚደረሱ አጫጭርና ፈጣን ዜማዎች ‹‹ዋቃላ››፣ ለበዓላት ‹‹ቆይቶርናቦት›› ይዘፈናሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ‹‹ቡሊፖ›› የተሰኘው ወጣቶች በከበሮ ታጅበው በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚጫወቱት ሙዚቃ የሚዘወተር ሲሆን፣ በአደን ጊዜ ‹‹ቢስ›› የሚባል ሴቶች የማይሳተፉበት የአዳኞች ሙዚቃም ቀልብን የሚስብ ቃና አለው፡፡ የኦፖ ብሔረሰብ የሙዚቃ መሣሪያዎች ታዋቂውን ክራር – ‹‹ቱምን›› ጨምሮ ከቀርቀሃ የሚሠራ የትንፋሽ መሣሪያ – ‹‹ቦት››፣ ከቀንድ የሚሠራ የትንፋሽ መሣሪያ – ‹‹ቱቱሉ››፣ ወፈር ካለ ሣር የሚሠራ የትንፋሽ መሣሪያ – ‹‹ጡጡለት››፣ ከእንጨት ከቆዳ የሚሠራ ከበሮ – ‹‹ቡል››፣ ከእንጨት የሚሠራ – ‹‹ቻቦት››፣ ከቀንድ የሚሠራ የትንፋሽ መሣሪያ – ‹‹ፌቱ›› ናቸው፡፡

የኮሞ ብሔረሰብ ወንዶች ለብቻ ሴቶች ለብቻ ሆነው የሚደንሱት ተመሳሳይ ስልት ያለው ዳንስ አላቸው፡፡ በሙዚቃቸው ውስጥም መከባበርና ተመስጦ ይታያል፡፡ አርሶ አደሮቹ የኮሞ ብሔረሰብ አባላት ዝናብ ከጠፋ ለአምላካቸው በዜማ ምልጃ ያቀርባሉ፡፡ ይኸውም ሥርዓት ‹‹ውፑ›› ሲባል በዚህ ወቅት በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች የሚሳተፉ ሲሆን ‹‹አቲሽ›› የተባለው የትንፋሽ መሣሪያ መጫወት በሚችሉ ሰዎች ይሰማል፡፡ የኮሞ ብሔረሰብ የሙዚቃ መሣሪያዎች ዋሽንት ‹‹ሸን››፣ ከበሮ ‹‹ቡል››፣ ጥሩንባ ‹‹ልክልክ››፣ ከፍየል ቀንድ የሚዘጋጅ ጥሩንባ ‹‹ኩምበሌ›› ከሣር የሚዘጋጅ የትንፋሽ መሣሪያ ‹‹ጋንቻ›› ናቸው፡፡ ስማቸው ‹‹ሽዋጊ›› ‹‹በሸንሸን›› የሚባሉ የትንፋሽ መሣሪያዎች ልዩ የአጠቃቀም ሥርዓት አላቸው፤ እነዚህ ከአሥር ሁለት ቀርከሃ የተሠሩ መጠናቸው የሚለያይ የትንፋሽ መሣሪያዎች በአሥራ ሁለት የሠለጠኑ የሙዚቃ ተጫዋቾች ሲሰሙ አንዳንዴ ልዩ ተመስጦ ያለው የቅኝት መሪ በመሀላቸው ሊኖር ይችላል፡፡ የሚመራቸውም ሁለት አጫጭርና ወፈር ያሉ እንጨቶችን በማጋጨት ሲሆን የቅኝት መሪው ለሚያሰማው የዜማ ቅንብር የማይመጥን ሰው ካለ ወዲያው በመለየት ይቀይረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...