Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሙዚቃውና በፊልሙ ያለን አቅም በትምህርት ካልተገነባ ጊዜያዊ ይሆናል››

የሰላም ድርጅት መሥራችና ዋና ኃላፊ፣ አቶ ተሾመ ወንድሙ

ሰላም ድርጅት የተቋቋመው ስዊድን፣ ስቶኰልም ውስጥ ሲሆን፣ ሰላም ኢትዮጵያ የተሰኘ ቅርንጫፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከፈተ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የተራድኦ ድርጅቱ በዋነኛነት በሙዚቃና በባህል ዘርፍ ይንቀሳቀሳል፡፡ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከወጣት ሙዚቀኞች፣ ዓይነ ስውራንና የሙዚቃ ማኅበሮች ጋር በጥምረት የሚሠራቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ በየዓመቱ የሚዘጋጀው ሰላም ፌስቲቫልም ተጠቃሽ ነው፡፡ ፌስቲቫሉ ታኅሳስ 30 እና ጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአምስተኛ ጊዜ በግዮን ሆቴል ተካሒዷል፡፡ ስለፌስቲቫሉ እንዲሁም አጠቃላይ የድርጅቱ ክንውኖች የሰላም ድርጅት መሥራችና ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ወንድሙን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሔደው ሰላም ፌስቲቫል ከቀደሙት ጋር ሲነጻጸር ጠንካራና ደካማ ጐኖቹ ምን ይመስላሉ?

አቶ ተሾመ፡- ፌስቲቫሉ በየዓመቱ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ እንዲጠነክር፣ ሰው እንዲለምደው፣ ሕዝቡ ሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን ሌላም ትምህርታዊ ነገሮችን እንዲቀስምና እንደ መገናኛም እንዲሆን ነው፡፡ ብዙ ሰው የሚያስበው የሁለቱን ቀን ፌስቲቫል ታኅሳስ 30 እና ጥር 1 2008 ዓ.ም. የተካሄደውን ነው፡፡ እኛ ግን የጀመርነው ከሳምንት በፊት ሰኞ ዕለት በሳውንድ ኢንጂነሪንግና የተለያዩ ወርክሾፖች ነው፡፡ የዘንድሮው አጋራችን ብሔራዊ ቴአትር ነው፡፡ ከ20 በላይ ባለሙያዎች የተካፈሉበት ፕሮግራም ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው ሥራቸውን በፕሮፌሽናል መንገድ መሥራት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ ባለፈው ዓርብ የነበረን ኮንፈረንስ፣ ለወደፊት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወይም ባህል ኢንዱስትሪ እንዲሆን ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በግዮን ሆቴል የዳሰስንበት ነበር፡፡ ሌላው ስለሚዲያ ሚና ነው፡፡ ሚዲያ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች በተለያዩ ነገሮች ላይ ትችት ሲያቀርቡ ምንን መሠረት አድርገው ነው የሚለው ብዙ ያነጋገረና ያወያየ ጉዳይ ነበር፡፡ ትምህርት፣ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ ተነስቷል፡፡ ሌላው የሁለቱ ቀን ፌስቲቫል ነው፡፡ የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው ጥራቱ እንዲያድግ፣ ከአጋሮቻችን ጋር ከድምፅ ዕቃዎች ጀምሮ በአመራርም በደንብ እንዲደራጅ ብዙ ተዘጋጅተን መምጣታችን ነው፡፡ አንዳንድ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ቀድመን ማስታወቂያ ለመሥራት መሟላት ያለባቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሩ፡፡ ፍቃዶችንና ዕቃዎችን በሚመለከት ትናንሽ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ባለችን ጊዜ አስተዋውቀን ፌስቲቫሉን ለመሥራት ሞክረናል፡፡ ዘንድሮ ሰላም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለን ሁለት ድርጅት ጋር አቀነባብረን ነው የሠራነው፡፡ ይህን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በየዓመቱ የአሠራር ልምድ እንዲያገኙና ለወደፊት ለመዝናኛና ለፌስቲቫልም ባህል ዝግጁ እንዲሆኑ በጣም እየሠራን ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው ቅዳሜም እሑድም ዝናብ ነበር፡፡ የተፈጥሮ ጉዳይ ስለሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ በትንሹ ግን ሰው እንዳይመጣና ዝናቡን ፈርቶ ቤት እንዲቀር አድርጓል፡፡ በተለይ የእሑዱ ዝግጅት መጨረሻው አካባቢ በጣም ኃይለኛ ዝናብ ዘንቧል፡፡ አንዳንድ ዕቃዎችን አበላሽቶብናል፡፡ ወደ መጨረሻ ያለውን ሥራም በጊዜ ነው የጨረስነው፡፡ ከዚያ ውጪ የፌስቲቫል ስሜቱ እየመጣ ነው፡፡ ሰው ቀን መጥቶ ከልጆቹ ጋር ተጫውቶ፣ ቀን ያሉ ዝግጅቶቻችንን ዓይቶ፣ ዕቃዎች ከባዛር ገዝቶ፣ ደስ እያለው ውሏል፡፡ ማታ ከኢትዮጵያና ከሌላ ሀገር የመጡ ታላላቅ አርቲስቶችን የሚያይበት መንገድ ፈጥረናል፡፡ ዘንድሮ ጋሽ መሐሙድ አህመድና ሮሀ ባንድ የሚገርም ሥራ አቅርበዋል፡፡ ሰውን ሁሉ በጣም ያስደነቀ ነበር፡፡ የጋሽ መሐሙድ ትልቅ አርቲስትነት እንደገና የታየበት ምሽት ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ እንግዶቻችን በሙሉ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሌላ ሀገር አላየንም ነው የሚሉት፡፡ ሰው ጋሽ መሐሙድ ጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ ዘፈኑን ሁሉ አውቆ አብሮ መዝፈኑ አስገርሟል፡፡ በተለይ የውጪውን የሚያውቁት እንግዶቻችን በጣም ነው የገረማቸው፡፡ አሁንም እኛ ሀገር ፌስቲቫል ማዘጋጀት አዲስ ባህል ነው፡፡ እኛ የምናስበው ዓይነት ፌስቲሻል ማዘጋጀትና ሰውን ማላመዱም ትንሽ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ እኛ ደግሞ የምንመጣው በየዓመቱ ነው፡፡ ያን ለመለወጥ አዳዲስ ሀሳቦች አሉን፡፡ ዓመት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የማድረግ ሀሳብ አለ፡፡ ካለፈው ዓመት ቦታ ለውጠን ከትሮፒካል ጋርደን ወደ ግዮን መጥተናል፡፡ ግዮን ትልቅና የሚስማማን ቦታ ነው፡፡ ከግዮን ጋር በመነጋገር ብዙ ዕቅድ እያወጣን ነው፡፡ ሥራችን ለኢትዮጵያ ባህል ዘርፍና ለከተማው ጠቀሜታ እንዳለው በመነጋገር አንዳንድ ሥራዎች አስበናል፡፡ በየጊዜው በሚዲያም በሌላም መንገድ የማቅረብ ሀሳብ አለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የቀደሙትን ፌስቲቫሎች እንደምሳሌ በመጥቀስ የታዳሚዎች ቁጥር እንደቀነሰ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ተሾመ፡- ፌስቲቫሉን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ፈቃዶች መዘግየት ለማስተዋወቂያ ሥራ ጊዜ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ሕጋዊ ፍቃዶች እስኪኖሩን ድረስ ማስተዋወቅ አለመቻላችን ትልቁ ችግር ነበር፡፡ በእኛ አመለካከት ዘንድሮ ያቀረብናቸው አርቲስቶቻችን ካለፈው ይሻላሉ፡፡ ሁሉም የየራሱ አመለካከት አለው፡፡ የዓለም አቀፍ የሀገራችንንም አርቲስቶች ለማመጣጠን ተሞክሯል፡፡ ሰው ፌስቲቫሉን ብሎ እንዲመጣና የተለያየ ነገር እንዲያገኝ እንጂ አንድ አርቲስት ብቻ ብሎ እንዳይመጣ ለማድረግ ጥረናል፡፡ ይሔ ማንኛውም ዓለም ላይ የሚታይና የሚደረግ ነው፡፡ ፌስቲቫሉ የራሱ ቀለም አለው፡፡ ሙዚቃው ብቻ ሳይሆን ካለው ድባብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የዘንድሮው ሰፋ ያለና ትልቅ ነው ብለን ነው የምንገምተው፡፡ ትልቅ አርቲስት የነበረው ከአሜሪካ ያሲን ቤ (በቀድሞ ስሙ ሞስ ዴፍ) የጉዞ ሰነድ ባለማሟላቱ በሚገባበት ቀን ከአውሮፕላን ማረፊያ ተመልሷል፡፡ ኮንሠርቱን ሊካፈልም አልቻለም፡፡ የተወሰኑ አርቲስቶች ደግሞ በዝናቡ ምክንያት ሥራቸውን አላሳዩም፡፡ በእኛ ሀሳብ ከዚያ ውጪ የመጡት አርቲስቶች ድንቅ ናቸው፡፡ ጋሽ መሐሙድ አህመድ፣ ሲድኒ ሰለሞን፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ፀደንያ ገብረማርቆስና ዳዊት ጽጌ የታወቁ አርቲስቶች ናቸው፡፡ ከውጭም ጌይ ፋይ በፈረንሳይና በሩዋንዳ የታወቀ አርቲስት ሲሆን፣ የሚያስደንቅ ነገር አሳይቷል፡፡ ከዩጋንዳም ምርጥ የተባለውን አርቲስት መርጠናል፡፡ እኛ የምናይበት የራሳችን መስፈርት አለ፡፡ አንዳንድ ሰው የለመደውና የሚወደው አለ፡፡ ይህንን በየዓመቱ ለማመጣጠን እንፈልጋለን፡፡ ሰው ማየት የሚፈልገው አርቲስት የተለያየ ነው፡፡ እንደ ፌስቲቫል አዘጋጅነታችን ማመጣጠን አለብን፡፡ እውነቱን ለመናገር በአንድ አርቲስት ብንሠራ ይቀለናል፡፡ አሁን ግን በየትም ቦታ የማይደረግ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በአንድ ምሽት ሰባት የተለያዩ አርቲስቶች የሚገኙበት ፌስቲቫል ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ብዙ ሰው ገና ግልጽ አልሆነለትም፡፡ ሰው ያነሰ የሚመስለው ወይም ካለፈው ያልበለጠበት ምክንያት በአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ በማስተዋወቃችን ነው፡፡ በአንዱ ሳምንት በተቻለን ሁሉ በማኅበረሰብ ድረ ገጽም ለማስተዋወቅ ሞክረናል፡፡ ለወደፊት በተሻለ መንገድ በጊዜ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንዲደግፉን በማድረግ፣ ያሰብነውን የፌስቲቫል ባህል ሀገራችን ውስጥ የማሳደግ እንዲሁም ፌስቲቫሎች በባህሉ ዘርፍ የራሳቸው ሚና እንዲኖራቸው የማድረግ ሀሳብ አለን፡፡ ያለፈው ዓመት ፌስቲቫሉ የተካሔደበት ቦታ አነስ ያለ ሲሆን፣ ግዮን በጣም ትልቅ ነው፡፡ ያለፈው ዓመት ሰው ቶሎ የሞላ ይመስላል፡፡ እዚያ የነበረው ሰው እንኳን ግዮን ቢመጣ ያነሰ ይመስላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የያሲን ቤ መቅረት ፌስቲቫሉ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለው ያምናሉ? በስምምነታችሁ መሠረትስ በቀጣይ ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ተሾመ፡- ያሲን ቤ በዓለማችን ትልቅ የተባለ አርቲስት ነው፡፡ አንድ ዓመት ለፍተን ነው ስምምነቱን ያደረግነው፡፡ ፕሮፌሽናልና ሕጋዊ ስምምነት አድርገናል፡፡ በእሱ በኩል የተጠየቀውን በሙሉ አሟልተናል፡፡ በሀገራችን ሕግ መሠረት የሚያስፈልገው ፐርሚሽን ቪዛ ተጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፌስቲቫሉ አንድ ቀን ሲቀረው መጀመሪያ ፍቃዱን ያገኘበትን የአሜሪካ ፓስፖርት ቀይሮ ወርልድ ሲቲዝን የሚል ፓስፖርት እንደያዘ ታወቀ፡፡ የቀየረው ፓስፖርት ብዙ አገሮች ስለማይቀበሉትና ሕጋዊነት ስለሌለው፣ ከኬፕታውን የሚነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፓስፖርቱ መንቀሳቀስ አትችልም ብሎ አገደው፡፡ ለእኛና እሱን ለሚወዱ አድናቂዎቹ ቅር አሰኝቷል፡፡ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በማኔጅመንቱና በአርቲስቱ ጥፋት ነው ያልተሳካው፡፡ በምን መንገድ ነው የምናስተካክለው የሚለውን እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰላም ድርጅት እንዲሁም ሰላም ሪከርድስና ሰላም ኢትዮጵያ እንዴት ተመሠረቱ፤ የተነሳችሁበት ዓላማስ ምን ነበር?

አቶ ተሾመ፡- ሰላም ኢትዮጵያ ስዊድን ያለው ሰላም ድርጅት ቅርንጫፍ ነው፡፡ ሰላም የተቋቋመው እኔ በምኖርበት ስቶኮልም ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የዌስት ኢንዲያን ባህሎችን፣ በስዊድንና ስካንዲኔቪያን አገሮች ውስጥ ለሕዝቡ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ በማቅረብ የታወቅን ነን፡፡ ፌስቲቫሎች፣ ኮንሠርቶች፣ ቱር፣ የክለብ ምሽት፣ ሴሚናርና ኮንፍረንስ በማዘጋጀት ብዙ የስዊድን ኅብረተሰብ ያውቀናል፡፡ ከመንግሥትና ሌሎች አጋሮቻችን ጋር በመሆን ጥሩ ግንኙነት የፈጠርንበት ድርጅት ነው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተራድኦ ድርጅት አቋቋምን፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያና የተለያዩ አፍሪካ አገሮችን የባህል ዘርፍ ማጠናከር የሚለውን መሠረታዊ ዓላማ ይዞ ተነሳ፡፡ ከስዊድን በሚገኙ የተለያዩ ዕርዳታዎች ብዙ ሥራ ሠርተናል፡፡ ሥራችን በኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሴኔጋል፣ ጋምቢያና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ይካሔዳል፡፡ የኢትዮጵያው ባለፉት አራት ዓመታት ጠንከር ያለበት ምክንያት የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ፍቃድ አግኝተን፣ የራሳችን ቢሮ ተከራይተን ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየሠራን ስለሆነ ነው፡፡ በግሌ ኢትዮጵያ ተወልጄ ስላደግኩና ኢትዮጵያዊ ማንነት ስላለኝ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገር ቤት ተመልሼ እንዲህ ባደርግ የሚል ህልም ነበረኝ፡፡ ብዙዎቻችን ውጪ የምንኖር ሰዎች ያለን ህልም ነው፡፡ ህልሙን ለማሳካት ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ብዙ ነገሮችም እያየን ነው፡፡ የተደራጀ ድርጅትና ጠንካራ ሠራተኞች ያስፈልጉናል፡፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር መሥራት ስለሚያስፈልገን ጠንካራ አጋሮች ያስፈልጉናል፡፡ ከመንግሥት፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሙዚቃና ሌሎች ማኅበራት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ የባህል ዘርፍ አድጐ ኢንዱስትሪ የሚሆንበትን መንገድ ለማየት እየደገፍን ነው፡፡ በተለይ በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ብዙ ውጤታማ ሥራ አሳይተናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ የተባለውን የሙዚቃ ስቱዲዮ መክፈታችን ነው፡፡ ስቱዲዮው ውስጥ ችሎታ ያላቸው ፕሮዲውሰሮችና ሙዚቃ አዋቂዎች አስተምረናል፤ እያስተማርን ነው፤ ለወደፊትም እናስተምራለን፡፡ የስቱዲዮው እዚህ መኖር ድሮ አርቲስቶች ውጭ ሀገር ሔደው ተቀድተው የሚመጡትን አቁሞ፣ ሀገራችን ውስጥ መሣሪያና የሠለጠኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ አገራችን ውስጥ ለአገራችንና ለውጭ አገርም ገበያ መቅረብ የሚችሉ ሥራዎችን ለመፍጠር ስቱዲዮው መከፈቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሌላው በኅብረተሰባችን ውስጥ ተጐጂ የሆኑትን መደገፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ለዓይነ ስውራን ሰላም በአቅሙ ምን ማድረግ ይችላል በሚል መነሻ ለሦስት ዓመት ያህል ሦስት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየሠራን ነው፡፡ አንደኛው ውሳጤ ብርሃን የሚባለውን የሙዚቃ ትምህርት ቤት መቶ በመቶ እየረዳን ነው፡፡ ቀድሞ ዓይነ ስውራን ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መግባት አይችሉም ነበር፡፡ ለ40 ዓመት ያህል ለምን አይገቡም በሚልና ትምህርት ቤቱም ዓይነ ስውራንን መቀበል አንችልም በሚል ክርክር ነበር፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ፕሮጀክት ቀርጸን ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ኖቢስ ከሚባል የዓይነ ስውራን ድርጅት ጋር በመሆን፣ የመንግሥት አካሎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና ግለሰቦችን በአንድ ጠረጴዛ በማነጋገር፣  በሚዲያ በመቀስቀስ እና ጥናት በመሥራታችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ መንግሥት ዓይነ ስውራን እንደ ማንኛውም ሰው እንዲፈቀድላቸው ወስኗል፡፡ ይሔ ትልቅ ውጤት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሰላም ካልቸራል ፎረም በየሁለት ወሩ የሚዘጋጅና ባለሙያዎች ተገናኝተው የሚወያዩበት መድረክ ነው፡፡ የፎረሙ ዓላማ በዩኒቨርሲቲ፣ በሚዲያ፣ በሙያ ማኅበራትም ያሉ ባለሙያዎች ተገናኝተው የሚወያዩበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ለዘርፉ ምን ያስፈልገናል፣ እንዴትስ ማሻሻል እንችላለን የሚለውን የሚወያዩበት ብዙ ፎረም የለም፡፡ ስለዚህ ሰላም ፎረሙን አዘጋጅቶ በየጊዜው ትልልቅ እንግዶች ይጠራሉ፡፡ እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም መንግሥት ከባለሙያው ጋር ተገናኝቶ ምን ያስፈልጋል የሚለውን የሚነጋገርበት ትልቅ ፎረም ነው፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኮፒ ራይት ኮሌክቲቭ ሶሳይቲ እንዲመሠረት በአቅማችን የተለያዩ አገሮችን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ለማስመጣት እየሠራን ነው፡፡ የኛ ሀገር ባለሙያዎች ወደ ሌላ ሀገር ሔደው ልምድ እንዲቀስሙ አድርገናል፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ድርጅቶች ጋር በመሆን የውጭውን ልምድ ወደ ሀገራችን አምጥተን፣ አንድ ቀን ሁላችንም የምናልመው የኮፒ ራይት ኮሌክቲቭ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሥርቶ፣ ባለሙያውን ማገልገል እንዲችል እያገዝን ነው፡፡ ሴቶች የባህል ዘርፉ ላይ ምን ሚና አላቸው በሚል ያደረግነው ጥናት አልቋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ለማየት ሞክረናል፡፡ ብዙ ቦታ በባህል ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ ያነሰ ነው፡፡ ችግሩ ከምን የመጣ ነው? ሴቶች እህቶቻችን ለምን ንቁ ሆነው አይሳተፉም? የሚለውን አጥንተናል፡፡ በቅርቡ የመወያያ መድረክ እናዘጋጃለን፡፡ ጥናት ሆኖ የሚቀር ሳይሆን ለወደፊት ምን እንሥራ የሚለውን የምንፈትሽበት ነው፡፡ ሌላው የካልቸር ሊደርሺፕ ፕሮጀክታችን ነው፡፡ እንደማንኛውም ሙያ የባህል ዘርፍ ውስጥ በመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤትና በሚዲያም ያለው ባለሙያ የካልቸራል ሊደርሺፕ ትምህርት ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን፡፡ ወደፊት ጠንካራ የሆነ የባህል ኢንዱስትሪ እንዲኖር፣ ባለሙያው ሀገሩን መርዳት የሚችል እንዲሆንና ያለንን ትልቅ የባህል ሀብት እንድንጠቀም በትምህርት የተገነባ ዘርፍ መመሥረት አለብን፡፡ ከስዊድን የመጡ ኤክስፐርቶች ከመንግሥት ድርጅቶችና የተለያዩ ሰዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፤ ልምዳቸውንም አካፍለዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ይህን ትምህርት ለማስተማር አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀን ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሌላው ፌስቲቫሉ ሲሆን፣ የባህል ዘርፉን በማጠናከር ባለሙያውና ሀገሪቱም የምትጠቀምበት መንገድ የመፍጠር ሚና አለው፡፡ ሀገራችን ውስጥ ፌስቲቫሎችና ትልልቅ ዝግጅቶች ቢዘጋጁ፣ ሀገር ውስጥ ያሉ ታዳሚዎችንና ውጭም ያሉትን በመሳብ ሀገራችንን ወይም ከተማችንን እንደ አንድ የሙዚቃ ከተማ መጠቀም እንችላለን፡፡ ሚውዚክ ሊድስ ዘ ዌይ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ጋር የምንሠራው ነው፡፡ በዘፈን፣ ግጥም በመጻፍ፣ በማቀናበር፣ ፕሮዲውስ በማድረግና በሌላም ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡ ችሎታ ቢኖራቸውም ዕድሉን ስለማያገኙ ችሎታቸውን መጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ እናያለን፡፡ ሰላም በአቅሙ የተወሰኑ ወጣቶችን በማሰባሰብ የሙያ ማሻሻያና ችሎታቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበትን መንገድ ለመፍጠር የተለያየ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ የስቱዲዮ ኮርስ፣ የዘፈን፣ የቅንብር፣ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ አጠቃቀምና ሕግን በተመለከተ ከሁለት ዓመት በላይ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ጋር እየሠራን ነው፡፡ ማኅበሩ ተጠናክሮ አባላቱን እንዲሁም አባላት ያልሆኑትንና የሙዚቃውን ዘርፍ እንዲረዳ ብዙ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት ማኅበሩ ድንቅ የሆነ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ በጣም ጠንካራ ሠራተኞች በቢሯችን አሉ፡፡ ውጤታችንን ያተለቀውም ያ ነው፡፡ በቅርቡ ሰላም ሳውንድ የሚባል ድርጅት አቋቁመናል፡፡ ከኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ ሥራዎችን ለዓለም ገበያ በምን መንገድ እናደርሳለን የሚለውን ተመርኩዞ የተነሳ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ ፕሮጀክቶቻችሁ በወጣቶችና ዓይነ ስውራን ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ሰላም ሳውንድ ደግሞ በቅርቡ የኢትዮ ከለርን ባህላዊ ሙዚቃዎች አልበም አሳትሟል፤ በእነዚህ ላይ ለምን አተኮራችሁ?

አቶ ተሾመ፡- በሀገራችን ብዙ የሚያስደንቅ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች እንዳሉ እናምናለን፡፡ የሚቀጥለውን ትውልድ ለማየት ከአሁኑ ወጣቶችን መደገፍ አለብን፡፡ ትልልቆቹና የታወቁት ዘፋኞች በራሳቸው ጥረት ትልልቅ ሥራ እየሠሩ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ እነሱ በራሳቸው አቅም ብዙ ነገር መሥራት ይችላሉ፡፡ ብዙዎቹ ወጣቶች ግን ሙያቸውን ሳይጠቀሙበት፣ አንዳንዶቹ በማይፈልጉት ሥራም ይሰማራሉ፡፡ ብዙ የሙያ ትምህርት ቤቶችም የሉንም፡፡ ያልታዩ ብዙ ታሪከኛ ወጣቶች አሉ፡፡ የባላገሩ ምርጥ እንደምሳሌ የሚታይ ነው፡፡ የተደበቀ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ከተረዱ ብዙ ይሠራሉ፡፡ የዘንድሮው የባላገሩ ምርጥ አሸናፊ ለተወሰነ ጊዜ በሰላም ኧርባን አዲስ ፕሮጀክት ተሳትፏል፡፡ አራተኛ የወጣው ደግሞ በዓይነ ስውራን ፕሮጀክት ከእኛ ጋር እየሠራ ያለ ዘፋኝ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን የምደግፍበት ምክንያት ክፍተት ስላለ ነው፡፡ ኢትዮ ከለርን ብንመለከት ድንቅ የሆኑ ሙዚቀኞች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው፡፡ የሚገርም ችሎታ ያላቸው አርቲስቶች፣ ሥራዎቻቸው ግን ታትመው ያልተቀመጡ ነበሩ፡፡ አምነንበትና የዚህ አገር ሙዚቃ ለውጭ ገበያም መቅረብ አለበት በሚል ያደረግነው ነው፡፡ የሚገርሙ ሥራዎችን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በማቅረብ ሀገራቸውንም እያስተዋወቁ ነው፡፡ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ቢኖሩንም፣ የምንሠራው ሥራ ያለ ዕድሜና ጾታ ልዩነት የባህሉን ዘርፍ የሚያግዝ ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው መሠረት እንዲተከል ነው፡፡ ዘርፉን በደንብ ለማስተካከልና ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ መሠራት አለበት፡፡ ከመንግሥት ጀምሮ፣ ፖሊሲውን በተግባር የሚያውሉ አካላቶችና የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች መጠናከር አለባቸው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆነ የአመራርና የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች መስፋት አለባቸው፡፡ የሙያ ማኅበሮች ያስፈልጉናል፡፡ ጠንካራ የሆኑ የሙያ ማኅበሮች ከሌሉ የሙዚቃውን ዘርፍ የሚያስከብርና የሚጨነቅለት አይኖርም፡፡ ተባብረንና አንድ ሆነን ካልቀረብን ዕድገትም አይመጣም፡፡ ሌላው የንግዱ ዘርፍ ነው፡፡ ንግድ መኖሩ ሲታወቅ ኢንቨስት ይደረጋል፡፡ የንግዱን ዘርፍ መደገፍ መሠረት ለመገንባት ከሚያስፈልጉ ነገሮች ጋር ይገናኛል፡፡ የሚዲያ ዘርፉም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በዋነኛነት በባህል ዘርፍ የሚሠሩ ጋዜጠኞች በትምህርት ሙያቸው ቢገነባ በዘርፉ ትልቅ ዕድገት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ዘርፉንም ሙያዊ በሆነ መንገድ መተቸት ይቻላል፡፡ ፕሮፌሽናል ሒስ ካለ ደግሞ እየተነጋገርን መሻሻል ያለባቸው መንገድ ይይዛሉ፡፡ ይሔ ሁሉ ነገር አብሮ ማደግ ካልቻለ በአንድ ፌስቲቫል ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ እኛ ሰላም ፌስቲቫል ብለን ስንጀምር ሌላው ቢቀጥል ዘርፉ ያድጋል፡፡ የባህል መሠረተ ልማት ስንል ያልኩትን ነገሮች በሞላ ያጠቃለለ ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- ሰላም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ አበርክቷል?

አቶ ተሾመ፡- በሀገር ውስጥ ከሀገር ውጭም እኛ ከምንናገር ሌላው ቢናገርልን ይሻላል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃና ባህል በተለይ በስካንዲኔቪያን አገሮች በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እየተጫወትን ነው፡፡ በቅርቡ በስቶኮልም ከተማ ውስጥ በስቶኮልም የባህል ፌስቲቫል ላይ የኢትዮጵያ ምሽት ተብሎ ከ8,000 ሰው በላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ እነ ጋሽ መሐሙድ፣ ጋሽ ዓለማየሁ እሸቴና ኢትዮ ከለር የሚያስደንቁ ሥራዎች አቅርበዋል፡፡ መሀል ስቶኮልም ላይ እንዲህ ያለ ዝግጅት ማዘጋጀት ከባድ ነው፡፡ እነ አስቴር አወቀ፣ ቴዲ አፍሮና ሌሎችንም ድንቅ አርቲስቶችን በመጋበዝ ሥራቸውን እያሳዩ ነው፡፡ እዚህ የምናደርጋቸው ሥራዎች በብዛት ትክክለኛ ውጤት እያሳዩ ነው፡፡ ፌስቲቫላችን አድካሚና ውድ ቢሆንም ከዓለም ድንቅ አርቲስቶች ወደ ኢትዮጵያ እናመጣለን፡፡ ዘርፉን ይጠቅማል በሚል ሳንሰለች ለአምስተኛ ጊዜ አድርሰነዋል፡፡ የባህል ዘርፉን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ እያንኳኳን ይህን ብናደርግ እንላለን፡፡ ውጤታችንን መናገር የሚችለው ሌላው ቢሆንም፣ ባለን ስትራቴጂና ዕቅድ በብዙዎቹ ነገሮች ጥሩ ነገር እያየን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በእንቅስቃሴያችሁ የገጠሟችሁ መሰናክሎችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ተሾመ፡- ፈተና የምንለው የባህል ዘርፉ የተዋቀረ አለመሆኑን ነው፡፡ በባህል ዘርፍ ጠንካራና የተደራጁ ማኅበሮች አሉ ብለን አንገምትም፡፡ በደንብ የተዋቀሩ ድርጅቶች ቢኖሩ ሥራችንን ያቀልልናል፡፡ የተለያዩ ቢሮክራሲያዊ ችግሮችም አሉ፡፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተን ሥራዎች ፈጠን ብለው እንዲሠሩ እንፈልጋለን፡፡ አንዳንዴ ለባህሉ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት የማይሰጥበት ሁኔታ እናያለን፡፡ ይሔ ፈታኝ ነው፡፡ ሌላው በተለያዩ ድርጅቶች ያሉ ኃላፊዎች ትስስር ያነሰ መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ነን እንዲህ እናድርግ ብለን የምንሔደው እንጂ፣ እንዲህ እናድርግ የሚለን ሌላ አካል ያንሳል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ አንድ ላይ ቁጭ ብለን ብንወያይ አሁን ካለን ውጤት የበለጠ እናገኛለን፡፡ ወደ አሥር ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ውስጥ ከገባን ብዙ ፈተናዎች አሉ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያመጣው የባህል ዘርፉ እንደሌላው ዘርፍ ጠንካራ ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ነው፡፡ ከመንግሥትና ከሁሉም አካላቶች እየተረዳዳ ዘርፍን ጠንካራ ማድረግ አለብን፡፡ ይሔ የሚሆነው ደግሞ በትምህርት ሲደገፍ ነው የምንለው ትልቅ ክፍተት ስላለ ነው፡፡ ነገሮች መስመር ቢይዙ ፌስቲቫል ስናዘጋጅ የሚገጥሙን ችግሮች ሊስተካከሉ ይችላሉ፡፡ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ወደ አገራችን በቀላሉ፣ በፍጥነት አስገብተን ታሪካዊ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ እኛ ሀገር ለአንዳንድ የሙያ ዘርፍ ልዩ ዕርዳታ አለ፡፡ ያ ዘርፍ እንዲያድግ በማሰብ ታክስ ማቅለልና ሌሎችም ዕርዳታዎች ይደረጋሉ፡፡ የባህል ዘርፉ እንዲጠናከር ከፈለግን ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን፡፡ በባህሉ ዘርፍ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ በጣም ብዙ ይቀረናል፡፡ በሀገራችን ልዩ የባህል ሀብት አለ፡፡ በሙዚቃው፣ በፊልሙና በሌሎችም ዘርፎች ከማንም የማያንስ አቅም አለን፡፡ በሙያዊ መንገድ እስካልተገነባ ግን ጊዜያዊ ሆኖ ይቀራል፡፡ እንደሚታወቀው በሙዚቃው ዘርፍ ከፍተኛ ችግር ያለው በሥርጭትና በኮፒ ራይት ጉዳይ ነው፡፡ ሥርጭትና የኮፒ ራይት ጉዳይ አብረው ይሔዳሉ፡፡ መብት የሚያስጠብቅ አካል ከሌለ መብት አይጠበቅም፡፡ ገበያ ላይ የወጣውን ሥራ በሕጋዊ መንገድ ማሠራጨት ካልተቻለ እንዴት ይከፋፈላል የሚለው ያሳስበኛል፡፡ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ በፈጣን መንገድ ቢሔድም መሟላት ያለባቸው ነገሮች ቢሟሉ የበለጠ ይፋጠናል፡፡ ሰላም ያለው ህልም ሰፊ ነው፡፡ ያ የመጣው ካለን የፍቅር ስሜት ነው፡፡ አንዳንዶች በሆነ ፈንድ የተመሠረተ የተራድኦ ድርጅት ነው የሚል አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኔ ስዊድን ውስጥ እንደማንኛውም ስዊድናዊ ቁልፍ ኔትወርኮች አፍርቻለሁ፡፡ ኔትወርኮቹን ለሀገሬ ለኢትዮጵያ እንዴት አድርጌ አካፍላለሁ የሚለውን ሁሌ አስባለሁ፡፡ የሰላም ፍላጐት ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮች ያላቸውን አቅም ከሚጠቀሙበት በበለጠ ያላትን አቅም እንድትጠቀምበት ማድረግ ነው፡፡ ወደተለያዩ አገሮች ስጓዝና አንድ ነገር ሲያደርጉ ሳይ እነሱ ካደረጉት እንዴት እኛን አቃተን የሚል ስሜት ይሰማኛል፡፡ መንግሥት፣ ትምህርት ቤቶችና የተለያዩ ድርጅቶች ብንደጋገፍ ከሀገራችን የባህል ዘርፍ እንደማንኛውም ዘርፎቻችን ተጠቃሚ የምንሆንበት መንገድ አለ፡፡      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች